በኦሮሚያ ‘የሽማግሌዎችን ትዕዛዝ አላከበረችም’ የተባለች እናት በተፈጸመባት ግርፋት ተጎድታ ሆስፒታል ገባች

0
500

ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) በምስራቅ ቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ‘የሽማግሌዎችን ትዕዛዝ አላከበረችም’ በሚል ከዛፍ ጋር ታስራ በባለቤቷ የተደበደበችው እናት በአስጊ ጤና ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የቤተሰብ አባሏ ተናገሩ።

በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ ሆስፒታል በህክምና ላይ የምትገኘው ኩሹ ቦናያ የተባለችው እናት በደረሰባት ግርፋት ክፉኛ ተጎድታ የአካሏ ግራ ክፍል አይሰራም። የራስ ቅሏ ተሰብሯል በማለት የቤተሰብ አባሏ ገልጸዋል።

የአካባቢው አቃቤ ሕግ በበኩላቸው ግርፋቱን መፈጸማቸው የተጠረጠሩ ባለቤቷን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መካሄዱን ተናግረዋል።

የሦስት ልጆች እናት የሆነችው እናት በኦሮምያ ምስራቅ ቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ የሽማግሌዎችን ትዕዛዝ አልተቀበለችም በሚል ከዛፍ ጋር ታስራ በባለቤቷ የተገረፈችው ግለሰብ በአሁን ሰዓት በሐዋሳ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እያደረገች መሆኑ ተገልጿል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች መካከል የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፈዋል የተባሉት ሽማግሌዎች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ሲለቀቁ ባለቤቷ ግን አሁንም በቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አቃቤ ሕግ ገልጿል።

የሦስት ልጆች እናት የሆነችውን ሴት ዋጪሌ ገበያ ላይ አስሮ የመግረፉ ድርጊት የተፈጸመው ባለፈው ወር መስከረም 9/ 2017 ዓ.ም. መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here