ማክሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ከመሬት መንሸራተት አደጋ ጋር በተያያዘ ስጋቶች እንዳሉ ተገልጿል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት በዞኑ ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም አደጋ የደረሰባቸውን ዜጎች የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ ካሳሁን አባይነህ አሁንም ግን በዞኑ በተለይም በ3 ወረዳዎች ላይ የመሬት መንሸራተት አደጋ ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ያስችላል የተባለ ስራ ከክልል እስከ ፌዴራል በተዘረጋ መዋቅር እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ሃላፊው በሶስቱ ወረዳዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችን የአደጋ ስጋት ካለበት ቦታ የማስወጣት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል ብለዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየደረሰ ያለው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን እያስከተለ ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ በትናንትናው እለት በክልሉ ወላይታ ዞን በደረሰው ተመሳሳይ አደጋ የሟቾች ቁጥር 11 መድረሱን የክልሉ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን መግለጹ ይታወቃል፡፡
በጎፋ ዞን የደረሰውን አደጋ ተከትሎም በስጋት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችን 170 ሺህ ሄክታር የሚሆን ቦታ ላይ እንደ አዲስ የማስፈር ስራ እየተሰራ መሆኑንም ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡



