👉🏿በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ቀጥታዊ ያልሆነ ውይይት እንደቀጠለ መሆኑ ተሰምቷል
ማክሰኞ 07 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአንካራ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ውይይት ዛሬ እንደቀጠለ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በትላንትናው ዕለት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ያለመ ሁለተኛ ዙር ንግግር በቱርክዬ አንካራ መጀመራቸው ይታወቃል።
ይሁን እንጂ የሁለቱም ሀገራት ተወካዮች ፊት ለፊት ሳይገናኙ በቱርክዬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን አስተባባሪነት ውይይታቸውን እያካሄዱ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
የቱርኩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለቱንም ተደራዳሪዎች በተናጠል በማወያየት ልዩነቶቻቸውን እንዲያጠቡ ጥረት እያደረጉ ሲሆን በትላንትናው እለት ሃካን ፊዳን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አፅቀስላሴ እና ከሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አህመድ ሞአሊም ፈቂ ጋር መክረዋል፡፡
ከሩሲያ ቱዴይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ውይይቱ መልካም ነገር ይዞ ይመጣል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶሃን ከኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህ ጋር በስልክ መወያየታቸው መዘገቡ ይታወሳል።
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ነሐሴ 4 ቀን ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር እና ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን ውዝግብ በሰለማዊ መንገድ ለመፍታት መምከራቸው ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል የተካሄደው ውይይት በስምምነት አለመጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡
በተጨማሪም በሰኔ 24 ቀን 2016 በቱርክ ጋባዥነት ወደ አንካራ ያቀኑት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞሊም ውይይታቸውን ለመቀጠል በነሃሴ ወር መጨረሻ ለመገናኘት መስማማታቸውን አሳውቀው ነበር፡፡
ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ከስድስት ወራት በፊት በተፈረመ የባህር በር መግባቢያ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እየተወያዩ ነው፡፡



