ኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ ከተማ ልትገነባ እንደሆነ ተገለጸ

የትራንስፖርት ሚኒስቴር በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ ኢንዶዴ በተባለ ስፍራ የሎጂስቲክስ ከተማ እንደሚገነባ አስታውቋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባዘጋጀው የመጀመሪያው የትራንስፖርት ኢንቨስትመንት ጉባዔ ላይ እንዳለው አብረውት ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆኑ አልሚዎች ጋር በመሆን በ2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ በኦሮሚያ ክልል ኢንዶዴ በተባለ ስፍራ ለመገንባት ማሰቡን ተናግሯል።

ኢንዶዴ ከአዲስ አበባ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ስፍራ ስትሆን በገላን ቱሊዲምቱ የፍጥነት መንገድ የኹለት ደቂቃ የመኪና ጉዞን ብቻ የሚወስድ እንደሆነ የተገኘው መረጃው ያስረዳል።
ለፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር 3 ኪሎ ሜትር ስኩየር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን ለዚህም ካርታ መሠራቱን ተናግረው ነገር ግን ፕሮጀክቱ በሰፊው እንዲሠራ አብረው የሚያለሙ የቢዝነስ አጋሮች እንደሚያስፈልጉ ተገልጿል።
ግንባታውን ለማጠናቀቅ በቂ ይሆናል ተብሎ ከታሰበው 2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መካከል 50 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው በስፍራው በተገነባው ቀድሞ በተገነባው እና አገልግሎት እየሰጠ ባለው የባቡር ጣቢያ መስመር የተነሳ ቀድሞ እንደተሸፈነ እና በዚህም 50 ሚሊዮን ዶላር ውጪን እንደሚያድን ተገልጿል።

ይህ የሎጂስቲክስ ከተማ የሚገነባው ምቹ የሆነ ስፍራ ላይ በመሆኑ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ የሎጀስቲክስ ከተማ ይሆናል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም የሚያደርገው የማስፋፊያ ግንባታ በቅርብ ርቀት ላይ በመሆኑ ተመራጭ እንዲሆን ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
የፕሮጀክቱ ዲዛይን፣ግንባታ፣ለግንባታ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች፣ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ሁሉ በአገር ውስጥ የሚከወኑ መሆናቸው ተብራርቷል።
በሎጂስቲክስ ከተማ ውስጥ ይገነባሉ ተብለው ከታሰቡት ‹ፋሲሊሲስ › መካከል መጋዘኖች፣ የጭነት ማስተላለፊያ ሥፍራዎች፣የስብሰባ አዳራሾች፣የንግድ ተቋማት፣የትምህርት መስጫ ማእከላት የመኖሪያ ሕንፃዎች እና የመዝናኛ ቦታዎች እንደሚገኙበት ተቋሙ አስታውቋል።

እንዲሁም ለገቢ እና ለወጭ እቃዎች ማስቀመጫ የሚያገለግል ለኪራይ የሚሆኑ ስፍራዎች፣ ጥቅል የሆኑ እቃዎችን ለማድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች መቀመጫ እና ሌሎችም ከገቢ እና ከወጭ ንግድ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች መስጫ ስፍራዎችን በውስጡ እንደሚያካትት ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዓመት ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆን ትርፍ እንደሚገኝ እና ለኢንቨስተሮች ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚጫወተው ሚና ላቅ ያለ እንደሆነ በአጽኖት ተቀምጧል።
የትራንስፖርት ሚኒስትር መጋቢት 15 እና 16 በስካይ ላይት ሆቴል ባዘጋጀው የትራንስፖርት ኢንቨስትመንት ጉባዔ ላይ በ2022 ዓመተ ምህረት አስተማማኝ የተቀናጀ ዘመናዊና ደህንነቱ የተረጋገጠ የትራንስፖርትና የሎጀስቲክስ አገልግሎት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ በማድረግ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ የሚል ራዕይ በመሰነቅ የዘርፉን የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ በማጸደቅ ወደ ሥራ መገባቱን ሚንስተሯ ዳግማዊት ሞገስ ገልጸዋል።

አክለውም ዕቅዱም የሚሳካዉ የግሉንም ዘርፍ በስፋት በዘርፋችን በማሳተፍ በመሆኑ በብሔራዊ የትራንስፖርት ፖሊስና ሌሎች ስትራቴጅዎች በግልጽ የተቀመጠ በመሆኑ በቀጣይነት በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ለግሉ ባለሀብት ክፍት በሆኑ አማራጮች ላይ የፓናል ዉይይት ለኹለት ቀናት ተካሂዷል።

በትራንስፖርት ኢንቨስትመንት ጉባዔ መክፈቻ ላይ የተገኙት ክብርት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘዉዴ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ምንም ያህል በግብርናም ሆነ በማንኛዉም የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ እንደ አገር ስኬታማ ብንሆንም የትራንስፖርትና የሎጀስቲክስ ስኬት ካልታከለበት ዉጤታማ አንሆንም ብለዋል።

የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የትራንስፖርቱ ዘርፍ ማዘመን የትራንስፖርት መሠረተ ልማትና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት ማስፋፋትና የዘርፉን አቅም ማጎልበት ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ክብርት ፕሬዝዳንት የግሉ ባለሀብት ይህንን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም በትራንስፖርት ዘርፍ ባሉት የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ ለአገራችን የብልጽግና ጉዞ ስኬት የሚጠበቅባቸዉን ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here