105 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የሕክምና ቁሳቁሶች ለኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ተበረከቱ

0
1358

ከአንድ ወር በፊት ተመርቆ የሕክምና ቁሳቁስ በመጠባበቅ ላይ የነበረው የኮምቦልቻ ከተማ ጠቅላላ ሆስፒታል 105 ሚሊዬን ብር ወጭ የተደረገባቸው የሕክምና ቁሳቁሶች እና የፅኑ ህሙማን መታከሚያ (ICU) ልዩ አልጋዎችን United relief Service ከተሰኘ የአሜሪካን ድርጅት በእርዳታ መረከቡ ተገለጸ።

ጠቅላላ ሆስፒታሉ ጥር 7 ቀን 2013 ቢመረቅም በውስጡ 50 ያህል አልጋዎች ብቻ የነበረው ሲሆን የሕክምና ቁሳቁስ ባለመኖሩ ምክንያት አገልግሎት እንዳልጀመረ የከተማ ከንቲባ ከማል ሙሀመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል። አሁን በተገኘው ኹለት ኮንቴነር የሕክምና ቁሳቁስ በተጨማሪ ጂቡቲ ወደብ የደረሱና እየመጡ ያሉ ተጨማሪ የሕክምና ቁሳቁሶች መኖራቸውንም ከንቲባው አመላክተዋል። በእርዳታ ከተገኙት ቁሳቁሶች ውስጥ Ultrasound እና X-ray ማሽኖች መኖራቸው ታውቋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልል እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሆስፒታሉ ተመርቋል። ሆስፒታሉ በታቀደው ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ ኅብረተሰቡ ለነበረው ትዕግስት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላላ ሆስፒታሉ በ2004 ዓመተ ምህረት ተጀምሮ ከኹለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ለመጠናቀቅ ግን ዐስር አመት በላይ እንደወሰደበት እና እንደተጓተተ ፤ተገቢውን ሕክምና በአቅራቢያቸው ማግኘት እየቻሉ በግንባታው መጓተት ምክንያት ላላስፈላጊ ወጭ እንደተዳረጉ በዚህም ቅሬታ እንደነበራቸው አዲስ ማለዳ ያነጋረቻቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የሆስፒታል ግንባታውን ውል የወሰደው ስሪ ኤም (3M) ኢንጅነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሆን የሆስፒታሉ አጠቃላይ ግንባታ 178 ሚሊየን ብር ፈጅቷል።
በሌላ በኩል የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ከሮተሪ ክለብ ጋር በመተባበር ለኮምቦልቻ አጠቃላይ ሆስፒታል ግምታቸው ዘጠኝ ሚሊየን ብር የሚደርስ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል እቃወቹ ትላንት መጋቢት 3 ቀን 2013 በኮምቦልቻ አጠቃላይ ሆስፒታል ርክክብ እንዳደረገ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

ሆስፒታሉ አገልግሎት የሚሰጠው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ቃሉ ወረዳን ጨምሮ በቅርበት ካሉ የአፋር ክልል ወረዳዎች ጭምር ለሚመጡ ታካሚዎች እንደሆነ ተገልጿል። በሙሉ አቅሙ ወደ አገልግሎት ሲገባ 230 ያህል ሐኪሞች እና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች እንደሚኖሩት ታውቋል።

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ስር አራት መንግሥት ጤና ጣቢያዎች እና ስድስት ጤና ኬላዎች እንደሚገኙ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የኮሚኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያሳያል።
በኮምቦልቻ ከተማ ተገንብተው ከተመረቁ ሌሎች ፕሮጀክቶች መካከል 107 ሚሊየን ብር የፈጀው የኮምቦልቻ ከተማ የቄራ አገልግሎት ሲሆን በአንድ ቀን ኹለት ሺሕ በግ እና ፍየሎች እንዲሁም አንድ ሺሕ በሬዎች የማረድ አቅም እንዳለው ተገልጿል። ግንባታው በአገር አቀፍ ደረጃ ውጭ ምንዛሬ ይጨምራል ተብሏል ለ 107 ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የኮሚኒኬሽን ቢሮ ገልጿል።

ሌላኛው በዘጠኝ ሚሊየን 600 ሺሕ ብር ተገንብቶ የተመረቀው የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን ሲሆን ታንከሩ 100 ሜትር ኪዩቭ ውሀ የመያዝ አቅም እንዳለው እና የፕሮጀክቱ ጠቀሜታ በባቡር መንገድ ግንባታ ተነሽ ለሆኑ ኗሪዎች የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ለማድረስ ታቅዶ እንደሆነ ተገልጿል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here