በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ የጎብኚዎች መዳረሻ ስፍራዎች የተዘጉ ሲሆን ከአንድ ወር በኋላ ወይም በጥቅምት 2013 ለጎብኚዎች ክፍት ሊሆኑ እንደሚችሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ክፍት ሊሆን እንደሚችሉ የተነገሩት የጎብኚዎች መዳረሻ የነበሩ ስፍራዎች፣ ቅርሶች፣ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ተብለው የተለዩትን እንደሆነም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ተወካይ ዳይሬክተር የሆኑት እንደገና ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ይህ ማለት ግን ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም በሆነው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ያልተመዘገቡ ቦታዎች ተደራሽ አይሆኑም ማለት ሳይሆን ቱሪስቶቹ ማየት እና መጎብኘት የሚፈልጓቸው ቦታዎች ክፍት እንደሚሆኑ ነው የተነገረው።
በአሁን ወቅት ኢትዮጵያን ለቱሪስት ክፍት የማድረግ ዘመቻ እየተሰራ እንደሆነ የጠቀሱት እንደገና፤ የቱሪስት መዳረሻዎችን ክፍት ለማድረግ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ ተቋመት ጋር በጋራ እየሰራን እንገኛለን ሲሉም ጠቁመዋል።
በጋራ ከምንሰራቸው ተቋማት ውስጥ የሆቴሎች ማህበራት ሲሆኑ፤ ሆቴሎችም ቢሆን ዝግጁ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ለቱሪስት ክፍት የሚሆን ምንም ዓይነት መዳረሻ የለም ብለዋል።
እንዲሁም በአስጎብኚ ድርጅቶች በኩልም ተገቢው ስራ ሲሰራ መዳረሻ ቦታዎች ክፍት እንደሚደረጉ እንደገና ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በመሆኑም የውጭ አገራት ቱሪስቶች በእኛ በኩል ስራችንን ጨርሰን መምጣት ትችላላችሁ ብለን ካላሰወቅን በስተቀር ማንኛውም ጎብኚ መሰባሰብ እንደማይችልም አመላክተዋል።
ለዚህም ሲባል ጎብኚዎች ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ እንዴት መግባት እንዳለባቸው እና ሌሎችም ዝርዝር መስፈርቶች በአሁን ሰዓት ተዘጋጅቶ ውሳኔ ብቻ እየተጠበቀ እንደሆነ እንደገና ገልጸዋል።
የተዘጋጀው ፕሮቶኮልም አንድ ቱሪስት የኮቪድ 19 ወረርሽን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዴት ወደ ቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ጉብኝት ማድረግ እንዳለበት ይጠቆማል ነው ያሉት።
ስለሆነም በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል ሲባል በመንግስት በኩል እንቀስቃሴዎች እንዲገደቡ የተደገረው በአዋጅ ስለሆነ መዳረሻዎችም በአዋጅ ክፍት መሆናቸው ይነገራል ብለዋል።
በባህልና ቱሪዝም በኩል የኮቪድ 19 ወረርሽኝል በመከላከል ቱሪስቶች መጎብኛት ያስችላቸዋል ያልናቸውን መንገዶች ሁሉ ያዘጋጀን ሲሆን ሙሉ በሙለ ግን ወደ ተግባር ለመግባት የጤና ሚኒስቴር የሚሰጠን ውሳኔም እየተጠባበቅን እንገኛን ሲሉ ምላሻቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።
ምላሹ ከተሠጠ በኋላም በአገር አቀፍ ደረጃ የቱሪስቶችን የመዳረሻ ቦታዎች ክፍት በማድረግ ስራውን ሙሉ በሙሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚቆጣጠረው እንደሆነ ነው የተገለጸው።
የዘንድሮው የመስቀል በአልም በአገር አቀፍ ደረጃ ከዚህ ቀደም ይከበር እንደነበረው እንደማይከበር የተናገሩት እንደገና በመስከረም ወር ላይ የሚከበሩት የመስቀል በዓልና የኢሬቻ በዓላት ጎብኚዎች የማይታደሙበት እንደሚሆን ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅበር በበኩሉ ሆቴሎችን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ ከባህልና ቱሪዝም ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ሆቴሎቹ በድጋሚ ሲከፈቱ ከደህንነት አንጻር እንዴት እና ምን ማካተት አለባቸው የሚለውን የሚመልስ የሆቴሎችን ስራ የሚያመለክት ፕሮቶኮል ቀርጸናል ሲሉ የማሀበሩ ስራ አስኪያጅ ዳንኤል ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ሆቴሎች ከሚሰሯቸው ሥራዎች መካከል ሠራተኞቻው ስለ ኮቪድ19 በቂ ሥልጠና የወሰዱ መሆን እንዳለባቸው መገልገያ ቁሶችም ቢሆንም ደህንነታቸው የተረጋገጠ መሆን አለበት የሚለውን ጠቅሰዋል።
ማህበሩ በስሩም 156 ሆቴሎች እና 18 ሺህ የሚሆኑ ሠራተኞች እንዳሉት ከማሕበሩ ለማወቅ ተችሏል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በ2012 በጀት ዓመት እስከ ሰኔ ወር ከጎብኚዎች 3 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት አቀዶ ከእቀዱ አንድ ሶስተኛውን ሳያሳካ በመቅረት አንድ በሊየን ዶላር ከዕቅዶ ሳያሳካ የቀረ ሲሆን 2 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገቢ ማግኘቱን ግን አስታውቋል።
በ2013 የበጀት ዓመት የኮሮና ቫይረስ የሚያመጣው ጫና ባይታወቅም አሁንም ድረስ ስጋቱ እንዳለ ነው ነገር ግን 3 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ውስጥ ገቢ ለማግኘት ውጥን ይዘናል ሲሉ እንደገና አስታውቀዋል። ይህም በቱሪስቱ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረት እቅድ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አልሸሸገም።
ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013



