የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አወጣጥ አሳታፊነት – ክፍል 1

0
1081

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አወጣጥ አሳታፊነት – ክፍል 1
በሚኪያስ በቀለ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት)
1) በሕገ መንግሥት ማውጣጥ ውስጥ የሚኖር ተሳትፎ አስፈላጊት እና ሒደት
የአንድ ሀገር ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው። ሕዝብ ይህንን ሉዓላዊ ሥልጣኑን በዋነኛነት የሚተገብረው መንግሥት በሚባል እና በሚወክለው ተቋም አማካኝነት ነው። ይህ መንግሥት የሚባል ተቋም በሕዝብ በውክልና የተሰጠውን ኃላፊነት የሚተገብረው ደግሞ በሕገ መንግሥት ውስጥ በተሠፈረለት ልክ ነው። ስለዚህ ሕዝብ የሉዓላዊነት ሥልጣኑን እንዴት በውክልና እንደሚሰጥ፣ እና ሥልጣኑንም እንዴት እንደሚተገበር መወሰን እና መቅረጽ መቻል አለበት።
ሕዝብ በሚመሰረተው የመንግሥት አወቃቀርም ሆነ ሊኖር ስለሚሻበት ማኅበረሰብ ሐሳቡን ካልሰጠ ስለ ሕዝብ ሉዓላዊነት ማውራቱ ዋጋ እንደሌለው አሎክ ፓካርል የተባሉ ጸሐፊን በመጥቀስ አቶ ተጓዳ አለባቸው የተባሉ የሕገ መንግሥት ተማሪ በኹለተኛ ዲግሪ ሟሟያቸው ላይ ያስረዳሉ።

አሳታፊ ሕገ መንግሥት የማውጣት ሒደት፤ የሰነዱን ቅቡልነት እና ውጤታማ ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ተገቢውን የማኅብረሰብ ፍላጎትም ግምት ውስጥ ለመክተት ያስችላል።

እንዲሁም እውቅና ከተቸረው ዋነኛ የዴሞክራሲ ሞሰሶ ብሎም “የዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ” የሰብኣዊ መብትም ማረጋገጥ ነው።
በሕገ መንግሥት ውሰጥ የሚኖር ተሳትፎ አንድም በሒደቱ ውስጥ በሚሳተፉ ኀይሎች እና ተቋማት ወኪልነት ሌላም ማኅበረሰቡ በቀጥታ በሚያደርጋቸው ተሳትፎዎች ይገለጻል።

አዲስ ሕገ መንግሥት የሚወጣው መሰረታዊ የሆነ ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ፣ አዲስ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ስርዓት ለመዘርጋት ነው። በዚህም ምክንያት አዲስ ሕገ መንግሥት የማውጣትም ሆነ የነበረውን የማሻሻል ሥራዎች ከሌሎች ሕጎች በተለየ፣ ጠልቅ እና ዘለግ ያለ ሒደት ይኖረዋል።
ሕገ መንግሥት የማውጣጥ አካሔድ በአራት ሒደቶች ተለይቶ ሊቀመጥ ይችላል። እነሱም ማርቀቅ (drafting)፣ ውይይት (deliberation)፣ ማውጣት (adoption) እና ማጽደቅ (ratification) ናቸው።

የፖለቲካ ለውጥን ተከትሎ በሕገ መንግሥት ላይ ድርድር የሚያደረግ ሁሉን ያሳተፈ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ዋነኛው ቅድመ ሁኔታ ነው። የሽግግር መንግሥት የመመስረት ሐሳብ ብሎም ተግባር ከአንድ የፖለቲካ ኀይል የመነጨ ቢሆንም ሁሉን ማሳተፍ እና እኩል የድርድር አቅም መሰጠት ይኖርበታል። በየአቅጣጫው ያሉ የማኅበረሰብ ተወካዮች የወደፊት ሀገራዊ እጣ ፈንታ ላይ ብቻ ሳይሆን እጣ ፈንታው በሚወሰንበት አካሄድም ላይ ሊሳተፉ ያሻል።

2. የለንደን ውይይት – የአሸናፊዎች ድርድር
የኢፌድሪ ሕገ መንግሥትን የማርቀቅ ሒደት ለመገንዘብ አጀማመሩን እና በሒደቱ ውስጥ የተሳተፉ ተቋማት እና የፖለቲካ ኀይሎች መመልከት ያስፈልጋል። ሒደቱ የኢሕድሪ መንግሥት መሽመድመድ፣ በሀገረቷ አስተዳደር እና ግዛት ላይ ያለውን ቁጥጥር ማጣጥ ይጀምራል። ይህን የተገነዘቡት የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕውሓት) የመሠረተው የኢትዮ ጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር አሜሪካን ባዘጋጀችው የለንደን ጉባኤ ላይ ግንቦት 19፣ 1983 ዓ.ም ተገናኙ። ኦነግ በውይይቱ ላይ ከታዛቢ የዘለለ ተሳታፊነት እንዳልነበረው የጊዜው ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በኢሜል ማሳወቃቸውን እራሳቸው ዶ/ር ነጋሶ በቃል እንደገሯቸው አቶ ተጓዳ አለባቸው ጽፈዋል።

በአሜሪካ በኩል ሲያደራድሩ የነበሩት በጊዜው በአፍሪካ ጉዳይ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ የነበሩት ኸርማን ኮህን የተሻለ ሥነ ስርዓት (discipline) የነበራቸው የኢሕአዴግ ሠራዊት ስለነበር፣ በሀገሪቷ ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ እኢሕአዴግ ማዕከላዊ መንግሥቱን መቆጣጠር እንዳለበት የአሜሪካን አቋም መሆኑን በጊዜው መግለጻቸው ተመዝግቧል።

ኢሕአዴግ ማዕከላዊ መንግሥቱን ከተቆጣጠረ በኋላ “የሰላም እና ዲሞክራሲ ጉባኤ” ከግንቦት 24 እስከ 28/1983 ዓ.ም እንዲዘጋጅ ቀጠሮ የተያዘው በዚሁ የለንደን ጉባኤ ነበር። ጉባኤው ከቀጠሮ ሌላም የሽግግር ቻርተር እንዲወጣ እና የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ከመወሰኑ ባሻገር የኤርትራም የነጻነት ጥያቄ እውቅና ተሰጥቶታል።

3. የአዲስ አበባው የሰላምና ዴሞክራሲ ጉባኤ – ያለቀለት ቻርተር ማጽደቅ እና የሽግግር ምክር ቤት ማቋቋም
ኢሕአዴግ ማዕከላዊ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት “የሰላም እና ዲሞክራሲ ኮንፈረስ” ተካሄደ። ተሳታፊቹ በአብዛኛው በብሔር የተደራጁ ኀይሎች ነበሩ። በፊት የነበሩ የሽምቅ ተዋጊዎች እና ከውጪ የገቡ የፖለቲካ ኀይሎች ቢኖሩም የኢሕአዴግ’ን ጥሪ ተከትሎ በአንድ ሌሊት የተፈለፈሉ የፖለቲካ ኀይሎችም እንደነበሩ አቶ ተጓዳ አለባቸው ጽፈዋል። ሕብረ ብሔራዊ፣ ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍል እወክላለሁ የሚል ድርጅት አልነበረም። የአማራን የማኅበረሰብ ክፍልን እወክላለሁ የሚል ድርጅት አለመምጣቱንም ከጉባኤው በኋላ በነበረ የፓናል ውይይት ላይ የጉባኤው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ (በኹለተኛው የጉባኤ ስብሰባ የተመረጡ) ገልጸዋል።

የተሳተፉት የፖለቲካ ኀይሎች 27 ሲሆኑ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እና ሠርቶ አደር ሕዝቡ የተወከሉ ነበሩ። 22 የውጪ መንግሥታት እና የዓለም ዐቀፍ ተቋማት ተወካዮች እንደታዛቢ ተሳታፊዎች ሆነው ነበር።

ጉባኤው አሳታፊ አለመሆኑ ለብዙዎች ግልጽ ነበር። በጉባኤው ላይ የነበረው ውክልና “የአመለካከት እንጂ የሕዝብ” እንዳልሆነ የጉባኤው ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተስተውሏል። ነገር ግን ይህ ከእውነት የራቀ ነበር።

ከብሔር እና ሃይማኖታዊ ማንነቶች በዘለለ የሕብረ ብሔራዊ አመለካከት የነበራቸው ድርጅቶች ውክልና አልነበራቸውም። በደርግ ጊዜ በሰፊው ሲንቀሳሰቀሱ የነበሩ እና ጠላት ሆነው የቆዩትን ሕብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች – የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ጨምሮ የኢትዮጵያዊያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዲፓ)፣ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ያካተተ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኀይሎች ጥምረት በጉባኤው፣ በኋላም በሚመሰረተው የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት ላይ እንዳይሳትፉ ሆነው ነበር። ለዚህ ምክንያት ብዙዎች የድርጅቶቹን ሕብረ ብሔራዊ ቅርጽ እና ከነበራቸው የረዥም ጊዜ ልምድ እና ተቀባይነት አንጻር ለኢሕአዴግ ተቀናቃኝ ሆነው ሊወጡ መቻላቸው እንደነበር ይገለጻል። ከጉባኤው በኋላ በነበረ የፓናል ውይይት ላይ የጉባኤው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ይሄ ውህድ ላለመሳተፉ እንደምክንያት ያስቀመጡት እንደ ጦርነት አዋጅ የሚቆጥሩትን የደርግ የመጨረሻ ጉባኤ መቀበላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ውህዱ እንኳን ጦርነት የማወጅ ወደ ውጊያ ለመግባት የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልነበር የብዙዎች ትዝብት ነበር።

የጉባኤው ሊቀመንበር አቶ መለስ የሚመሰረተውን የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት መቀመጫዎች ባደላደሉበት የመጨረሻ ቀን ስብሰባ ላይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ፓርቲ (ኢሠፓ) “ወንጀለኛ ድርጅት” ስለሆነ በጉባኤውም ሆነ በሚቋቋመው የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት እንዳይሳተፍ እግድ ተጥሎበታል። የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር በጉባኤው እንደ ታዛቢ ተሳትፎ አድርጎአል።

የሰላም እና ዴሞክራሲ ጉባኤ ዋነኛ ውጤቶች የሽግግር ጊዜ ቻርተር እና ባለ 87 አባላት የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት ነበሩ። ቻርተሩ የጉባኤው ውጤት ሳይሆን መጀመሪያ በኢሕአዴግ፣ ኦነግ እና የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር የተወሰነ መሆኑን ብዙዎች በትክክል ይናገራሉ። ብዙዎች እንደሚገልጹት፤ ዶ/ር ቃልአብ ታደሰ አቶ ገብሩ አሥራትን በቃል በማነጋገር ብሎም “ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” የሚለውን መጽሐፋቸውን በመመርመር እንደገለጹት የሽግግር ጊዜ ቻርተሩ ቀደም ብሎ በኤርትራ ሰንኣፌ በሚባል ቦታ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ እና አቶ ሌንጮ ለታ ተስማምተው የተፈራረሙበት ሰነድ ነው።

ቻርቱሩን ለጉባኤው ያቀረበው ኢሕአዴግ ነበር። ቻርተሩ በቀረበበት በኹለተኛ ቀን የጉባኤው ስብሰባ ላይ ተሳታፊዎቹ ቻርተሩ የደረሳቸው እዛው በስብሰባው ላይ ስለነበር ከማድመጥ በዘለለ፣ ተዘጋጅተው ሐሳባቸውን እንዲሰጡ አልቻሉም ነበር። “ጊዜ ወስደን መወያየት ያስፈልጋል” በሚል የተነሱ ሐሳቦች የጥቂት አባላት ሐሳብ ነው በሚል እንዲጣሉ እና ቀጥታ ወደ ውይይት እንዲገባ ተደርጓል።

ስለዚህ ቻርተሩ በተለያዩ ኀይሎች ውይይት እና የጋራ ሰምምነት የመጣ ሳይሆን ቀድመው በብሔር-ተኮር እና የመገንጠል ጥያቄ ላይ ተመስርተው የተዋጉ ሽምቅ ተዋጊዎች፣ “የአሸናፊዎች የጋራ ስምምነት” መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። ከግንቦት 24 እስከ 28፣ 1983 ዓ.ም የተደረገው ጉባኤ ባለቀለት ጉዳይ ላይ እውቅና የተሰጠበት ለመሆኑ ብዙ አመላካች ኩነቶች አሉ።

4. የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት – የተለያዩ ፖለቲካ ኀይሎች ማፈግፈግ
የሽግግር ቻርተሩ ለሕገ መንግሥቱ ዋነኛ ምንጭ ነበር – አንድም ይዘቱ በሕገ መንግሥቱ ላይ ከነበረው ተጽዕኖ፣ ሌላም ለሽግግር ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱን ከማርቀቅ እና ከማውጣጥ ጋር በተያያዘ የሰጠው ሥልጣን።

የሽግግር ጊዜ ምክር ቤቱ አንዱ እና ዋነኛው ኀላፊነት ሕገ መንግሥት የሚያረቅ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ማቋቋም ነበር። በሽግግር ጊዜ ምክር ቤቱ የወጣው እና የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን የተመሠረተበት አዋጅ (24/84)፤ ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥቱን “ከቻርተሩ መንፈስ ጋር ባልተቃረነ ሁኔታ” እንዲያረቅቅ ኀላፊነት ጥሎበታል። ይሄም ሕገ መንግሥቱ ቻርተሩን ካወጡት ኀይሎች ፍላጎት እንዳያፈነግጥ፣ እና ይዘቱም ቀድሞ የተወሰነ እንደነበር ያሳያል።

የሽግግር ቻርተሩ የመሠረተው የሽግግር መንግሥት አወቃቀር እና ለሽግግሩ ያስቀመጣቸው ዋነኛ ምሰሶዎች – ፓርላሜንታዊ የመንግሥት አወቃቀር (ክፍል 3) እና፣ እስከ መገንጠል የሚደርስ የብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች እራስን በራስ የማስተዳደር የቡድን መብት ብሎም “የብሔር አሰፋፈሮችን” መሰረት ያደረገ የፌደራላዊ አስተዳደራዊ ክልሎች (አንቀጽ 2 እና 13) በኋላ ላይ በጸደቀው ሕገ መንግሥት፣ ብሎም በመሰረተው የኢፌድሪ መንግሥትም ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል። የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ኮሚሽን አባል እና ሕገ መንግሥቱን ያወጣው/ያጸደቀው የሕገ መንግሥት ጉባኤ ሰብሳቢ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የሽግግር ቻርተሩ የሕገ መንግሥቱ ዋነኛ መሠረት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

የተቋቋመው የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ተጠያቂነት ለሽግግር ምክር ቤቱ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ በኮሚሽኑ የሚቀርብለትን ረቂቅ ሕገ መንግሥት የማጽደቅ (adopt የማድረግ) ሥልጣኑ ነበረው።

የሽግግር ምክር ቤቱ ከመጀመሪያ በኢሕአዴግ ተጽዕኖ ሥር መሆኑ ግልጽ ነበር። የሽግግር ምክር ቤቱን መቀመጫ ያደላደሉት የኢሕአዴግ እንዲሁም የሰላምና ዴሞክራሲ ጉባኤው ሊቀመንበር ብሎም የጊዜያዊ መንግሥቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ። ከነበሩት 87 ወንበሮች አብላጫውን ያየዙት ኢሕአዴግ (32 ወንበር) እና ኦነግ (12 ወንበር) ነበሩ። ሊቀ መንበሩ ድልድሉን ባደረጉበት ጊዜ “የተለያዩ አመለካከቶች ይወከላሉ” ከሚል በዘለለ በምን መስፈርት መቀመጫዎቹ እንደተደለደሉ እዚህ ግባ የሚባል ማብራሪያ አልሰጡም። ወደ ፊት ሊመጡ ለሚችሉ እና ላልተወከሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሚል 6 ወንበሮች ያለ ተወካይ ባዶ ሆነው የቆዩ ሲሆን የተያዙት ወንበሮች 81ዱ ብቻ ነበሩ።

ያም ሆኖ ምክር ቤቱ እንደአጀማመሩ አልቀጠለም። በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሰሚነት የነበራቸው ድርጅቶች ከምክር ቤቱ እና ከሽግግር አስተዳደሩ በመውጣጥ ሕገ መንግሥቱን ከማርቀቅ እራሳቸውን አግልለዋል። በተለይም ኦነግ እራሳቸውን ካገለሉ ኀይሎች ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው ነበር። የተለያዩ የፖለቲካ ኀይሎች እና ልኂቃን ከሽግግር ምክር ቤቱ ለመውጣታቸው የነበራቸው ምክንያት ያደረባቸው የመገለል ስሜት ብቻ ሳይሆን ምክር ቤቱና የሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሒደቱ በኢሕአዲግ ተጽዕኖ ውስጥ መውደቁ ነበር። ያለምንም ተጽዕኖ በምክር ቤቱ ውስጥ በመቆየት ለሒደቱ እውቅና ላለመስጠጥ ለቀው ወጥተዋል።

ምክር ቤቱ ከተቋቋመ በኋላ በተለያዩ ጊዜዎች የሒደቱ ተሳታፊ የነበሩ የፖለቲካ ኀይሎች ጥሎ መውጣጥ አንዱ የሒደቱን አሳታፊነት አጠያያቂ ካደረጉት ኩነቶች ውስጥ ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here