የአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከሰባት በመቶ በታች በሆኑ የውጭ አገር ጎብኚዎች ብቻ መጎብኘቱ ተገለጸ

የአማራ ክልል በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 124 ሺሕ 382 የውጭ አገር ጎብኚዎች ክልሉን ይጎበኙታል ብሎ አቅዶ የነበረ ቢሆንም ሰባት ሺሕ 757 የውጭ አገር ጎብኚዎች ብቻ ክልሉን መጎብኘታቸውን የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው በስድስት ወራት ብቻ ክልሉን ከሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መጎብኘታቸው ገልጾ የህ ቁጥርም ስድስት ሚሊዮን 999 ሺሕ 975 የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ይጎበኛሉ ተብሎ ታቅዶ ከነበረው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ጎብኚ መገኘቱን የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢአለ ገልጸዋል።

ከዘርፉ 931 ሚሊዮን 191 ሺሕ 173 ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ 769 ሚሊዮን 586 ሺሕ 673 ብር ገቢ መሰብሰቡን ኀላፊው ገልጸው፣ የገንዘቡ መጠን የቀነሰው የጎብኚዎቹ ቁጥር ከታቀደው በታች በመሆኑ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ የጎብኚዎቹ የቆይታ ጊዜ አጭር መሆንና ሌሎች ምክንያቶች ለመሰብሰብ የታቀደውን የገንዘብ መጠን ዝቅ እንዳደረገው ተገልጿል።

የላልይበላ፣ የግሸን ማርያም፣ የተድባበ ማርያም፣ የጎዜ መስጂድ፣ የአንኮበር ቤተ-መንግሥት፣ የዘንገና ሐይቅ፣ የጭስ ዓባይ ፏፏቴ፣ የጣና ገዳማት፣ የጎንደር አብያተ-ክርስቲያናትና ቤተ-መንግሥታት፣ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እና መሰል ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ሀብቶች መገኛ የሆነው የአማራ ክልል የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው።

በአገራችን ብሎም በዓለማቀፍ ደረጃ የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክልሉ ይህን እምቅ ሀብቱን እንዳይጠቀም ማድረጉን አበበ ገልጸው፣ ያም ሆኖ ግን ክልሉን የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ከታቀደው በላይ ጎብኝተውታል ብለዋል። አክለውም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

በተለይም የውጭ አገር ጎብኚዎች በሚበዙባቸው የደባርቅና የላልይበላ ከተሞች ተፅእኖው የጎላ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ የውጭ አገር ጎብኚዎችን እንቅስቃሴ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስለገታው የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን መሠረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። የአገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲመጡ የተለያዬ ሁነቶችን መፍጠር አንደኛው መሆኑንም አበበ አንስተዋል።

ከሸዋ እስከ ወሎ በሚል በተዘጋጀ የመስህብ ጉብኝት፣ የግሸን ማርያም ክብረ በዓል፣ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች በዓል፣ የመርቆሪዮስ በዓል፣ የጥምቀት በዓል፣ የልደትን በዓል በላልይበላ፣ የዘራ ብሩክን በዓል በግሽ ዓባይና ሌሎች በዓላትና ሁነቶች የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ እንዲመጡ ያደረጉ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

በመስህብ ሥፍራዎች የኮሮና ቫይረስ መከላከል ፕሮቶኮል እንዲተገበር እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ኀላፊው፣ መመሪያውን በመተግበር ረገድ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ግን ጠቅሰዋል። ለጉብኝት የሚሄዱ ሰዎች ፕሮቶኮሉን በማክበር የተሻሉ ቢሆኑም በአካባቢው ማኅበረሰብ ያለው ግንዛቤ እና መዘናጋት መሻሻል አለበት ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣው መመሪያ ቁጥር 30/2013 ክፍል ኹለት የተከላከሉ ተግባራት እና የተጣሉ ግዴታዎች ቁጥር ሰባት ላይ ማንኛቸውም በሆቴል፣ በአስጎብኚነት እና በሌሎችም የቱሪዝም መስክ የተሰማሩ ተቋማት በሰራተኞቻቸው እና ተገልጋዮቻቸው መካከል ሁለት የአዋቂ እርምጃ ወይም የሁለት ሜትር ርቀት እንዲኖር የማድረግ፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን የመቆጣጠር፣ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮችን የማዘጋጀት ፣ ለሰራተኞቻቸው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ እንዲሁም የቱሪዝም አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ዘርፉ በመመሪያ የሚያስቀምጣቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለባቸው በማለት ደንግጓል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here