የኮሮና ቫይረስን ለመከታተል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሪፖርቱን አቀረበ
የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ያለበትን ሁኔታ ለመከታተል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሪፖርቱን ዛሬ የካቲት 30/2012 አቅርቧል፡፡
የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና የጤና ሚንስትር ዴኤታ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ምርመራ የተደረገላቸው 38 ሰዎች ቢኖሩም ሙሉ ለሙሉ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በምርመራ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ (ኢቢሲ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..
በነሐሴ መጨረሻ የሚደረገውን አገር አቀፍ ምርጫ የሚታዘቡ 125 የሲቪክ ማህበራት ዛሬ የካቲት 30/2012 ባደረጉት ስብሰባ ላይ በይፋ መቀናጀታቸውን የቅንጅቱ ሰብሳቢ ብሌን አስራት ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ። ከዚህ ቀደም በሕዝብ ታዛቢዎች ብቻ ሲደረግ የነበረውን አገራዊ ምርጫ፣ከዚህ በኋል ግን ቅንጅቱ በምርጫ ታዛቢነት የሚሳተፍ ይሆናል።
(አዲስ ማለዳ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..
መንግሥት የህዝብ አንድነትና አብሮነት እንዲሸረሸር በሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ። የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት፣ በህዝባዊ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን በኩል የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች በአገር አንድነትና አብሮነት ላይ አደጋ ይደቅናሉ።ከዚህ አንጻርም በመሰል ድርጊት በሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ተገቢና ተመጣጣኝ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ አስታውቀዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..
የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማጠናከሪያ መርሃ ግብር የሚውል የ26 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ። መርሃ ግብሩ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና የአውሮፓ ኅብረት የመርሃ ግብሩን መጀመር በአዲስ አበባ አብስረዋል።(ኢዜአ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀዉ ከኢቲ አር ኤስ ኤስ ዋን ሳታላይት የሚቀበለዉን የምስል መረጃ ለተለያዩ ተቋማት በቅርቡ መሸጥ እጀምራለሁ አለ። የኢንስቲትዩቱ የሳታላይት ተቆጣጣሪ ባለሙያ እሸት ተስፋዬ በቅርቡ የመጠቀችዉ ሳታላይት መረጃ መላክ ከጀመረች ከሁለት ወር በላይ ሆኗታል፤ በቅርቡም መረጃዎቹን ለሚፈልጉ ተቋማት እንሸጣለን ብለዋል።(ኢትዮኤፍኤም)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መንግስት የሃሳብ ነጻነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲያድግ የፖለቲካ ምህዳሩን ቢያሰፋም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ፈር እየለቀቁ እንደመጡ መመልከቱን ገልጿል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን አንዷለም እንዳሉት ተቋሙ በሁሉም ዘርፍ የሚዲያ ነጻነት እንዲረጋገጥና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን ለማገዝ ኢ ፍትሀዊ ሀሳቦች ሲተላለፉ በተለያየ መንገድ ለመፍታት እየጣረ ነው ብለዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ዛሬ የካቲት 30/2012 ጠዋት ተገናኝተው በርካታ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መምከራቸው ተገልጿል። በሠራዊቱ ዘንድ የሚከናወኑ ተቋማዊ እና መዋቅራዊ ለውጦችን በተመለከተ ምዘና ማድረጋቸው ተነግሯል። (የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..
“የጋሞ አባቶች የሰላም ተምሳሌትነት ለሃገር ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ የካቲት 30/2012 በሚለኒየም አዳራሽ ታካሄደ። የጋሞ ልማት ማህበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማና የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የአዲስ አበባ እና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። (ከንቲባ ጽኀፈት ቤት)



