ማክሰኞ ታህሳስ 22 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) እናት ፓርቲ ደረሰኝ ባለው መረጃ በወላይታ ዞን፣ አበላ አባያ ወረዳ፣ አባያ ክላስተር በሚባል የእርሻ ልማት ከሲዳማ ክልል መጡ በተባሉ የልዩ ኃይል አባላት እንደተከፈተ በተገለጸ ተኩስ የሰው ሕይወት ማለፉን እና በርካታ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል እንደሚገኙ ገልጻል፡፡
በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት እንደቀጠለ ሲሆን “ችግሩ ትኩረት ሰጥቶ የሚፈታው አጥቶ እንጂ የሰነበተ ነው” የሚሉት ነዋሪዎች “የአሁኑ ግን ኃይል የቀላቀለና ለአገር ብዙ ውለታ የዋሉ የቀበሌው አስተዳደር ጭምር በተኩስ የተገደሉብት ጭምር ነው” በማለት መግለጻቸውን አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በወላይታ ዞን፣ ሁምቦ ወረዳ፣ ጠበላ ከተማ አስተዳደር ሥር ከጥምቀተ ባህር ይዞታ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ ፓርቲው አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም ከጥንት ጀምሮ የጥምቀተ ባህር የነበረ ይዞታ በቀበሌው አስተዳደር ጠረጴዛ ልማት ማኅበር ለሚባል የተወሰነ ቆርሶ የሰጠና ልማት ማኅበሩም ቀጥሎ ሙሉ በሙሉ በማጠሩ በተፈጠረ ችግር ተበደልን ባሉ ካህናትና ምዕመናን ላይ ፖሊስ እሥርና ከፍተኛ እንግልት እያደረሰ እንደሚገኝ ከአካባቢው ነዋሪዎች ለማወቅ መቻሉን ፓርቲው አመላክቷል፡፡
እናት ፓርቲ የተፈጠረውን ችግር የክልሎቹ መንግሥታት እንዳላዩ ከማለፍ በአፋጣኝ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊና ሕጋዊ መፍትሔ እንዲሰጡ፣ ማኅበረሰቡም በክልሉም ከክልሉም ውጭ እረፍት የሚያገኝበትን ሁኔታ እንዲመቻች አሳስቧል።



