ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።
(ክፍል 2)
በሚኪያስ በቀለ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት)
1. የኢትዮጵያን ሕግ የማዘመን ታሪክ ፈር ቀዳጅ ኩነት
የኢትዮጵያን የሕግ ስርዓት በማዘመን ትልቅ አሻራ ያሳረፈ ዐቢይ ኩነት ነበር፤ የስድስት ጥራዝ ሕጎች ወደ ሃገሪቷ መግባት።
ዶ/ር አበራ ጀንበሬ “ሕግና የፍትሕ አፈጻጸም ታሪክ፡ ከ1426-1966” በሚለው ሰፋ ያለ መጽሐፋቸው ላይ እንደመዘገቡት በ1946 ዓ.ም ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ 17 ኢትዮጵያዊ እና 13 የውጭ ዜጎችን ያካተተ ጥራዝ ሕጎችን የሚያዘጋጅ ኮሚቴ ያቋቋሙ ሲሆን ኮሚቴው የሚሠበሠበው እና ሥራውን ይሠራ የነበረው በጊዜው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ዱክ ቤት በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር።
የኮሚቴ አባላቱ 30 ቢሆኑም የማርቀቁን ሥራ ግን የሠሩት አራት የሕግ ልኂቃን የሆኑ የኮሚቴው አባላት ነበሩ።
በጊዜው የተረቀቁት የሕግ ጥራዞች፤ 1) የ1952 ፍትሐ ብሔር፣ 2) የ1958 የፍትሐ ብሔር ሥነ ስርዓት፣ 3) የ1949 የወንጀለኛ መቅጫ፣ 4) የ1954 የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት፣ 5) የ1952 የንግድ፣ እና 6) የ1952 የባህር ሕጎች ነበሩ። ሕጎቹ የጸደቁት ከ1949 እስከ 1958 ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር።
በዚያ ጊዜ ከተረቀቁት ስድስት ሕግጋት አምስቱ የተለያዩ ማሻሻዎች እየተደረገላቸው እስከ ዛሬ ተፈጻሚ ሲሆኑ አንዱ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ግን በ1997 ዓ.ም በሌላ ተተክቷል።
የኢትዮጵያን የሕግ ስርዓት ታሪክ በጥልቀት ያጠኑት ዶ/ር አበራ ጀንበሬ እንደጻፉት የፍትሐ ብሔር ሕጉን ያረቀቁት የፓሪስ ዩንቨርሲቲ መምህር በነበሩ ሬኔ ዲቪድ በሚባሉ ግለሰብ ሲሆን በአብዛኛው የተገለበጠውም ከፈረንሳይ እና የስዊዝ የፍትሐ ብሔር ሕጎች ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት እና የፍትሐ ብሔር ሥነ ስርዓት ሕጎችን ያረቀቁት ደግሞ ጄኔቫ ዩንቨርሲቲን በመምህርነት፣ በስዊዝ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በዳኝነት እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የሕግ ትምህርት ክፍል ደግሞ በዲንነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ጄን ግራቨን የሚባሉ ግለሰብ ነበሩ። የንግድ ሕጉን በመጀመሪያ ያረቀቁት የፓሪስ ዩንቨርሲቲ መምህር በነበሩት ፕሮፌሰር ጄ ኤስካር ሲሆኑ ሕልፈታቸውን ተከትሎ ግን የተጠናቀቀው የፈረንሳይ ኤክስ አን ፕሬቫንስ ዩንቨርሲት መምህር በነበሩት ፕሮፌሰር ኤ. ጆፍሬ ነበር። የባህር ሕጉን ያረቀቁት ደግሞ ፕሮፌሰር ጄ. ኤስካር ነበሩ።
ዶ/ር አበራ ስለ ሕጎቹ የአወጣጥ ሒደት ሲያብራሩ ረቂቆቹ ወደ ኮሚቴው የሚላኩ ሲሆን፣ ከፈንሳይኛ ወደ አማርኛ እየተተረጎሙ ለአባላቱ ይታደሉ ነበር። አባላቱ በሕጎቹ ላይ ውይይት አድርገው፣ ለጥልቅ ውይይትም ለንዑስ ኮሚቴ ካስተላለፉ እና ሰፊ ውይይት ከተካሄደባቸው በኋላ ወደ ሚንስትሮች ምክር ቤት ይላካሉ።
የሚንስትር ምክር ቤቶቹ ስለ አራቱ ሕጎች ከኮሚቴ አባላት እና ስለ ኹለቱ የሥነ ስርዓት ሕጎች ደግሞ ከፍትሕ ሚንስቴር ማብራሪያ ከተደረገላቸው በኋላ አጠቃላይ ውይይት አካሔደውባቸው ወደ ኹለቱ ምክር ቤቶች ተልከው፣ ምክር ቤቶቹ አንቀጽ በአንቀጽ ዝርዝር ውይይት ካካሄዱባቸው በኋላ እንዲያልፉ ተደርገዋል።
2. የ1948ቱን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች እና ይዘታቸው
ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የ1928 ሕገ መንግሥት በ1948 ዓ.ም ላይ ተሻሽሏል። የ1948ቱን ሕገ መንግሥት በድጋሚ ለማሻሻል ኸለት ጥረቶች ተደርገው ነበር።
ሀ) የታኅሣሥ ግርግርን ተከትሎ የተሞከረ ማሻሻል
የመጀመሪያው ጥረት የተደረገው በተለምዶ የታኅሣሥ ግርግር በመባል በሚታወቀው እና በመንግሥቱ ነዋይ፣ በግርማሜ ነዋይ እና በወርቅነህ ገበየሁ ታቅዶ የተመራውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍ ተከትሎ ለዚሁ ምላሽ በ1953 ዓ.ም ነበር።
በዚህ ጊዜ ንጉሡ የሕገ መንግሥት ችግር የሚያጠና 7 የሀገር ውስጥ እና 2 የውጪ ዜጎች አባላት ያለው ኮሚሽን ማቋቋማቸውን ዶ/ር አበራ መዝገበዋል። ዶ/ር አበራ ጨምረውም፣ ይህ “አሻሻይ ኮሚሽን” 22 ማሻሻያዎችን ያቀረበ ቢሆንም ከአምስት ዓመታት በኋላ የጠቅላይ ሚንስትርን እና የሚንስትሮችን ሥልጣን የሚጨምር ትእዛዝ በማውጣጥ ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል ቀርቷል።
ለ) አብዩቱ የቀደመው የማሻሻል ሙከራ
ኹለተኛው የማሻሻል ሙከራ የተጀመረው በንጉሡ ላይ ያሉ ተቃውሞችን ማየላቸውን ተከትሎ፣ ከአብዮቱ ዋዜማ በ1966 ዓ.ም ላይ ነበር። ዶ/ር አበራ እንደመዘገቡት 30 አባላት ያሉት በእውቁ የታሪክ ተመራማሪ ተክለጻዲቅ መኩሪያ ሊቀመንበርነት የሚመራ ኮሚሽን በመጋቢት 1966 ዓ.ም ተቋቁሞ ሥራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በሐምሌ 1966 ዓ.ም ጨረሰ።
የቀረበው ማሻሻያ ከበፊቶቹ ሕገ መንግሥቶች የተለየ ነበር። ንጉሡ ከመንግሥት አስተዳደር ተለይተው ርእሰ ብሔር የሚሆኑበት ብቻ ሳይሆን ሥማቸው የተለወጠ እና ሰፊ ሥልጣን ያላቸውን ፓርላማዎች የሚያቋቁም ነበር። ምክር ቤቶቹ በጋር ብሔራዊ ሸንጎ የሚባል ሥያሜ ሲሰጣቸው በተናጠል የሕዝብ ሸንጎ (በፊት የሕዝብ መመሪያ የነበረው) እና የመማክርት ጉባኤ (በፊት የሕዝብ መወሠኛ የነበረው) ይባላሉ። ምክር ቤቶቹ በጋራ ሕግ የማውጣጥ፣ ጠቅላይ ሚንስትር የመምረጥ እና የመሻር ሥልጣኑ ሲኖራቸው፣ አባላቱም የሚመረጡት በቀጥታ የሕዝብ ምርጫ ነበር።
ይህ ሕገ መንግሥት ጸድቆ አዲስ መንግሥት በሕዝብ ምርጫ እስከሚቋቋም ኢትዮጵያ የምትተዳደርበት መመሪያ ከኮሚሽኑ የቀረበ ሲሆን ይህ ሳይፈጸም አብዮቱ ቀደመ። የዓመታት የንጉሣዊ አስተዳደርም በኢትዮጵያ አከተመ። ንጉሠ ነገሥቱም ከመንበራቸው በወታደራዊ መፈንቀለ መንግሥት ተነሱ።
3. ድህረ ኃይለ ሥላሴ – ከወታደራዊ ኮሜቴ ሕግ አውጪነት እስከ ብሔራው ሸንጎ
የመሬት ስሪትን እና የንጉሣዊ አስተዳደር መዋቅርን የሚቃወሙ ሰፊ የተማሪዎች ንቅናቄ እንዲሁም የሠራተኛና ወታደራዊ አመጾች ለዓመታት የዘለቀውን የንጉሥ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር አዳከሙት። ይህንንም ተከትሎ የ44 ዓመታቱ የንጉሡ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አከተመ።
የስርዓቱን መፍረስ ተከትሎ መንግሥታዊ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው በታችኛው ወታደራዊ ዘርፍ የሚገኙ መኮንኖች ስብስብ የሆነ “ደርግ” የተሰኘ ኮሚቴ ነበር።
ደርግ ሀገሪቷን ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በሚል ለ13 ዓመታት ያለ ሕገ መንግሥት አስተዳድሯታል። ደርግ በአዋጅ (1/67) እራሱን ጊዜያዊ አስተዳደር በማድረግ መሥርቶ፣ የ1948 ሕገ መንግሥት ተፈጻሚነት ብሎም ኹለቱን ምክር ቤቶች “ሕዝቡ የራሱን እንደራሴ እስከሚመርጥ ድረስ” አግዷቸዋል።
ሀ) የደርጉ ዘመን ሕግ አውጣጥ
ደርጉ የአስተዳደር ኮሚቴውን ሥልጣን እና ኃላፊነት ለመዘርዝር ሌላ አዋጅ (2/67) በማወጣጥ ከሥልጣኖቹ መካከል አንዱ ማናቸውንም ዓይነት ሕጎች የማውጣጥ እና የማስፈጸም እንዲሆን በመወሰን፤ የሕግ አውጪውንም አስፈጻሚውንም ሥልጣን ቀላቅሎ እና ጠቅልሎ ይዞ ሃገሪቷን የሚያስተዳደርበት መዋቅር ዘርግቶ ነበር።
የደርግ ሥልጣን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 2/67 ከኹለት ዓመታት በኋላ መዋቅር በመቀየር የደርግ አባላት ያካተተ ኮንግረስ፣ በኮንግረሱ የሚመረጡ 40 አባላትን ያካተተ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና 17 አባላትን ያካተተ ቋሚ ኮሚቴ የሚባሉ አደረጃጀቶችን በመመስረት በሌላ አዋጅ (108/67) ተሻሽሎአል። በዚህም የደርጉን አባላት ያካተተው ኮንግረስ የሕግ ማውጣጥ ሥልጣኑን ይዞ ቆይቷል።
አዋጅ – 108/67 በድጋሚ የኮንግረሱን ኹለተኛ ምክትል ሊቀመንበር ቦታ በሰረዘ አዋጅ (110/69) እንዲሻሻል ተደርጓል። በዚህ አዋጅም የሕግ ማውጣጥ ሥልጣኑ የኮንግረሱ ነበር። ይህ አዋጅ ለማውጣጥ ምክንያት የሆነው መንግሥቱ ኃይለማርያም የውስጥ ተቀናቃኛቸውን እና ወደ ፊት ሊቀመንበር ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ሲነገርላቸው የነበሩትን ብርጋዴል ጄነራል ተፈሪ በንቲን ካስገደሉ በኋላ ሥልጣኑን በሙሉ ለመቆጣጠር በነበራቸው ዓላማ መሆኑን ዶ/ር አበራ ጀምበሬ እና ወልደሚካኤል ወልደትንሳኤ ከ1966-2001 ስላለው የኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ በእንግሊዝኛ በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ አስፈረዋል።
ደርግ ለ13 ዓመታት ሀገሪቷን ያስተዳደራት ያለ ፓርላማ፣ በሕግ አውጪ እና በአስፈጻሚ ሥራዎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያደርግ ነበር።
ለ) የኢሕዴሪ ሕገ መንግሥት አወጣጥ
ደርግ ከ12 ዓመታት በኋላ ወታደርያዊውን ስርዓት ወደ ሲቪል አስተዳደር (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ መንግሥት/የኢሕዴሪ መንግሥት) ለመቀየር ያለመ ሕገ መንግሥት የማውጣጥ ክንውን ጀመረ።
የሕገ መንግሥቱ ጥንስስ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ፓርቲ (ኢሠፓ) ለማቋቋም በአዋጅ (174/77) በተመሠረተ ኮሚሽን ኹለተኛ ጉባኤ ላይ ነበር። በዚህ በኹለተኛው ጉባኤ የተያዘው ቃለ ጉባኤም ሆነ አዲስ የተመሠረተው የሠራተኛ ፓርቲ ፕሮግራም የሕገ መንግሥቱን ዋነኛ ምሰሶዎች ያካተተ እንደነበር ዶ/ር አበራ እና አቶ ወልደሚካኤል ታዝበዋል።
ሕገ መንግሥቱ እንዲረቀቅ የሠራተኛ ፓርቲን ለማደራጀት የተመሠረተው ኮሚሽን “የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ተቋም” የሚባል ተቋም የመሠረተ ሲሆን ኃላፊነቱም የሀገሪቷን ማኅበራዊ ሁኔታ፣ አስተዳደርያዊ መዋቅር ብሎም አማራጭ ሶሻሊስታዊ ሕገ መንግሥቶችን ማጥናት እና ሕገ መንግሥቱን ማርቀቅ ነበር። በዚህ ተቋም የተዘጋጀው ሕገ መንግሥት “ንድፍ” እንደሚሰኝ ዶ/ር አበራ እና አቶ ወልደሚካኤል ይገልጻሉ።
ሕገ መንግሥቱን ለማርቀቅ የአዲሱ የሠራተኛ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ 354 አባላት ያሉት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን (የሕዝባዊ ድርጅት፣ የሠራተኛ ማኅበር፣ እና ሃይማኖታዊ ተቋማት ተወካዮችን እና ባለሙያዎች የተካተቱበት) በአዋጅ – 291/78 ያቋቋመ ሲሆን ከብሔረሰቦች ጥናት ተቋም ወደ አርቃቂ ኮሚሽኑ የሚላከው “ንድፍ” መሻሻሎች ተደርጎበት “ረቂቅ” እንደሚሆን እና ለሠራተኛ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ይቀርብ እንደነበር ዶ/ር አበራ እና አቶ ወልደሚካኤል ጽፈዋል።
የኢትዮጵያን የሕገ መንግሥት ታሪክ ያጠኑት ዶ/ር ቃልአብ ታደሰ እንደመዘገቡት ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ከቀረበ በኋላ ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎዎች ተሰናድተው ነበር። የሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ለውይይት በሚል ወደ 15 የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች መተርጎሙን እና ወደ 25 ሺሕ የውይይት መድረኮች መዘጋጀታቸውንም የተለያዩ ሰነዶችን ከማገላበጥ ያገኙትን መረጃ ዋቢ በማድረግ ዶ/ር ቃልአብ ጽፈዋል። ነገር ግን እንደ ዶ/ር ቃልአብ ምርመር በሕዝባዊ ውይይቶቹ የነበረውን ሒደት ብሎም የተሰበሰቡ ግብዓቶች ጥቅም ላይ ስለማዋላቸው የተለያዩ ታዛቢዎችን ትችት አስተናግጓል።
ሕዝባዊ ወይይቶቹን ተከትሎ ሕገ መንግሥቱ ለሕዝበ ወሳኔ ቀርቦ 81 በመቶ እሺታ እንዳገኘ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መዝግቦታል።
የኢሠፓ ፓርቲ በተመሰረተ በ3 ዓመቱ በ1979 ዓ.ም ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሕገ መንግሥት በሚል ተፈጻሚነቱ ታወጀ።
ሐ) የኢሕድሪ ሕገ መንግሥት የመሠረተው ፓርላማ እና ሕግ አወጣጥ
የኢሕድሪ ሕገ መንግሥት በሠራተኛ ፓርቲ፣ ሕዝባዊ ድርጅቶች፣ ወታደርያዊ ክፍሎች እና ሌሎች በሕግ ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት የሚታጩ እና በሕዝብ የሚመረጡ እስከ 835 አባላት የሚኖሩት “ብሔራዊ ሸንጎ” የተሰኘ ምክር ቤት አቋቁሟል።
የብሔራዊ ሽንጎ አባላት የመጀመሪያ ምርጫ በ1979 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን ከ2 ሺሕ 466 እጩዎች፣ 818 ተመራጮች “ደካማ በሆነና እና ገለልተኛ ባልሆነ ምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት እና ታዛቢነት” እንደተመረጡ ዶ/ር ምህረት አየነው ስለ ኢትዮጵያ ፓርላማ እና ሕዝብ ቁርኝት ባጠኑበት ጽሁፍ ላይ አስፍረዋል። አባላቱ የ5 ዓመታት የሥራ ዘመን ሲኖራቸው ተጠያቂነታቸውም “ለሠርቶ አደሩ ሕዝብ” መሆኑን ሕገ መንግሥቱ ያስቀምጣል።
ሕገ መንግሥቱ ሕግ የማመንጨት እና ወደ ብሔራዊ ሸንጎ የማቅረብ ሥልጣኑን ለመንግሥት ካውንስል፣ ለፕሬዝዳንቱ፣ ለሚስትሮችን ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ለዐቃቤ ሕግ፣ ለሸንጎው ከፍተኛ አስተዳደሮች፣ ራስ ገዝ አውራጃዎች እና ሕዝባዊ ማኅበራት ሰጥቷል።
የብሔራዊ ሸንጎ አባላት ሌላ የሙሉ ሰዓት ሥራ ሊኖራቸው የሚችል ሲሆን መደበኛ ስብሰባቸውን የሚያደርጉት በዓመት አንዴ ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት ምክር ቤቱ በማይሰበሰብበት ጊዜ ሕግ ማውጣትን እና የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ማጽደቅን ጨምሮ፤ የሸንጎ ሥራ የሚሠራው በፕሬዝንዳንቱ በሚመራ “የብሔራዊ ሸንጎ ቋሚ አካል” ነበር። በዚህም ምክንያት ሕግ የማውጣጥ ሥራ ከምክር ቤቱ ይልቅ በአስፈጻሚ የሚከወን ተግባር ነበር።
ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013



