የፍልሰተኞች ፖሊሲ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተዘጋጀ ነው

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፍልሰተኞች ፖሊሲ እየተዘጋጀ እንደሆነ በኢፌዴሬ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቤል ገብረእግዚአብሄር ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

ዐቃቤ ሕጉ ከዚህ በፊት በሠራኞች እንዲሁም በዲያስፖራዎች ዙሪያ የወጡ እንጂ በፍልሰት ዙሪያ የተጠቃለለ እና ሁሉንም ያማከለ ፖሊሲ አልነበረንም ብለዋል። ከ 2011 መጨረሻ ጀምሮ አቅጣጫ በማስቀመጥ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሪነት ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ፣ፕላን እና ልማት ኮሚሽን እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ኮሚቴ በማዋቀር እንዲሁም ዓለማቀፍ አማካሪ በመቅጠር የፖሊሲውን ረቂቅ እያዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል።

ስደት በኹለት መንገድ እንደሚከፈል ገልጸው መደበኛ የሆነ በሕጋዊ መንገድ የሚደረግ እና መደበኛ ያልነ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚደረግ ነው። የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሰዎች የመነገድ እና ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመከላከል አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ማውጣቱን አስታውሰዋል። አዋጁ ዜጎችን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከተለያዩ የብዝበዛ ተግባር መጠበቅ፣ በሕገ-ውጥ መንገድ ከአገር የመውጣትም ሆነ የመግባት ድርጊቶችን መከላከልና መቆጣጠር እና ዜጎች ለሥራ ወደ ውጭ አገር በሕገ- ወጥ መንገድ በመሄድ ለአደጋ እንዳይጋለጡ መጠበቅ የሚሉ ሦስት አላማዎችን መሰረት በማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዐቃቤ ሕጉ አሁን እየተዘጋጀ ያለው የፍልሰተኞች ፖሊሲ ስደትን እንደ እዳ ብቻ የሚቆጥር ሳይሆን ጠቃሚ ጎን እንዳለው የሚያሳይ ጭምር ነው ብለዋል።የበለጠ ትኩረት የምንሰጥበት ግን በሕገ-ወጥ መንገድ በሰዎች ላይ መነገድ፣በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ለሥራ መላክ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። በእነዚህ እና ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማካሄድ አቅጣጫዎችን እያስቀመጥን እንገኛለን ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጅ ትምህርት ክፍል ኀላፊ አበባው ምናየ (ዶ/ር) የፍልሰተኞች ፖሊሲ ባለመኖሩ በፍልሰት ዙሪያ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ስለሌለን እንኳን ሕገ-ወጥ ስደትን ይቅርና ሕጋዊ የሆነውንም መልክ ማስያዝ አልቻልንም ነበር። ሕገ ወጥ ስደት እንዲንሰራፋም አንደ ምክንያት ሆኗል። ዜጎቻችንን እውቀት አስጨብጠን በመላክ ከነርሱ ማግኘት ያለብንን ጥቅም ማግኘት አልቻልንም ለነርሱም ጥበቃ አላደረገንም ብለዋል።

አበባው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት ፈልሰው የገቡ በርካታ ስደተኞች ያሉባት ከአገር ውስጥም ከፍተኛ የሆነ መፈናቀል የበዛባት አገር ሆናለች። ስለዚህ ይህ ፖሊሲ መውጣቱ ስለነዚህ ሰዎች የሚመለከተው አካል ማን እንደሆነ መለየት እንድንችል ይረዳናል። ከስደት ተመላሾችም ቢሆኑ የአለማቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) እዳ ናቸው።ፖሊሲ ሲኖር ግን ይህንን የተበታተነ አሠራር አንድ እንዲሆን ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

‹‹ፍልሰት፣ የውጭ ሐዋላና የቤተሰብ ሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት የኢትዮጵያ የጉልበት ሠራተኞች ፍልሰት ወደ መካከኛው ምሥራቅና ወደ ደቡብ አፍሪካ›› በሚል ርዕስ ዘሪሁን ሞሐመድ (ዶ/ር) እና አስናቀ ከፍያለ (ዶ/ር) በጋራ ባጠኑት ጥናት፤ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በተለይም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎችም የዓረብ አገሮች ከሚያቀኑትና ከተመላሽ ስደተኞች በተገኘው መረጃ መሠረት ከ97 በመቶ ያላነሱት ወደ አገር ቤት ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ይልካሉ።

ጥናቱ ካካተታቸው 240 ገደማ አባወራዎች መካከል በውጭ ከሚገኙ ልጆቻቸው ወይም የቤተሰባቸው አባላት ውስጥ 37 በመቶዎቹ ከአምስት እስከ 10 ሺሕ ብር በየወቅቱ ይላክላቸዋል። 15 በመቶዎቹ ስደተኞች ከ10 ሺሕ በላይ እንደሚልኩ ሲጠቀስ፣ ከ20 ሺሕ ብር በላይ የሚልኩት በአብዛኛው በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ስደተኞች መሆናቸውን ተገልጿል።

እንዲህ ያለውን አነስተኛ የገንዘብ መጠን በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆነው ወደ አገር ቤት ቢልኩም፣ አብዛኛው የላኩት ገንዘብ ግን ለቤተሰቦቻቸው ልዩ ልዩ ፍጆታዎች የሚውል በመሆኑ ከስደት በሚመለሱበት ወቅት በአገር ቤት ሥራ መሥራት የሚችሉበት ጥሪት አይተርፋቸውም። በዚህ ሳቢያም አብዛኞቹ መልሰው በቤተሰቦቻቸው ላይ ጥገኛ ለመሆን እንደሚገደዱ፣ መልሰው ችግር ላይ ሲወድቁ እንደሚታዩ ምሁራኑ በጥናቱ አረጋግጠዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here