ዘውግ እና የዘውግ ፖለቲካ

ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በዚህ መጣጥፋቸው በዘውግ እና ዘውግን መሰረት ባደረገ ፖለቲካ ዙሪያ የኢትዮጵያን ነባራዊ ኹኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም የአገራት ተመክሮዎችንም በማካተት ከቃላቶች ብያኔ ጀምሮ ዘውግ እና ግጭቶች መካከል ስላለው ቁርኝት ተንትነው ምልከታቸውን አጋርተዋል። በተለይ በዘውግ ፖለቲካ እና በግጭቶች መካከል ያለውን ትስስር ለመረዳት መጤን ይገባቸዋል የሚባሉ ጉዳዮችን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አስተሳስረው አቅርበዋል።

ሟሟሻ
የቀድሞዋ ዩጎስላቪያ አካል የሆነችው ጉሁሳንጅ (Gusinje) በምትባል የሞንቴኔግሮ አነስተኛ ከተማ የቱርክ ዝርያ ካላቸው ቤተሰቦች የተወለው ዙቭዲጃ ሆድዚክ (Zuvdija Hodžić) በአንድ ወቅት የሚከተለውን ተናገረ።
ወደ እስታቡል ከተማ ስደርስ ሰዎች ‹‹ማነህ?‹‹ ብለው ጠየቁኝ፤ በሙሉ ልብ ‹‹እኔ ቱርክ ነኝ‹‹ አልኳቸው። አንገታቸውን እየነቀነቁ ‹‹አ!… አ!… አንተማ ቱርክ አይደለህም፤ አልባኒያዊ ነህ‹‹ አሉኝ። ያሉኝን ተቀብዬ ‹‹ከእንግዲህ አልባኒያዊ ነኝ‹‹ ብዬ ራሴን አሳምኜ የአልባኒያ ከተማ ወደ ሆነችው ስኮደራ (Shkodra) ሄድኩ፤ እዛ ስደርስ ግን ቦስኛክ መሆኔ ተነገረኝ። ቦስኛክነቴን ተቀብዬ የቦስኒያ ኸርዞጎቪና ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ሰሪዬቮ (Sarejevo) ሄድኩ። እዚያ ስደርስ ደግሞ ሰዎች ‹‹ቦስኛክ ነኝ‹‹ ማለቴን እንደ እንደ እብደት ቆጠሩት፤ ትውልዴን አስልተው ሞንቲኔግሮ መሆኔን አስረግጠው ነገሩኝ። ይሁን እንጂ የሞንቴኔግሮ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ፖድጎሪትሳ (Podgorica) ስደርስ እኔ ከቱርክ ውጭ ምንም መሆን እንደማልችል ተነገረኝ። [ይህ እውነተኝ ታሪክ Florian Coulmas (2019) ከፃፈው Identity ከተሰኘው መጽሐፍ የተወሰደ ነው]።

ከድብልቅ የቤተሰብ ሐረግ የተወለዱ፤ የቤተሰቦቻቸው የዘር ሐረግ ከሚበዛበት አካባቢ ውጭ ያደጉ፤ በቤተሰብ ሥራ ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ከተለያዩ ማኅበረሰቦች በመኖር ድብልቅ ማንነቶችን ያዳበሩ እንደ ዙቭዲጃ ሆድዚክ ዓይነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ እገምታለሁ።

በቃላት መወዛገብ
አንዳንድ ሰዎች ‹‹ዘውግ›› የሚለው ቃል ‹‹ብሔርን›› የሚያሳንስ አድርገው ስለሚወስዱት ምቾት አይሰጣቸውም። ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃል ለመጠቀም ደግሞ በርካታ ችግሮች አሉ። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ‹‹ብሔር››፣ ‹‹ብሔረሰብ›› እና ‹‹ሕዝብ›› ለሚሉ ሦስት ቃላት የሰጠው ትርጓሜ ግልጽ አይደለም። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንደ ውል ካየነው ‹‹የውሉ ፈራሚዎች›› እና ‹‹የውሉ ባለቤቶች››፤ እንደ መግለጫ ካየነው ደግሞ የመግለጫው ፀሐፊዎች›› ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች›› ናቸው። ይሁን እንጂ በሕገ መንግሥቱ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ቦታ የተሰጣቸው አካላት ምንነት ግልጽ አይደለም፤ ምናልባትም የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎችም በትክክል አያውቋቸውም ነበር ይሆናል። ይህን ለማለት ያስደፈሩኝን ጥቂት አንቀጾችን እጠቅሳለሁ።

አንቀጽ 8፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት
1. የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።
2. ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መግለጫ ነው። [‹‹መገለጫ›› አይደለም መግለጫ]
በዚህ አንቀጽ ዕሳቤ መሠረት፡
1. በአንቀጹ ርዕስ ‹‹የሕዝብ ሉዓላዊነት›› በሚለው ሐረግ ውስጥ ያለው ‹‹ሕዝብ›› የሦስቱ ጽንሰ ሐሳቦች – ‹‹ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› ድምር ነው። በሒሳብ ስሌት እናቀምጠው ቢባል ብሔሮች + ብሔረሰቦች + ሕዝቦች = ሕዝብ። በአንቀጽ 8፣ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ ሲሆኑ ሕዝብ ሉዓላዊ ይሆናል።

2. ሕገ መንግሥቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ ያወጡት መግለጫ ነው። ሦስቱ በጋራ ስላወጡት ‹‹የሕዝብ ሉዓላዊነት›› መግለጫ ሆነ።
ይህ ስሜት እንዲሰጥ አድርጎ መረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። ችግሩ የቋንቋ አጠቃቀም አይደለም፤ የአስተሳሰብ ነው። እነዚህ ቃላት በዚህ ሁኔታ ሲቀመጡ ሥርዓት የያዘ አስተሳሰብን (disciplined thought) አይፈጥሩም።
ስለሦስቱ ቃላት ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ የተሰጠበት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 5 የሚከተለው ነው።

በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ›› ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን ባህርይ የሚያሳይ ማኅበረሰብ ነው። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፤ ሊግባቡ የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፤ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፤ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው።

1. ይህ ትርጓሜ እጅግ በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮች ቢኖሩትም ከሁሉም የባሰው ‹‹ብሔር››፣ ‹‹ብሔረሰብ›› እና ‹‹ሕዝብ›› የተባሉት ሦስት ቃላት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያላቸው ትርጉም አንድ መሆኑ ነው። ሦስቱም ትርጉማቸው አንድ ከሆነ ሦስት ቃላትን መጠቀም ለምን አስፈለገ?

2. በዚህ ትርጓሜ መሠረት ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ›› ማለት በዚሁ ንዑስ አንቀጽ የተዘረዘሩት ባህሪያት ያሉት ‹‹ማኅበረሰብ›› ማለት ነው። ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ›› ማለት ማኅበረሰብ ማለት ከሆነ ታድያ ለምን ባህሪያቱን ገላጭ ቃል አስቀድመን ‹‹ማኅበረሰብ›› የሚለውን ቃል አናስከትልም? ለምሳሌ አንዳርጋቸው ጽጌ ያስተዋወቀውን ‹‹ዘውጌ ማኅበረሰብ›› ወይም ከዘውግ የተሻለ ቃል ካለ ሌላ ቃል ለምን አንፈልግም?

3. ‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ›› ማለት የሚለው አገላለጽ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃል በዚሁ ሕገ መንግሥት በተለየ ትርጓሜ ሥራ ላይ ውሎ እናገኛለን። ሕገ መንግሥቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ (አንቀጽ 3)፣ ብሔራዊ መዝሙር (አንቀጽ 4) እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (አንቀጽ 102) ይላል እንጂ ‹‹ብሔራዊ፣ ብሔረሰባዊና ሕዝቦቻዊ›› ስለማይል በእነዚህ አንቀጾች ያለው ‹‹ብሔራዊ›› በሕገ መንግሥቱ መግቢያ፣ አንቀጽ 8 እና 39 ካለው ትርጓሜ የተለየ ነው። በሕገ መንግሥቱ የእንግሊዝኛ ቅጂ ደግሞ ዜግነትን nationality ተብሎ የተረጎመ መሆኑ፤ “national standards”, “national security” የሚሉ ሐረጎች ስላሉ ተጨማሪ የጽንሰ ሐሳቦች ግጭት አለ።
ሕገ መንግሥቱ በፈጠረው የጽንሰ ሐሳብ ዝንፈት ምክንያት የእንግሊዝኛውን “ethnicity” ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ብለን መተርጎም የምንችል አይመስለኝም። በዚህም ምክንያት ዘውግ የሚለውን መጠቀም መርጫለሁ፤ ሆኖ በአንዳንድ ሁኔታዎች ‹‹ብሔር›› የሚለውን ቃል መጠቀም የተሻለ መስሎ የተሰሙኝ ቦታዎችም አሉ። ለእኔ የቃላት ምርጫ ዋነኛ መመዘኛዬ ሐሳቤን የትኛው ቃል የተሻለ ያስተላልፍልኛል የሚለው ነው።

ስለ ዘውግ (Ethnicity)
ስለ ዘውግ (Ethnicity) ከተሰጡ ብዙ ትርጓሜዎች የቶማስ ኤሪክሰን እመርጣለሁ። እንዲህ ይላል – “Ethnicity is an aspect of social relationship between persons who consider themselves as essentially distinctive from members of other groups of whom they are aware and with whom they enter into relationships” (Eriksen, 2010, pp.16-17) በደምሳሳው ‹‹ዘውግ ማለት ሰዎች ከሚያውቋቸውና በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከተጎዳኟቸው ሌሎች ቡድኖች ራሳቸው የተለዩ አድርገው ከሚያቀርቡባቸው ማኅበራዊ ግኑኝነቶች አንዱ ነው።›› ሊተረጎም ይችላል።

ሰዎች ከሚያውቋቸው ሌሎች የቡድን አባላት ራሳቸውን የሚለዩባቸው ብዙ መንገዶች አሏቸው። ዕድሜ፣ ፆታ፣ ሙያ፣ ሃይማኖት፣ የጋራ ተስፋ፣ የጋራ ሀዘን፣ … ዝርዝራቸው ብዙ ነው። ዘውግ (ጎሳ፣ ብሔረሰብ፣ ብሔር .. የምንለው) ከእነዚህ ሁሉ ራስን የመለያ አማራጮች አንዱ ነው። ዋናው ሥራው ራስን በቅርብ ካሉ ‹‹ሌሎች›› ለይቶ ማቅረቢያ ነው፤ ከዚህ ውጭ በውስጡ ምንም የተለየ ምስጥራዊ ነገር የለም። የዘውግ ማንነት የሚያገለግለው ራስን በቅርብ ካለው ሌላ ቡድን ወይም ሌሎች ቡድኖች ለመለየት እንጂ ሩቅ ካለው ለመለየት እጅግም ፋይዳ የለውም። አንድ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ብሔር፣ ብሔረሰቦች የአንዱ አባል መሆኑ በብዙ ነገሮች እሱን ከሚመስሉ የቅርብ ጎረቤቶቹ ከሆኑ ሰዎች ራሱን ለመለየት ይጠቅመው እንደሆን እንጂ ራሱን ከፓኪስታን፣ ከአዘርባጃን ወይም ከብራዚል ለመለየት ምንም አይፈይድለትም። ብሔረተኞች ራሳቸውን ለይተው ለማቅረብ የሚጥሩት በቅርባቸው ካሉት በብዙ ነገሮች በሚመስሏቸው ወገኖቻቸው ነው።

ለምን የብሔር ጉዳይ እንዲህ የብዙዎችን ልብ የሚነካ ነገር ሆነ ለሚለው ጥያቄ ቶማስ ኤሪክሰን መልስ አለው። “Ethnic groups have myths of common origin, and they nearly always have ideologies encouraging endogamy, which may nevertheless be of highly varying practical importance” (p.17) የአንድ ብሔር አባላት ከአንድ ግንድ የበቀሉ፤ በሆነ ሩቅ ጊዜ ከአንድ እናትና ከአንድ አባት የተወለዱ እንደሆነ ዓይነት አፈታሪክ አላቸው። በተግባር ይገለጽም አይገለጽ ሁሉም በብሔር ውስጥ የሚወሰን ጋብቻን (endogamy) ያበረታታሉ። ዶናልድ ሆሮይትዝ ደግሞ “the idea, […] not always the fact, of common ancestry makes it possible for ethnic group to think in terms of family resemblance” (Horowitz, 1985. p. 56) እውነት ይሁንም አይሁን ‹‹ከአንድ ግንድ የወጣን ነን‹‹ የሚለው እምነት የቤተሰብ አባላት የሆኑ ዓይነት ስሜት እንዲፈጥሩ ያደርጋቸዋል።

የአንድ ሰው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ቋሚ ነገር ነው ወይስ በዚህ ጽሁፍ ማሟሻ ላይ እንዳነሳነው ዙቭዲጃ ሆድዚክ ብሔር በቦታና ሁኔታዎች የሚለዋወጥ ነው ወይ ለሚለው ጥያቄ መልስ በእያንዳንዱ ሰው አተያይ ይወሰናል። ይሁንና ግን ሦስት ዋና ዋና አተያዮች አሉ።
1. ‹‹ጅማሬዓዊ አተያይ›› ( Primordial Approach)፡ ሰው ብሔር ይዞ ይወለዳል፤ ብሔሩን እንደያዘ ይሞታል ብሎ የሚያምን አተያይ ነው። የዚህ አተያይ አራማጆች ልጅ የሚወለደው ለእናትና አባቱ ብቻ ሳይሆን ለጎሳውም ለብሔሩም ጭምር ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው። በዚህ አተያይ የብሔር ጉዳይ ለምንም ዓይነት ድርድር የማይቀርብ፤ ቀድሞ ተጽፎ ያለቀ ጉዳይ ነው። ባህርይም በተፈጥሮ የሚወሰን ነው ብለው ስለሚያምኑ እያንዳንዱ ዘውግ (ጎሳ፣ ብሔረሰብ፣ ብሔር) የራሱ ቋንቋና ባህል ብቻ ሳይሆን ባህርያትም አሉት። በዚህም መሠረት ‹‹ደግ ጎሳ›› አለ ‹‹ክፉ ጎሳ›› አለ፤ ‹‹ጀግና ብሔር›› አለ፤ ‹‹ፈሪ ብሔር›› አለ፤ ‹‹ለጋስ ብሔር›› አለ፤ ‹‹ቆጥቋጣ ብሔር›› አለ። የዚህ አተያይ ተከታዮች ሁል ጊዜ ጥሩ ጥሩውን ለራሳቸው ብሔር፤ ክፉ፣ ክፉውን ደግሞ ለሌሎች ይሰጣሉ። የዚህ አተያይ ተከታዮች የአንድን ሰው ብሔር እንዳወቁ ሐቀኛ ይሁን አይሁን፤ ጀግና ይሁን ፈሪ፤ ቸር ይሁን ስስታም ያወቁ አድርገው ይወስዱታል፤ ግኑኝነታቸውን ወዲያውኑ በዚሁ መሠረት ያስተካክላሉ። ይህ ‹‹ጅማሬዓዊ አተያይ›› ስያሜው እንደሚያመላክተው ሁሉ ለግለ ስብዕና ዋጋ የማይሰጥ፤ ሰዎችን በቡድን እንጂ በግል ለመመዘን የሚቸገር፤ የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ ሲወለድ ጀምሮ የተወሰነ ነው ብሎ የሚያስብ ኋላቀር አስተሳሰብ ነው። ይህ አተያይ ነው ጋብቻን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርገው – መጋባት የሚይችሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ ለመጋባት የሚፈላለጉ ጎሳዎች አሉ። አገራችን ውስጥ ያለው የብሔር እይታ በአብዛኛው በዚህ መስመር የተቃኘ በመሆኑ ለብሔር ተሻጋሪ ትብብር እና ድርድር አስቸጋሪ አድርጎታል።

2. ‹‹ተለዋዋጭ አተያይ›› (Perennial Approach) ፡ ይህ የአንድ ሰው ብሔር ወይም ዘውግ እንደ ሁኔታው የሚቀያየር ነው የሚል አተያይ ነው። አንዳንድ ብሔሮች በረዥም ታሪካቸው ምክንያት ቋሚ መስለው ሊታዩ ይችላሉ፤ አንዳንዶች ተቋርጠው እንደና ይጀምራሉ፤ አዳዲሶችም ይወለዳሉ። የዚሁ አተያይ አካል የሆነው Instrumentalist Perennialism ዘውግን እንደ ዘርፈ ብዙ መገልገያ መሣሪያ (as a multipurpose tool) ይመለከታል። በዚህ አተያይ ብሔሮች የልኂቃን መጫወቻ ካርታዎች ናቸው፤ ይበትኗቸዋል፤ ይደባልቋቸዋል፤ ካስፈለገን አዳዲስ ይፈጥራሉ። የሕወሓት/ኢሕአዴግ የብሔሮች እይታ በአብዛኛው Instrumentalist Perennialism ነው። ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ማግስት ጀምሮ ብሔር ብሔረሰቦችን ሲፐውዝ፤ ሲሰነጥቅና አዳዲስ ሲሠራ ቆይቷል። ሕወሓት/ኢሕአዴግ ለአገዛዝ እንዲያመቸው ብሔሮችን ሰንጥቋል (ለምሳሌ ጉራጌ እና ስልጤ፤ አማራ፣ ወልቃይት፣ ራያ፤ ጉጂ እና ቡርጂ … )፤ ብሔሮችንም አዋህዷል (ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሊ፣ ትግራዋይ፣ … እነዚህ የብዙ ራሳቸውን ችለው ብሔር መባል የሚችሉ አካላት ውህድ ናቸው)።

3. ‹‹ግንባታዊ አተያይ‹‹ (Constructivist Approach)፡ ይህ አተያይ ዘውግ በማኅበረሰቦች መካከል የሚኖሩ ትብብሮችና ፉክክሮች፤ መስተጋብሮችና ፍትጊያዎች ውጤት አድርጎ የሚያይ ነው። ዘውጎች ለልኂቃኑ ሀገር ግንባታ ፕሮጀት እስካገለሉ ድረስ የሚኖሩ አስፈላጊነታቸው ሲያበቃ የሚረሱ ነገር አድርጎ የሚገነዘብ አተያይ ነው። ለምሳሌ ፍሎሪያን ኮልማስ “ethnicity and cultural identity are not timeless and static. … Many [contemporary] ethnic groups are the result of relatively recent fission or fusion” (Coulmas, 2019, p.29) ይላሉ። ‹‹ዘውግ እና ባህላዊ ማንነቶች ዘላለማዊና ቋሚ አይደሉም። ብዙዎቹ አሁን ያሉት የዘውግ ስብስቦች (ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች) አንጻራዊ በሆነ ቅርብ ጊዜ ውስጥ በነበሩ መለያየቶች እና መዋሃዶች ሳቢያ የተፈጠሩ ናቸው። ‹‹ማኅበረሰቦች በቅራኔ ሳቢያ ቀስ በቀስ ይለያያሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የተለያዩ ማኅበረሰቦች በረዥም ጊዜ ይዋሃዳሉ። ይህ አተያይም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመረዳት እና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለመፈለግ የሚጠቅም ይመስለኛል።
ብሔርን እንደ ቋሚ ነገር መመልከት አሁን ተቀባይነት እያጣ የመጣውን አስተሳሰብ ማራመድ ነው። በአገራችን እንዳየነው ፓለቲከኞች ቅርንጫፍ የነበረውን ዘውግ ግንድ አድርገው በማቅረብ የማንነት መለያ ሊያደርጉ፤ ግንድ የነበረውን ደግሞ ቅርንጫው አድርገው የአንድ ብሔር አካል አድርገው ሊያቀርቡ ይቻላቸዋል። ለሀገር ግንባታ ቅድሚያ ከሰጡ ደግሞ ከሌሎች በላይ ሀገራዊ ማንነትን በማጉላት ሊያሰባስቡት ይቻላቸዋል።

በዘውግ ፖለቲካ እና ግጭቶች መካከል ስላለው ቁርኝት
የዘውግ ፖለቲካን ‹‹የብሔር ፖለቲካ››፣ ‹‹የዘር ፖለቲካ‹‹፣ ‹‹የጎሳ ፖለቲካ‹‹ … ወዘተ እያልን በተለያዩ ሥያሜዎች የምንጠራው መሆኑ ግንዛቤ ይያዝልኝ። ለመሆኑ ‹‹የዘውግ ፖለቲካ›› ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ ጥሩ ትርጓሜዎች ናቸው ከምላቸው ኹለቱን ብቻ ልጥቀስ፡-
የመጀመሪያው “Ethnic politics refers to a situation in which politicians tend to mobilize support on the basis of an appeal to ethnic identity and people tend to support leaders from the same ethnic group”” (Lynch, 2015,p.1) ሲሆን ትርጉሙም ‹‹የዘውግ ፖለቲካ›› ፓለቲከኞች የድጋፍ መሠረቶቸው በዘውግ (በብሔር፣ ብሔረሰብ) ማንነት ላይ ተመርኩዘው በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ላይ የሆነበት እና ሰዎችም ከራሳቸው ብሔር ለወጣ መሪ ድጋፋቸውን የሚሰጡበት ሁኔታ ነው።

በቀላል አገላለጽ ‹‹የዘውግ ፖለቲካ›› መሪዎች ለራሳቸው ዘር ተከታዮች፤ ተመሪዎችም ለራሳቸው ዘር መሪዎች የሚቆሙበት ፖለቲካ ነው። በዘውግ ፖለቲካ ውስጥ የፓሊሲ አማራጮች እምብዛም ዋጋ የላቸውም፤ ቀዳሚው ጉዳይ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ነገድ ነው።
ኹለተኛው “Ethnic politics can be understood as a struggle over control of the state between various ethnically defined organizations and their constituencies” (Cederman, Wimmer and Min, 2010, p.95) ሲሆን ትርጉሙም ‹‹የዘውግ ፖለቲካ›› ራሳቸውን በዘውግ (በብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ነገድ) ያደራጁ ድርጅቶችና ተከታዮቻቸው የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ የሚያደጉት ትንንቅ አድርጎ መረዳት ይቻላል።

በዚህ ትርጓሜ መሠረት የዘውግ ፖለቲካ ግቡ የመንግሥትን ሥልጣን በብሔር ድርጅት መቆጣጠር ነው። የዘውግ ፖለቲካ የበላይነት በጨበጠት አገር ሥልጣን የያዘው የፖለቲካ ልኂቅ በአጋር ፍለጋም ሆነ በማኅበራዊው ምርቶች ስርጭት ለራሱ ወገን ማዳላቱ የማይቀር ነው። የዘውግ ፖለቲካ በገነነበት ገለልተኛ የሚባል መንግሥትም ሆነ ሌላ ተቋም የለም። የዘውግ ፖለቲካ የበላይነት በጨበጠት አገር የትኛው የዘውግ ድርጅት የትኛውን የመንግሥት ቢሮ ያዘ የሚለው ነጥብ ሳይቀር የፍልሚያ ሜዳ ነው። በዚህም ምክንያት የዘውግ ፖለቲካ ከግጭት መራቅ አይችልም።

በዘውግ ፖለቲካ እና በግጭቶች መካከል ያለውን ትስስር ለመረዳት ቢያንስ አምስት ጉዳዮች መጤን ይኖርባቸዋል (1) ብሶት (Grievance)፣ (2) ስስት (Greed)፣ (3) ብዝሀነት (Diversity)፣ (4) ጽንፈኛነት (Polarisation)፣ እና (5) የዘውግ ደህንነት አጣብቂኝ (Ethnic Security Dilemma)። እነዚህ እያንዳንዳቸው ሰፋፊ ርዕሶች ቢሆኑም እጅግ በጣም አሳጥሬ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

1. ብሶት
የዘውግ ፖለቲካ በባህርዩ የብሶት ፖለቲካ ነው። ከዘውግ ፓለቲከኞች አንደበት የሚደመጠው ‹‹ተገፋን፣ ተበደልን፣ ተገለልን፣ ተሳደድን፣ ተገደልን‹‹ የሚሉ ምሬቶች ናቸው። ይህን የሚሉ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ዘውጎች መሪዎች ብቻ አይደሉም፤ በቁጥር አብላጫ የሆኑትም ማማረራቸው አይቀርም። ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ አብላጫ የያዘ ብሔር ቢኖር እንኳን የዘውግ ፓለቲከኛ ከሆነ ማማረሩ አይቀርም። የዘውግ ፓለቲከኞች ራሳቸውን ሲቃረኑ አይታወቃቸውም። በአንድ በኩል ሁሌ የራሳቸውን ዘውግ አባላት ቁጥር አስበልጠው መናገር ይወዳሉ፤ ይኩራራሉ። ‹‹እኛ ጀግኞች ነን፣ አንበገርም‹‹ ይላሉ፤ ይህንን ባሉበት ደግሞ ‹‹ተበደልን፣ ተገፋን፣ አለቅን‹‹ ይላሉ። የዘውግ ፖለቲካ ከብሶት ውጭ አይታሰብም። ለብሶት ምክንያት መቼም ቢሆን አይጠፋም። የዘውግ ፖለቲካ ትኩረት ያለውን ብሶትን በማጋነንና በማጋጋል ፖለቲካዊ ትርፍ መሻት እንጂ መፍትሔ ፍለጋ ላይ አይደለም። የዘውግ ፖለቲካ መሪዎች ተግባራትን የማቀናጀት እና ‹‹የነፃ ጋላቢዎች‹‹ (free riders) ችግር ስላለባቸው ብሶታቸውን ከመጠን በላይ ያስጮሃሉ፤ ከዚያም አልፎ ጩከታቸውን ያልጮኸ ሁሉ በጠላትነት በመፈረጅ አምባገነናዊ እርምጃዎችን ይወስዳሉ። ብሶታቸው ያላስተጋባ፤ ጩኸታቸውን ያልጮኸ ሁሉ ጠላታቸው ነው።

2. ስስት
የዘር ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን በሙሉ ነው ‹‹ስስት‹‹ በሚል ምፀታዊ ቃል ማጠቃለል ይቻላል። የፖለቲካ ልኂቃን በዘር ፖለቲካ ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርጓቸው ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች አሉ። በብዙ አገሮች የታየው ልምድ እንደሚያረጋግጠው ‹‹የነፃ አውጭዎች›› መሪዎች ቀድመው ነፃ የሚያወጡት ራሳቸውን ነው። የዘውግ መሪዎች ለዘውጎቻቸው መታገላቸው የሚያስገኙላቸው በርካታ የግል ጥቅሞች አሉ፤ ዝና፣ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት የሚፈቅድ ብዛት ያለው ተከታይ፣ ንብረት እና ገንዘብ መሪዎችን በትግሉ ዘመን ያማልላሉ። ትግሉ ስኬታማ ከሆነ ደግሞ የመንግሥት ሥልጣን እና ሥልጣንን ተከትሎ የሚመጣ ሀብት ቤታቸው ይገባል። በብዙ አገሮች የዘውግ ፖለቲካ ከሀብት (resource) ቅራኔ ጋር የተያያዘ ነው። የትግሉ ድብቅ ግብ ያንን ሀብት በቁጥጥር ሥር ማዋል ነው። እንደሚታወቀው የሀብት ዓይነቶች ብዙ ናቸው፤ ማዕድናት፣ መሬት፣ የአባላት መዋጮ፣ በውጭ አገራት ከሚገኙ ዜጎች የሚገኝ ድጋፍ፣ ሕገወጥ የመሣሪያና የሸቀጦች ንግድ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በአገሪቱ ጉዳይ እጃቸው ማስገባት የሚፈልጉ የውጭ ኃይላት መደለያ፣ … እነዚህና የመሳሰሉት ሁሉ ሀብት ናቸው። አንዳንድ ተመራማሪዎች የዘር ፖለቲካ ያለ ሀብት በጭራሽ መምራት ስለማይቻል፤ የዘር ፖለቲካ ማጥፊያ አንዱ መንገድም የሀብት ፍሰቱን መዝጋት ነው ብለው ይመክራሉ። እነዚህ ምሁራን የተካረረ የዘር ግጭቶች የሚበዙት ብሶቶች በበዛባቸው ሳይሆን ልል የማስተዳደር ሁኔታ ያለባቸው ሀብቶች ባሉባቸው ቦታዎች ነው ይላሉ፤ ለዚህ ክርክሮቻቸውም በርካታ ማስረጃዎች አሏቸው።

3. ብዝኀነት
ብዝሀነት እና ቅራኔ ያላቸው ተዛምዶ በተመለከተ በአንድ ጉዳይ ግን ሰፊ መግባባት አለ። የፖለቲካ ቅኝት ካልተሰጣቸው በአንድ አገር ውስጥ ያሉት ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ነገዶች፣ ጎሳዎች … ብዙም ይሁኑ ጥቂት ማኅበራዊ ቅራኔ በመፍጠር ረገድ እጅግም ለውጥ አያመጣም። ብሔሮችና ብሔረሰቦች በራሳቸው ችግሮች አይደሉም። ችግሩ የሚፈጠረው ብሔሮችና ብሔረሰቦች የፖለቲካ መሣሪያ ሲሆኑ፤ ፖለቲካው የዘውግ ፖለቲካ ሲሆን ነው። ፖለቲካው የዘውግ ካልሆነ በርካታ ዘውጎች መኖራቸው ችግር አይደለም፤ እንዲያውም የተወሰኑ ጥቅሞች አሉት።

የዘውግ ፖለቲካ ሥር ከሰደደ ግን ቁጥር ዋጋ አለው። ለምሳሌ ኹለት እኩል ኃይል ባላቸው ብሔሮች የተገነባ አገር የዘውግ ፖለቲካውን ሚዛን ውስጥ ለማስገባት ጊዜ ላይፈጅበት ይችላል። ጥቂት ተመጣጣኝ አቅም ያላቸው ቡድኖች ያሉበት አገር ውስጥም የዘውድ ፖለቲካ እያለም ቢሆን ቡድኖች አቅማቸውን አውቀው ተቻችለው ሊኖረው ይችላሉ። እጅግ በርካታ እና ትናንሽ ከሆኑም ማናቸውም በግል አሸንፈው ማዕከላዊ መንግሥትን የመያዝ ህልም ስለማይኖራቸው ግጭቶች ከአካባቢ አልፈው ሀገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥሏት አይሆኑም። ችግሩ በመሀል ቤት ያለ አገር ላይ ይበረታል። ጥቂት ተመጣጣኝ አቅም ያላዳበሩ ጉልበታሞች እና በርካታ ጥቃቅን የዘውግ ቡድኖች ባሉበት አገር ውስጥ እያንዳንዱ ግዙፍ (ወይም ግዙፍ ነኝ ባይ) ከትናንሾቹ ሸሪክ ለማብዛት መጣሩ አይቀርም፤ እናም አገሪቷ የማያባራ መታመስ ውስጥ ልትገባ ትችላለች።

4. ጽንፈኛነት
ጽንፈኝነት የሚፈጠረው ማኅበረሰቡ ተራርቀው በተቀመጡ ጥቂት ብድኖች ሲሰባሰብ፤ እና በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ ‹‹እኛ አንድ ነን›› በሚል በአንድ ብሔር ውስጥ ያለን ልዩነት የማይታገስ እሳቤ ሲፈጠር እና ሌሎችን ሲያገል ነው። ይህ አገራችን ውስጥ እየበዛ የመጣ ችግር ይመስለኛል። እያንዳንዱ ብሔረተኛ በራሱ ብሔር ውስጥ ያለውን ልዩነት ለመታገስ አይፈልግም። በእሱ ብሔር ውስጥ ስላሉ ልዩነቶች ማንሳት በዚያ ብሔር ጠላትነት የሚያስፈርጅ ወቅት ላይ ደርሰናል። ‹‹እኛ መካከል ልዩነት የለም፤ አንድ ነን›› እያለ ቡድኑን በመላ ‹‹ሌሎች›› በሚላቸው ላይ ያነሳሳል።

5. የዘውግ ደህንነት አጣብቂኝ
የደህንነት አጣብቂኝ (security dilemma) በ1950ዎቹ ብቅ ያለ የአገሮች የውጭ ግንኑኝነት ንድፈ ሐሳብ ነው። አገሮች ሉዓላዊ በመሆናቸው እያንዳንዱ አገር የራሱን ደህንነት መጠበቅ የራሱ ግዴታ ነው። ከአገሮች በላይ ዳኛ የለም፤ በዚህም ምክንያት ይፈራራሉ። ለምሳሌ አንዱ አገር የራሱን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲል ወታደሮችን ያሰልጥናል፤ ዘመናዊ መሣሪዎችን ይታጠቃል። ይህን ማድረጉ ጎረቤቱ አገር በጥርጣሬ ሊመለከተው ይችላል፤ ወታደሮችን የሚያሰለጥነው፤ መሣሪያዎችን የሚያዘምነው በርግጥም ለመከላከል ብቻ ለመሆኑ በምን ማረጋገጥ ይቻለል? ይህ ጥርጣሬ ይኸኛው አገር ሌሎች ፕሮጀክቶቹን ትቶ ወታደሮችን ወደ ማሰልጠንና የውጊያ መሣሪያዎችን ወደ ማዘመን እንዲገባ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ የመጀመሪያውን አገር ስጋት ይጨምራል። ሳይፈልጉት እነዚህ አገሮች የመሣሪያ ውድድር ውስጥ ይገባሉ። ደህንነትን ለማረጋገጥ ተብሎ የተጀመረ ነገር የደህንነት ስጋት ይሆናል፤ ለዚህም ነው አጣብቂኝ (dilemma) የተባለው። እንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ አገሮች በትንሽ ግጭት ሰበብ ጦርነት ውስጥ የመግባት እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ከሶቭየት ኅብረት መፍረስ በኋላ የብሔር ቅራኔ ተመራማሪዎች ይኸ ንድፈ ሐሳብ ለብሔር ፓለቲከኞችም እንደሚሠራ አስተዋሉ። የብሔር ፖለቲከኞች ብሔራቸው ‹‹ከጥፋት ለማዳን›› ሚሊሻ ያሰለጥናሉ፤ በግልጽም በስውርም ‹‹ሕዝባቸውን›› ያስታጥቃሉ፤ ይህንን የሚያደርጉት ለደህንነታቸው ሲሉ ነው። ሆኖም ጎረቤት ብሔር ይህን በቸልታ አይመለከትም፤ ለመከላከል የተያዘ መሣሪያ ለማጥቃትም ይውላል። እሱም ራሱን የመከላከል ዝግጅት ያደርጋል። በብሔር፣ ብሔረሰቦች መካከል የመሣሪያ እሽቅድድም ይጀመራል። አንዴ እሽቅድድም ውስጥ ከተገባ መውጫው አሽቸጋሪ ነው።

የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት ከላይ ከተዘረዘሩ አራቱም ጠቃሚዎች ቢሆኑን በተለይ ‹‹የዘውግ ደህንነት አጣብቂኝ›› ልዩ ትኩረት የሚሻ ነጥብ ነው ብዬ አምናለሁ። በሌሎች አገሮች የሌለ ተጨማሪ እክል እኛ አገር ስላለ ይኸ አጣብቂኝ ከሌሎች በላይ እኛን አደጋ ላይ ጥሎናል። በሌሎች አገራት የሌለ እኛ አገር ያለው እክል ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ሉዓላዊ ሥልጣን የተሰጣቸው የክልል መንግሥታት መኖራቸው ነው።

ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በንቃት የሚሳተፉ የምጣኔ ሀብት፣ የሰላም፣ ቅራኔዎችና ዲፕሎማሲ ጥናቶች ባለሙያ ሲሆኑ ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ አገር፣ ለንደን ከተማ ነው። ታደሰን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here