‹‹በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር ሥር ያሉ መሥሪያ ቤቶች መመሪያቸውን አልላኩም›› ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

የፌደራል የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ለማውጣት የፌድራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያሏቸውን የአሠራር መመሪያዎች በ 90 ቀናት እንዲልኩ የተደረገ ቢሆንም በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የፌደራል መንግሥት መሥሪያቤች መመሪያቸውን አለመላካቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።

የፌደራል የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2020 በፌድራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ መጋቢት 29/ 2012 መውጣቱ ይታወሳል፤ ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁን ለማውጣት የፌድራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያሏቸውን የአሠራር መመሪያዎች እንዲልኩለት የ90 ቀን ጊዜ ቢሰጥም በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የፌድራል መንግሥት መሥሪያቤች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም አንዳንድ በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የፌደራል መንግሥት መሥሪያቤቶች አለመላካችው ለአሠራሩ እንቅፋት እንደነበር ተናግሯል።

በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ኀላፊ እንዳልካቸው ወርቁ እንደገለጹት የፌደራል የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ሁሉም የፌደራል መሥሪያቤቶች ያሏቸውን መመሪያዎች ቁጥር ተሰጥቷቸው በጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና በራሳቸው ድረ ገጽ ላይ ካልተጫነ እንደ ሕግ አይቆጠርም ብለዋል። እነዚህ መመሪያዎቻቸውን ያልላኩ የፌደራል ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ተጠያቂነት ካለባቸው ተገልጋዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ክስ ሊመሰርትባቸው ይችላል በማለት ገልጸዋል።

የፌደራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ከዚህ በፊት ያልነበረ መሆኑን ገልጸው የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ መውጣቱ ተገልጋዩ የሚሰጠውን አገልግሎት በግልጽ እንዲያውቅ ያደርጋል፣ከመሥሪያ ቤት መሥሪያ ቤት ያለውን አሠራር ወጥ እንዲሆን ያደርጋል፣መሥሪያ ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎት የተለያየ ቢሆንም እንደየ ሥራ ባህሪያቸው አሠራራቸው ግልጽ ቀልጣፋ እንዲሆን እና ተመሳሳይ ውሳኔ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

እንዳልካቸው ተመሳሳይ የሆኑ ተቋማት የተለያየ ውሳኔ ሲሰጡ የሚታየው ወጥ የሆነ የአሠራር ሥነ-ሥርኣት ባለመኖሩ በግለሰቦች የግል ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሰረተ ግልጋሎት ስለሚሰጥ ነው በማለት ተናግረዋል። የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ያላቸው አገራት በጣም ውጤታማ እንደሆኑ በርካታ ተሞክሮዎችን ማየት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ሰለሞን አባይ(ዶ/ር) ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ተለያዩ ቁንጽል የአስተዳደር መመሪያዎች በአንዳንድ መሥሪያቤቶች ብቻ የነበሩ ቢሆንም በአገራችን አሥተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ መጋቢት 29/ 2012 እንደወጣ ገልጸዋል።

ሰለሞን (ዶ/ር) በፌደራል መንግስት ከሚተዳደሩ የአለማችን አገራት መካከል ጀርመንን እንደ ምሳሌ ብንወስድ እንኳን የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ያወጡት የፌደራል እና የክልል መንግሥታት በጋራ ተቀምጠው ሲሆን ወጥ የሆነ የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ስለሚከተሉ አሠራራቸው ተመሳሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በኛ አገር የወጣው የፌደራል የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ የሚያገለግለው ለፌደራል የመንሥት መሥሪያ ቤቶች ሲሆን ክልሎች የራሳቸውን ሥልጣን ተጠቅመው የራሳቸውን የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ማውጣት ይችላሉ ሲሉ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ኀላፊ እንዳልካቸው ገልጸዋል።

መንግሥታዊ አሠራርን ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ ለማከናወን እና ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን ኃላፊነቱን ቢያጓድል ተጠያቂ እንዲሆን እንዲሁም የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉትን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራ እና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን መረጋገጥ በማስፈለጉ እንዲሁም በአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥ እና የመመሪያ አወጣጥ ሥነ-ሥርአት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ ቅር የተሰኘ ሰው የውሳኔዎቹን እንዲሁም የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ሥርኣት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትህን ለማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ በኢትዮጵያ ፌድራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሰረት የፌደራል የአሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ታውጇል።

አዲስ ማለዳ በድሬዳዋ የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደውላ ለማጠራት ሙከራ አድርጋም የድሬዳዋ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ የሆኑት ሕዝቅኤል ታፈሰ ስለ ጉዳዩ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here