የቢሃ ኮንስትራክሽን ሠራተኞች የአምስት ወር ደሞዝ አልተከፈለንም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ

ቢሃ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጀት በአዲስአበባ ሳይት ወይንም የግንባታ ቦታ የሚሠሩ ሠራተኞች የአምስት ወራት ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው ቅሬታቸውን ለአዲስማለዳ ገለጹ።
ቢሃ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በተለያዩ የግንባታ ቦታዎች የሚገኙ 150 ያህል ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ደሞዛቸው በአግባቡ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ድርጀቱ ግንባታ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ደውላ ለማረጋገጥ ችላለች።

ሠራተኞቹ በተለያዩ የግንባታ ቦታዎች ያልተከፈላቸው ደሞዝ ከአምስት እስከ ሰባት ወር እንደሚደርስ ገልጸው በአዲስ አበባ ከሚገኙት ኹለት የግንባታ ቦታዎች በአንዱ የሚሠሩ ሠራተኞች ከጥቅምት ወር ጀምሮ ደሞዝ አልተከፈለንም ብለዋል። ድርጅቱ ግንባታ እያከናወነ ካለባቸው ቦታዎች መካከል በጋምቤላ የሚሠሩ ሠራተኞች የስድስት ወር ደሞዝ አልተከፈለንም ሲሉ በአዲስአበባ ‘አስቱ’ የግንባታ ቦታ የሚሠሩ ሠራተኞች ደግሞ ሰባት ወር ሙሉ ደሞዝ አልወሰድንም በማለት ገልጸዋል።

ሠራተኞቹ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ እና ልጆች የሚያሳድጉ በመሆናቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል። ለአሠሪ መሥሪያቤቱ በተደጋጋሚ እንደጠየቁ ገልጸው የተሰጣቸው ምላሽ ድርጅቱ ከክፍያ መጓተት ጋር የተያያዘ ችግር እንደገጠመው ገልጸው እንዲታገሷቸው ከመንገር ውጭ ምንም አይነት መፍትሄ እንዳልሰጧቸው ተናግረዋል።

በተለይ በአንዳንድ የሥራ ቦታዎች 30 ያህል ቋሚ ሠራተኞች መኖራቸውን ተናግረው ግንባታ እየተጠናቀቀ ባለባቸው የግንባታ ሳይቶች ወይንም ቦታዎች ደግሞ የቋሚ ሠራተኞች ቁጥር እንደሚቀንስ ገልጸው ቋሚ ያልሆኑ የቀን ሠራተኞችም ቢሆን የሚከፈላቸው በወር ስለሆነ እንደ ደሞዝተኛ ይቆጠራሉ ብለዋል ክፍያ ለእነዚህ ሠራተኞችም አለመከፈሉን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የቢሃ ኮንስትራክሽን የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ገዛኸኝ ሙሀመድ ቢሃ ኮንስትራክሽን በዐስር የግንባታ ቦታዎች 150 ያህል ሠራተኞች እንዳሉት ተናግረው አሁን በገጠማቸው የገንዘብ እጥረት እና በክፍያዎች መጓተት ምክንያት ለሠራተኞቻቸው ደሞዝ መክፈል አለመቻላቸውን ገልጸው ችግሩ በቅርቡ ይፈታል ብለዋል።

ይህን ጉዳይ በሚመለከት የሕግ ምሑር የሆኑት ሔኖክ አሻግሬ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ላይ የተቀመጡ ግዴታዎች መኖራቸውን ገልጸው አዋጁ ላይ የአሠሪ እና የሠራተኛው መብት እና ግዴታ በግልጽ ተቀምጧ ብለዋል። አሠሪው እና ሠራተኛው በተዋዋሉት ውል መሰረት ክፍያዎች ሊፈጸሙ ይችላሉ ብለዋል።

የስምምነቱ ውል ላይ ክፍያው፣በአንድ ዓመት በሦስት ወር፣ በአንድ ወር፣ ከወር ባነሰ ጊዜ በሳምንት ወይንም በቀን ክፍያ ሊወሰን ይችላል አሠሪው ይህንን ካልፈጸመ ግዴታን እንደጣሰ ተቆጥሮ በሕግ እንደሚጠየቅ ገልጸዋል። ድርጀቱ ለሠራተኞቹ ደሞዝ ያልከፈለው መክፈል ሳይችል ቀርቶ ከሆነ በሕጋዊ መንገድ ማሰናበት ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን ሠራተኞቹ እራሳቸውን ከሥራ እንዲያሰናብቱ እንደማድረግ ይቆጠራል ብለዋል።

አሠሪው የተጣለበትን የመክፈል ግዴታ ካልተወጣ በሕጉ መሰረት ካሳ እስከመክፈል ድረስ ሊያስጠይቀው ይችላል ብለዋል። እንደ ዳኛው ሕግ የመተርጎም ችሎታ ሠራተኞቹ ደሞዛቸው በጊዜ ባለመከፈሉ ምክንያት ያጧቸው ነገሮች ከግምት ውስጥ ይገባሉ ለምሳሌ የሚከታተሉት ሕክምና እና የሚወስዱት መድሃኒት ካለ ደሞዛቸው በጊዜ ባለመከፈሉ ምክንያት ቢቋረጥ እንዲሁም የብሩ የመግዛት ዋጋ ዛሬ እና ከዛሬ አምስት እና ስድስት ወራት በኋላ ስለሚለያይ በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች አሠሪው ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል።
ሔኖክ ጨምረውም አንድ ሠራተኛ ሥራ ቦታው የመገኘት ግዴታ ያለበት ደሞዝ እስከተከፈለው ድረስ በመሆኑ እነዚህ ሠራተኞች የትራንስፖር እና ሌሎች ወጭዎች ስለማይኖሯቸው ከሥራ የመቅረት መብት አላቸው። እንዲሁም ሠራተኞች ተማረው ሥራ ቢያቆሙ ውሉ በሕገ ወጥ መንገድ እንደተቋረጠ ይቆጠራል በማት ገልጸዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here