አጎዳ-ዮ ሜታል እና ሌላ ማይኒንግ ኢንርችመንት የተባለ የአገር ውስጥ የማዕድን አውጪ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በደቡብ ወሎ እና ምስራቅ ጎጃም ዞን ቦረና እና እነፍሴ ሳር ምድር ወረዳ በ ኹለት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በሚጠጋ በጀት የብረት ማዕድን ለማውጣት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
ድርጅቱ በሚቀጥሉት 60 ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ቶን ብረት ለማምረት ስምምነት ወስዷል ሲሉ የድርጅቱ መስራች እና ባለቤት መኳንንት አለሙ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ቁርጥራጭ ብረቶችን መተካት የሚችል ስፖንጅ የሆነ የብረት አይነት እያመረትን እንገኛለን በማለት ገልጸዋል።
ግዙፍ የሆኑ የብረት ማዕድን ማውጫ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት የሚጠይቀው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን የብረት ማእድን የማውጣት ተግባር ለመጀመር ከህንድ አገር የቴክኖሎጅ ልምዳቸውን በመውሰድ በመካከለኛ ደረጃ ሥራውን ጀምረናል በማለት፣ መኳንንት ገልጸዋል።
መኳንንት አክለውም ኢትዮጵያ በትልቅ ኢንደስትሪ ደረጃ የብረት ማዕድን ማውጫ መገንባት ይኖርባታል፤ ይህ ካልሆነ ብረት እና የብረት ምርቶችን ከውጪ አገራት ለማስገባት የምታወጣውን ገንዘብ ለማስቀረት አትችልመ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ድርጅቱ ከብረት ማዕድን ማውጫው በተጨማሪ በ600 ሚሊየን ብር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ካማሽ ወረዳ ድንጋይ ከሰል ለማውጣት እየሠራ ይገኛል። የድንጋይ ከሰሉ በደቡብ ወሎ እና ምስራቅ ጎጃም ዞን ቦረና እና እነፍሴ ሳር ምድር ወረዳ ለሚያወጡት የብረት ማዕድን ማቅለጫ እንደሚያገለግላቸው አስታውቀዋል። በቀጣይም ጥራቱን የጠበቀ የድንጋይ ከሰል ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለማቅረብ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም እንዲረዳቸው የድንጋይ ከሰል ለማጠብ የሚያስችል ማሽን በማስገባት ላይ እንደሆኑም መኳንንት ተናግረዋል።
አክለውም አንድ አገር እድገት ልታስመዘግብ ከምትችልባቸው መንገዶች አንዱ የሆነው የብረት ማዕድን ምርት በመሆኑ እና ብረትን እና የብረት ማዕድንን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የምናወጣው ወጭ ማስቀረት ከቻልን የምናስቀረው የውጭ ምንዛሬ ለሌላ ተግባር እናውላዋለን በማለት ገልጸዋል።
ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለአሥር ዋና ዋና የገቢ ምርቶች ከወጣው 90 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 53.5 ቢሊዮን ዶላር ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ውጤቶች መዋሉን እና ከዚህም ውስጥ 29.3 ቢሊዮን ዶላሩ ያለቀላቸው የብረታ ብረት ውጤቶችን ለማስገባት እንደዋለ ከብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ኢትዮጵያ ይህንን ያህል ገንዘብ ለምርት ብታውለው ኖሮ የብረት ማዕድን ከውጭ ከማስገባት በአገር ውስጥ ወደ ሚፈለገው ያለቀለት ምርት ለመወጥ የሚቻልበት፣ ከውጭ የሚገባው ምርት የሚቆምበት አቅም ይገነባ እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ቻይና የዓለምን ገበያ መቆጣጠር የቻለችበት፣ ጃፓን፣ ህንድ፣ እንዲሁም በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ የምትነፃፅረው ቬትናምም በዚሁ መንገድ ውጤታማ መሆናቸውን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንደሚቻል እና ከአፍሪካ አገራትም ውስጥ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ ያለፉበት ውጤታማ አካሄድ ለኢትዮጵያ መነሻ ሀሳብ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013



