ማክሰኞ ነሐሴ 07 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድር የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን በዛሬው ዕለት በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ግብዣ ተደርጎለት ነበር።
በግብዣ እና ሽልማት ዝግጅቱ ላይ በውድድሩ ለኢትዮጵያ ሜዳልያዎች ያስገኙ አትሌቶች እና አሰልጣኞች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በውድድሩ ለሀገራችን ብቸኛውን ወርቅ ያስገኘው አትሌት ታምራት ቶላ ሰባት ሚልዮን ብር እና የወርቅ ኒሻን ሽልማት ተበርክቶለታል።
የታምራት ቶላ እና ትግስት አሰፋ አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ በበኩሉ የሁለት ሚልዮን ብር ሽልማት ለመቀበል ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
በዝግጅቱ ላይ መልዕክቱን ያስተላለፈው አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ “ ፕሬዝዳንታችን እኛ አሰልጣኞች ለረጅም ጊዜ ለፍተናል ፣ ልፋታችንን አይመጥንም “ ብሏል።
አያይዞም “ ለኔ ሁለት ሚልዮን የስድብ ያህል ስለሆነ እርስዎን ካላስከፋዎት ይሄንን ሽልማቴን መመለስ እፈልጋለሁ” ስለማለቱ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።



