ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከሰሞኑ በኢትዮጵያና ሱማሊያ መካከል የተከሰተውን ዲፕሎማሲያዊ ቁርሾ ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች መሰጠታቸው ቀጥለዋል፡፡
የሱማሊያ መንግስትም ሆነ የሞቃዲሾ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ በአገሪቱ ሰላም እንዲመጣ ያደረገችውን ጥረት ከምንም ሳይቆጥሩ እንደ ግብጽ ካሉ የኢትዮጲያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር መተባበራቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋግረው ይችላል የሚሉ ወገኖችም በርካቶች ናቸው፡፡
ከዚህ ሰሞነኛ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ኢትዮጲያን ለመውረር ማለም የቀን ቅዠት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
እንደ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምንም ዓይነት የፀጥታ ሥጋት እንዲኖር አልፈልግም ያሉት ሚኒስትሩ ነገር ግን በኢትዮጵያ አቅም በተለይም በሕዝቦቿ ስለምተማመን እንቅልፍ አልባ ሌሊት የለኝም ሲሉ አነጋሪ አስተያየትን ሰጥተዋል፡፡
አክለውም ግብፅ በሶማሊያ በኩል መጥታ ኢትዮጵያን አጣቢቂኝ ውስጥ መክተት ትችላለች ማለት የቀን ቅዠት ነው ሲሉ ገልጸዋል ።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘም የሞቃዲሾ መንግስት የክተት አዋጅ በፕሬዝዳንቱ በኩል ማስነገሩ ታውቋል፡፡
ሁሉም ሱማሊያዊ ለሚመጣው ፈተና ይዘጋጅ ሲሉም ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼህ መህመድ ጦርነት ጎሳሚ ቅስቀሳ ማድረጋቸውም እየተነገረ ነው፡፡



