ዳሰሳ ዘ ማለዳ (የካቲት 27/2012)

0
788

የዓለም ባንክ ለአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር የሚያግዝ የ25 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው

የዓለም ባንክ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር ማህበራዊ መሰረተ ልማት ለማቅረብ የሚያግዝ 25 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት መወሰኑን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል። የዓለም ባንክ ድጋፍ የተቋሙ የከተማ ምርታማነት ሴፍቲ ኔት መርሐ ግብር አካል መሆኑ ተገልጿል።(ኢቢሲ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

በምስራቅ ጎጃም ዞን በእናርጅ እና እናውጋ ወረዳ ደብረወርቅ ከተማ በቤት ውስጥ ከተቀመጠ ቤንዚን ጋር ተያይዞ በተነሳ እሳት ቃጠሎ የእናትና ልጅ ህይወት ማጥፋቱን ፖሊስ አስታወቀ። የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኮማንደር መኮንን ጎሹ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ትናንት እኩለ ቀን አካባቢ ነው። ከመኖሪያ ቤት በተጓደኝ በነበረ ማብሰያ ቤት ውስጥ ለባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ባጃጅ በጀሪካን ተገዝቶ የተቀመጠ ቤንዚን በረንዳ ላይ ከነበረ እሳት ጋር ተቀጣጥሎ በመያያዙ አደጋው ሊደርስ ችሏል። (ኢዜአ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያካሄደው የዩንቨርሲቲ ምሩቃን ቅጥር ፍትሃዊ እንዳልነበር ተፈታኞች ገለጹ። ከተማ አስተዳድሩ የስራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት በሚል ከ8 ሺህ በላይ በ2010 እና 2011 የተመረቁ ወጣቶችን በተለያዩ ተቋማት ቀጥሯል። ፈተናዉ የታረመበት መንገድ እና የቅጥር ሁኔታዉ ግልፅ እና ገለልተኛ አይደለም በሚል በርካታ ተፈታኞች ቅሬታቸዉን  ተናግረዋል፡፡የከተማዋ አስተዳድር በበኩሉ ቅጥሩ እና ፈተናው ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ መከናወኑን ገልጿል።(ኢትዮኤፍኤም)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የኮሮናቫይረስ ባስከተለው ስጋት ምክንያት በአዲስ አበባ ሊካሄዱ ታቅደው የነበሩ ስብሰባዎች በመሰረዛቸው በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆቴሎች ገቢ ላይ ተጽእኖ እንደሚያስከትል ተነገረ።የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ሰብሳቢ  ቢኒያም ብስራት  እንደተናገሩት በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ ባይከሰትም በሌሎች አገራት ውስጥ ባለው ሁኔታ ሳቢያ ተጓዦች ቀደም ሲል የያዙትን እቅድ እየሰረዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።(ቢቢሲ አማርኛ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የሰላም ሚኒስቴር ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቅንጅት ለመስራት የሚያግዘውን ስምምነት ተፈራረመ። ሚኒስቴሩ ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ – ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሰላምና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የምክክር፣ የስልጠና እና የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።ስምምነቱ የፀጥታ እና ፍትህ አካላትን አቅም ግንባታ ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል እንደሆነም ተነግሯል፡፡(የሠላም ሚኒስቴር)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ኢትዮጵያ የዓረብ ሊግ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብፅን በመደገፍ ያወጣውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አደረገች። ይህን የውሳኔ ሀሳብም የሊጉ አባል የሆነችው ሱዳን የታቃወመች ሲሆን፥ የውሳኔ ሀሳቡ የዓረቡን ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር የሚያጋጭ እና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት በሀሳቡ ላይ ስሟ እንዳይሰፍር እስከመጠየቅ በመድረስ ተቃውማለች። የዓረብ ሊግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ባለፈው ረቡዕ ባካሄደው ስብሰባው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የግብፅን አቋም በመደገፍ የውሳኔ ሀሳብ ማውጣቱ አይዘነጋም።(ኢዜአ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የንግድ ስራን ምቹና ቀልጣፋ የሚያደርግ ብሔራዊ የንግድ ፖርታል ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ይፋ ተደረገ። አገልግሎቱ ዜጎች ኢንተርኔትን ተጠቅመው የግንባታ ፍቃድ አሰጣጥ አገልግሎትን፣ የንግድ ስራ አጀማመርና ፍቃድ አወጣጥ ሂደትን እንዲሁም የመረጃ አሰጣጥ ስራን ኦንላይን በሆነ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 31 የመኪና ስርቆት ወንጀሎች ተመዝግበው ሁሉንም ተጠርጣሪዎችን ከነ ኤግዚቢቶቻቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በከተማዋ የተለያዩ ክፍለ-ከተሞች የመኪና ሥርቆት ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታወቋል።(ኢዜአ)

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here