በቀጣይ የትምህርት ዘመን በመላ አገሪቱ በሚገኙ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች የቴአትር ትምህርት ሊሰጥ ነው

በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የቴአትር ትምህርት በ 2014 ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህር እና የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዩ ገለጹ።
በአስራ አምስት የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ሲሰጥ የቆየው የቴአትር ትምህርት በሚቀጥለዉ ትምህርት ዘመን ደግሞ በሁሉም የክፍል ደረጃ ለሚገኙ ለመንግስትና ለግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደሚሰጥ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት እስቴቲክስ (ሙዚቃ ፣ ስእልና ስፖርት) ተብሎ ይሰጥ ከነበረዉ የትምህርት አይነት ባልተለመደ መልኩ የቴአትር ትምህርት ሊሰጥ የመፅሀፍ ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስተባባሪዉ ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ገልጸዋል።
የተዘጋጀው መጽሐፍ ለግል ትምህርት ቤቶች በሽያጭ መልክ የሚቀርብ መሆኑን የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች ደግሞ መንግስት በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ዋና አስተባባሪዉ አክለውም የቴአትር ትምህርት መጻሕፍት በጀትም በመንግስት እና በለጋሽ ድርጅቶች ወጪ መሸፈኑን ገልጸዉ፣ በአስተማሪነትም 3000 የሚጠጉ መምህራን እንደሚያስፈልጉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በዘርፉ የመምህራን እጥረት እንዳያጋጥም ከዚህ በፊት በሙያዉ ተመርቀዉ ወደ ስራ መስክ ያልተሰማሩትን እና በየክልሉ በሚገኙ በባህልና ቱሪዝም ስር ያሉትን ባለሙያዎች በሰዓት እንዲሰሩና በቀጣይም የሚመረቁ ተማሪዎች ወደ ስራዉ እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የትምህርቱ ዓላማ ተማሪዎች ከልጅነታቸዉ ጀምሮ የመግባባት ችሎታቸዉን እንዲገልጹ፣ ማመዛዘንና ማሰላሰልን እንዲያጎለብቱ፣ በጎ አስተሳሰቦችን እንዲያዳብሩ፣ በተፈጥሮ ያላቸዉን ድብቅ የጥበብ ችሎታቸዉ እንዲገልፁ፣በሰዉ ፊት የመናገር ችሎታቸዉን እንዲያዳብሩ ፣ከተፈጥሮ ጋር መግባባት እንዲችሉ፣ ቀና አስተሳሰብ እንዲኖራቸዉ፣ አገራቸውን እንድወዱ፣ ዉበትን እንዲያደንቁ፣ በሚያዩት ነገር ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸዉ ለማድረግ እና ብሎም የጥበቡን ዘርፍ ለማሳደግ ጭምር ያሰበ አንደሆነ ተገልጿል።
የቴአትር ትምህርቱ ሃሳብ የመነጨዉ በአዲሱ አጠቃላይ የትምህርት ፖሊሲ ክለሳ እና ቀረጻ ወቅት በተካሄደ ውይይት ላይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ባደረጉት ተፅእኖ ትምህርቱ አንዲሰጥ በመንግስት መወሰኑን ዋና አስተባባሪው አስረድተዋል።
በዚህ ትምህርት መጀመር ምክንያት በቴአትር ጥበባት ለተመረቁ ባለሙያዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

ትምህርቱ የተዘጋጀዉ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ሲሆን የክልል ትምህርት ቢሮዎች የተዘጋጀዉን ሞጁል(ማስተማሪያ) እንደመነሻነት በመዉሰድ፣ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በራሳቸው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ማዘጋጀት እንደሚችሉም ተገልፃል።
በመጽሐፍ ዝግጅቱ ላይም ከዘጠኝ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ የቴአትር፣ ስእል፣ ሙዚቃ፣ ፊልምና የስነ-ጥበብ መምህራን መሳተፋቸውን ረዳት ፕሮፌሰሩ አስታውቀዋል።

ማክሰኞ ሚያዝያ 05/2013 በሸራተን አዲስ ሆቴል በኢትዮጵያ ቴአትር የተጀመረበትን 100ኛ ዓመት አስመልክተዉ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ(ኢንጂነር) የቴአትር ትምህርት በልዩ ሁኔታ ለ11ኛ እና ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የሚሰጥ ሲሆን ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ዲፕሎማ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም እነዚህ ተማሪዎች የተለያዩ ስምንት ሙያዎች እንደሚማሩ እና ከእነዚህ ዉስጥም ቴአትር፣ ፊልም እና ሙዚቃ እንደሚገኙበት አዲስ ማለዳ መረጃዉን ሰምታለች።
ትምህርቱ በ2014 ሲጀመር በኢትዮጵያ በሚገኙ ከሃምሳ በላይ ከተሞች እንዲሁም ለትምህርቱ ግብአት በተሟላባቸው አካባቢዎች እንደሚጀመርና ቀስበቀስም የሚያስፈልጉ ነገሮችን በክልል ካሉ አስተባባሪዎች ጋር በመነጋገር እና በማሟላት በመላዉ አገሪቷ እንደሚዳረስ አስታዉቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here