ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።
በሚኪያስ በቀለ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት)
1. የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን – ከባለሙያ ይልቅ የፓርቲ ተጽዕኖ
የሽግግር ምክር ቤቱ አንዱና ዋነኛው ሥልጣን የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ማቋቋም ነበር። በምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱ በባለሙያዎች እንዲረቀቅ የቀረበው ጥያቄ የተሻለ መቀመጫ እና ተጽዕኖ በነበረው ኢሕአዴግ “ሰነዱ የፖለቲካ እንጂ የሕግ ሰነድ አይደለም” በሚል ተቃውሞ እንደገጠመው አቶ ተጓዳ አለባቸው በኹለተኛ ዲግሪ ሟሟያቸው ላይ ጽፈዋል።
ምክር ቤቱ የአርቃቂ ኮሚሽኑን ለመመስረት እና ኃላፊነቱን ለመወሰን አዋጅ – 24/83 አውጥቷል። አዋጁ የአርቃቂ ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥቱን “ከሽግግር ቻርተሩ መንፈስ ጋር ባልተቃረነ ሁኔታ” እንዲያረቅ ኃላፊነት ጥሎበታል። በምክር ቤቱም ግልጽ እና ቀጥተኛ አቅጣጫ ይሰጠው ነበር። ኮሚሽኑ ከኹለት ዓመት ከመንፈቅ ባልዘለለ ጊዜ ውስጥ ሥራውን ማጠናቀቅ ነበረበት።
የአርቃቂ ኮሚሽኑ በመጀመሪያ 27 ከዚያም ኹለት ከመምህራን ማኅበር ተጨምረውበት 29 አባላት ነበሩት። አባላቱ 7 በምክር ቤቱ ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ኀይሎች፣ 7 ከምክር ቤቱ ወጪ ከነበሩ የፖለቲካ ኀይሎች፣ 3 ከሠራተኛ ማኅበራት፣ 3 ከንግድ ምክር ቤት፣ 2 ከሕግ ባለሙያዎች ማኅበር፣ 2 ከመምህራን ማኅበር፣ 2 ከጤና ባለሙያዎች ማኅበር እና 3 የሴት ተወካዮች ነበሩ። ኮሚሽኑ የሰብኣዊ መብት፣ የመንግሥት መዋቅር እና ሌላ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ሦስት ኮሚቴዎች በሥር አዋቅሮ ነበር። ከሽግግር ምክር ቤቱ ቀድመው የወጡ የፖለቲካ ኀይሎች በአርቃቂ ኮሚሽኑ ውስጥ አልተወከሉም።
ከሽግግር ምክር ቤቱ ውጪ ያሉ የፖለቲካ ኀይሎችን (በመገናኛ ብዙኀን ጥሪ) እና ማኅበራትን ለማካተተ የተደረገው የኮሚሽኑን አሳታፊነት ለማረጋገጥ መሆኑን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ ክፍሌ ወዳጆ መግለጻቸውን አቶ ተጓዳ ጽፈዋል። ሞአ አንበሳ እና የኢትዮጲያ አንድነት ፓርቲ የተባሉ ድርጅቶች ምክንያቱ በግልጽ በማይታወቅ ሁኔታ ኮሚሽኑን ለቀው ወጥተዋል። አቶ ክፍሌ ወዳጆ አክለው አባላቱ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ስር በነበረው የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት ተመርጠው በመካተታቸው የኢሕአዴግ አመለካከቶች ይንጸባረቁበት እንደነበር መግለጻውን አቶ ተጓዳ ጽፈዋል።
የተለያዩ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች በኮሚሽኑ ውስጥ ኖረው የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦች ቢነሱም፣ በጋራ ስምምነት (consensus) ያልተወሰኑ እና ውሳኔ በምርጫ በሚሰጥበት ጊዜ ግን የኢሕአዴግ ፍላጎት በግልጽ ይንጸባረቅ እንደነበር ኮሚሽኑን ከሚያማክሩ የሙያ ኮሚቴዎች ውስጥ የነበሩት የቀድሞ የሴቶች መብት አቀንቃኝና የዛሬዋ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ያስታውሳሉ።
2. በሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን የተሞከሩ ሕዝባዊ ውይይቶች – ባለቀላቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት
ኮሚሽኑ የሕዝብ አስተያየቶችን ለመሰብሰብ ኹለት አካሄዶችን ተከትሎ ነበር – የተለያዩ ቡድኖችን ያሳተፉ ጉባኤዎች ማዘጋጀት እና ሕገ መንግሥታዊ አማራጮች የያዘ ሰነድ አዘጋጅቶ በየቀበሌው ሐሳብ ማሰብሰብ።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ተቋማት ተወካዮች፣ የሴቶች ተወካዮች፣ ጋዜጠኞች፣ የሲቪክ ተቋማት እና የባለሙያ ማኅበራት ያሳተፉ ጉባኤዎች ተሰናድተው ነበር።
ሌላው በየቀበሌው የተዘጋጁ ሕዝባዊ ውይይቶች ነበሩ። የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽኑ 23 ሺሕ 320 የቀበሌ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀቱን ሒደቱን መርምረው ዶ/ር ቃልአብ ታደሰ ጽፈዋል። የውይይት ሰነዱ አጠቃላይ የሕገ መንግሥት ቅርጾችና መርሆዎች ላይ ለማወያየት ከመዘጋጀት ይልቅ የኢሕአዴግ አካሄድና አቋም የተካተተበት መሆኑን፥ ሰነዱን በቅርብ የመረመሩ ይገላጻሉ። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መጠይቅ ተዘጋጅቶ በማኅበረሰቡ እንዲሞላ ተደርጓል።
ውይይቶቹ አነስተኛ ተሳታፊዎች ነበሯቸው። በሕገ መንግሥት አጽዳቂው የሕገ መንግሥት ጉባኤ ውስጥ በግላቸው አባል የነበሩት ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ ሒደቱ አሳታፊ አለመሆኑን የገለጹ ሲሆን እንደምሳሌም 17 ሺሕ ነዋሪዎች ባሉበት ቀበሌ 19 ሰዎች፣ 5 ሺሕ ነዋሪዎች ባሉበት ደግሞ 32 ተሳታፊዎች ብቻ መምጣቻውን ገልጸዋል። ሻለቃ አድማሴ ጨምረውም ለውይይት የመጡት እራሱ በፍቃዳቸው ሳይሆን በፖሊስ ተቋም ውስጥ ለመካተት የተገባላቸው ቃል ተከትሎ መሆኑን በጉባኤው የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የተያዘውን ቃለ ጉባኤ በማጣቀስ ዶ/ር ቃልአብ ታደሰ ጽፈዋል።
ለውይይቶቹ የተሰጠው ጊዜ አጭር መሆኑ ብሎም ማኅበረሰቡ ለውይይት በቀረቡ ጉዳዮች ላይ የነበረው ግንዛቤም ሒደቱን አጠያያቂ ካደረጉት ኩነቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ። የሕገ መንግሥቱ ጉባኤ አባል የነበሩት አቶ ዳንኤል በላይነህ ተሳታፊዎቹ ካላቸው ግንዛቤ እና ውይይት ከተካሄደባቸው አንቀጾች ስፋት አንጻር የአንድ ቀን ውይይት በቂ ጊዜ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ይሄም ቢሆን የአርቃቂ ኮሚሽኑ 13 ሚሊዮን ተሳታፊዎች እንደነበሩ በቃለ ጉባኤ ተመዝግቦ መያዙን አቶ ተጓዳ ስለ ሕገ መንግሥት ቅቡልነት በጻፉት የኹለተኛ ዲግሬ ሟሟያ ጽሁፋቸው ላይ አስፍረዋል።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለረዥም ዓመታት የተከታተሉ ጆን ማርካኪስ የተባሉ አጥኚ “ሕገ መንግሥታዊነት እና ፌደራሊዝም በአፍሪካ ቀንድ” በሚል ጽሁፋቸው መንግሥት አጀንዳዎቹን እራሱ እንዳስቀመጣቸው እና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ በቂ የውይይት ጊዜ እንዳልነበር ይገልጻሉ። እንደ ማርካኪስ ትዝብት የመሬት ስሪት እና የብሔር ተኮር የፌደራል አወቃቀርን የመሳሰሉ የሕገ መንግሥቱ ምሰሶች ላይ በገጠሩ ክፍል ያለው ማኅበረሰብ ቀድሞ ለውይይት የሚያበቃ ግንዛቤ ካለመያዙ ባሻገር፣ ቀድመው የተወሰኑ እና ለድርድር የሚቀርቡ አልነበሩም።
ሕዝባዊ ውይይቶች ከመካሄዳቸው በፊት ስለ ሕገ መንግሥት አንኳር መርሆዎች እና የአወጣጥ ሒደቶች በተለያዩ አካሄዶች የሲቪክ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባ፣ ይህም ማኅበረሰቡ የእውነት በሒደቱ አካል እሆናለሁ፣ ተጽዕኖም እፈጥራለው በሚል መተማመን ሊሳተፍ እንደሚያስችለው በሕገ መንግሥት ቅቡልነት ላይ የኹለተኛ ዲግሪ ሟሟያቸውን የጻፉት አቶ ተጓዳ አለባቸው ይገልጻሉ። ነገር ግን በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ ማኅበረሰቡን ለማሳወቅ የተደረገ ተነሳሽነት አልተስተዋለም።
የገዥው ፓርቲ አባላት እና ደጋፊ ከሆኑ ውጪ የመሳተፍ መብት አለማግኘታቸውንም ማርካኪስ ይገልጻሉ። እንደ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽኑ አባል እና የአጽዳቂ ጉባኤው ሰብሳቢ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አገላለጽ የውይይቶቹ ተሳታፊዎች የተመረጡ እና ከየቀበሌው በነበሩ አመራሮች ተጽዕኖ ሥር ስለነበሩ አማራጭ ሐሳቦች መደመጥ ካለመቻላቸው ባሻገር ተሳታፊዎች በጣም ትንሽ ነበሩ።
ዶ/ር ነጋሶ አክለውም ተቃዋሚዎች በራሳቸው አደራጅተው ውይይት እንዲያደርጉ አለመፈቀዱ ታላቅ ስህተት እንደበር እና ወደ ኋላ ሲመለከቱ እራሳቸውን የሚወቅሱበት ነገር መሆኑን ከኅልፈታቸው ቀደም ብለው ከአንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
የሕገ መንግሽቱ ረቂቅ መጋቢት 29/1986 ዓ.ም ወደ ምክር ቤቱ ከቀረበ፣ እና ምክር ቤቱም በሚያዚያ 24/1986 ዓ.ም በአብላጫ ድምጽ ካጸደቀው (adopt) በኋላ የማርቀቁ ሒደት ተጠናቀቀ።
3. የመጨረሻው ሕገ መንግሥቱን የማጽደቅ ሒደት – ሕዝባዊ ይሁንታ የሚሰጥበት አጋጣሚ መታለፍ
የመጨረሻ የሕገ መንግሥት የማጽደቅ ሒደት በሕዝቡ በሚካሄድ ሕዝበ ውሳኔ ወይም በተመረጡ የኮሚሽን አባላት ሊሆን ይችላል። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለሕዝበ ውሳኔ ከመቅረብ ይልቅ በሕዝብ “በተመረጡ” የሕገ መንግሥት አጽዳቂ ኮሚሽን (የሕገ መንግሥት ጉባኤ በሚባል) እንዲጸድቅ ተደርጓል። ይህም ማኅበረሰቡ በሰነዱ ላይ ቀጥታ ተሳትፎ እና ይሁንታ የሚሰጥበትን ሌላ አጋጣሚ እንዲያጣ ምክንያት ሆኖአል።
የሕገ መንግሥት አጽዳቂ ኮሚሽኑ አባላት የተመረጡት ግንቦት 5/1986 ዓ.ም ነበረ። የአጽዳቂ ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥቱን የመመርመር፣ የማሻሻል እና የማጽደቅ ሥልጣኑ ነበረው። ተመራጮቹ የቀረቡት ከግል እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ነበር። ነገር ግን በምርጫው ዋነኛ ተቃዋሚዎች ተሳትፋውበታል ማለት አይችልም። የጉባኤው አባል የነበሩት አቶ ዳንኤል በላይነህ የተባሉ ግለሰብ በምርጫው ላይ በውጪ የሚገኙ ተቃዋሚዎች እና የኢሠፓ አባላት መሳተፍ ባለመቻላቸው ሒደቱ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ መግለጻቸው ዶ/ር ቃልአብ ታደሰ መዝገበዋል። ቀድመው በሽግግሩ ውስጥ የተሳተፉት የተለያዩ የፖለቲካ ኀይሎች እና ልኂቃን ከሒደቱ እየተንጠባጠቡ ወጥተዋል።
የተሳተፉት ድርጅቶች 39 ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ኢሕአዴግ ሒደቱን ቅቡልነት ለማስገኘት የፈለፈላቸው መሆናቸው ይነገራል። መምረጥ ከሚችለው 23 ሚሊዩን ሕዝብ 15 ሚሊዩን እንደተመዘገበ፣ 13.2 የሚሆነው ደግሞ እንደመረጠ ይገለጻል። ከነበሩት አንድ ሺሕ 400 ተመራጮች፤ 937 ከሌላ የፖለቲካ ኀይል እና በግል የተወዳደሩ ሲሆኑ 534 ከኢሕአዴግ የተወከሉ ነበሩ። ኮሚሽኑ ከነበረው 557 አባላት ኢሕአዴግ 539 አሸንፏል።
በአጽዳቂ ኮሚሽኑ ውስጥ የነበሩ ወይይቶች እና ክርክሮች የተዳፈኑ ነበሩ። ለዚህ ዋነኛ የነበረው ምክንያት ኢሕአዴግ የነበረው የግራ ዘመም ፖለቲካዊ አካሄድ ነበር። ይህም ማለት ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት በሚከተለው የፓርቲ ዲሲፕሊን እና የውስጥ ዲሞክራሲ (centralized democracy) ምክንያት አባላቱ እንደ ግለሰብ ሐሳብ ከማቅረብ ይልቅ የፓርቲያቸውን አቋም ይዘው መምጣታቸው ነበር። በዚህም ምክንያት አማራጭ ሐሳቦች ሳይነሱ በሽግግር ምክር ቤት የወጣው ሕገ መንግሥት እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ሳይደረግበት እንዲጸድቅ ሆኖአል።
ከሕልፈታቸው በፊት ከአንድ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የአጽዳቂ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሕገ መንግሥቱ ለሕዝበ ውሳኔ ከመቅረብ ይልቅ በጉባኤ መጽደቁ ታሪካዊ ስሕተት እንደነበር ገልጸዋል።
4. ሕገ መንግሥት ማሻሻል – ለምን እና እንዴት?
ሕገ መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች ሊሻሻል ይችላል። የሕገ መንግሥት አርቃቂዎች ወደ ፊት ሊገጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሙሉ ገምተው ማርቀቅ አይችሉም። በቅርቡ የመንግሥት የአምስት ዓመት የሥልጣን ጊዜ በሚጠናቀቅበት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያሳውጅ እና ምርጫን ለማካሄድ የማያስችል ሁኔታ ሲፈጠር መደረግ ስላለበት አካሄድ በሕገ መንግሥቱ የተፈጠረው ክፍተት ለዚህ ማሳያ ይሆናል። በየጊዜው ከሚኖሩ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ለውጦች ጋር ለማጣጣም ሕገ መንግሥት ሊሻሻል ይችላል።
ከሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም ብቻ ሳይሆን አዲስ የተፈጠሩም ሆነ በፊት ሕገ መንግሥት በሚወጣበት ጊዜ ያልተወከሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ለማካተት ሕገ መንግሥት ሊሻሻል ይችላል።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አወጣጡ አሳታፊ አለመሆኑ እሙን ነው። ሕገ መንግሥቱ ዓላማውን እና ጥቅሙን ባስቀመጠበት መግቢያው ላይ የተቀመጠው “በትግላችን እና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዲሞክራሲ እና ሠላም…” ከሚለው መረዳት የሚቻለው ሰነዱ የአመጽ ውጤት እንጂ የማኅበረሰቡ ስምምነት የወለደው አለመሆኑን ዶ/ር ዘላለም እና አለምነሽ የተባሉ ተመራማሪዎች ሕገ መንግስታዊ ቅቡልነትን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ አንጻር በፈተሹበት ጽሁፋቸው ላይ በትክክል ይገላጻሉ።
ሕገ መንግሥት ከማሻሻያ ሒደቶች አኳያ በኹለት ተከፍሎ ይቀመጣል – “ላላ ያለ” (flexible) እና “ጠንካራ” (rigid) በሚሉ። “ላላ ያሉ” ሕገ መንግሥቶት ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ሕጎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሒደት፣ በምክር ቤት አነስተኛ ድምጽ ሊሻሻሉ ይችላሉ። “ጠንከር ያሉት” ግን ውስብስብ የሆኑ፣ ጊዜ የሚወስዱ፣ ሰፋ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በሚያሳትፉ፣ የሕዝቡን የጋራ መግባባት፣ ዘለቅ ሲልም ሕዝበ ውሳኔን በሚያካትቱ ሒደቶች የሚሻሻሉ ናቸው። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት “ጠንከር” ካሉት የሕገ መንግሥት ጎራዎች ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል።
5. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የማሻሻያ ሒደቶች
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት “የመሻሻያ ሐሳብ መነጨ” ለማለት ሐሳቡን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2/3ኛ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት በ2/3ኛ እና የፌደሬሽኑ አባል ክልሎች 3 ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምጽ ሊደግፉት ይገባል። ይህንን ተከትሎ ለሕዝባዊ ውይይት እና ውሳኔ ብሎም የማሻሻል ሥልጣኑ ለተሰጣቸው ተቋማት ይላካል።
የማሻሻል ሐሳቡ ከመነጨ በኋላ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሚኖሩ የማሻሻል ሒደቶች በኹለት ጎራ ተቀምጧል።
የሰብኣዊ መብት እና የሕገ መንግሥት ማሻሻልን ስለማመንጨት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ሁሉም የፌደሬሽኑ አባላት ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምጽ፣ እና ኹለቱም የፌደራል ምክር ቤቶች ለየብቻቸው በ2/3ኛ ድምጽ ማጽደቅ ይኖርባቸውል።
ከሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎች እና የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ስለማመንጨት ከሚመለከቱ አንቀጾች ውጪ ያሉ ድንጋጌዎች ግን በኹለቱ የፌደራል ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ 2/3ኛ ድምጽ እና ከፌደሬሽኑ ክልሎች 2/3ኛ ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምጽ ማጽደቅ ይኖርባቸዋል።
በመጨረሻ የሕገ መንግሥት ማሻሻያው በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ቁጥር ተሰጥቶት ይታተማል።
ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013



