ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪስ (ICL) ከትግራይ ክልል ጤና ቢሮ እና ከመቐለ ሆስፒታል ጋር በመተባበር እና ከጤና ሚኒስቴር እና ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ጋር በመሆን በትግራይ ለሚገኙ 50 ሺሕ ለሚደርሱ ሰዎች ለአንድ ዓመት የሚቆይ የኮቪድ 19 ምርመራ ዘመቻ በነጻ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ምርመራው በመቐለ ዓይደር ሆስፒታል፣እንዲሁም በግል ሆስፒታሎች እና በክሊኒኮች ጭምር እየተደረገ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ዜና እስከተሠራበት አርብ ሚያዝያ 15 ድረስ 300 ያህል ሰዎች የኮቪድ 19 ምርመራ እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል።
አንድ ዓመት የሚቆየው ዘመቻ በክልሉ ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ፣ የሕመም ምልክት ያለባቸው፣ እንዲሁም ሕጻናት እና ሴቶች ላይ የበለጠ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ በኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪስ (ICL) የኦፕሬሽን እና አድሚን ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሲስትር አጸደ ካሀሊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሯ የጤና ሚኒስቴር በክልሉ ማዳረስ ያለበትን ሌሎች ሥራዎችን እንዲሰራ ለማገዝና እርዳታ ለማድርግ በማይችልባቸው አጠቃላይ በአገር ውስጥ ባሉ ቦታዎች 130 ሺሕ ምርመራዎች በነጻ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ሲስተር አጸደ ተናግረዋል።
ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪስ (ICL) በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ ኮሮና ምርመራ የሚያደርጉ ኹለት መኪኖችን ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እና በስራ ላይ ለማዋል ከውጪ መኪኖቹ እስከሚመጡ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ሲስተሯ ገልጸዋል። የኮቪድ ወረርሽኝ ጠፍቶ ወደ ቀደመ ህይወታችን ከተመለስን መኪኖቹን ለጤና ሚኒስቴር በስጦታ እንደሚያበረክቱም አሳውቀዋል።
በአዲስአበባ እና በክልል ዋና ዋና ከተሞች በተዘረጉ ከ45 በላይ የናሙና መሰብሰቢያ ጣቢያዎች የኮቪድ-19 ምርመራን እያከናወነ የሚገኘው ይህ ተቋም፣ ኮቪድ 19ኝን ለመመርመር 790 ብር እንደሚያስከፍል ከተቋሙ ፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ተቋሙ ኮቪድ 19 ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ አዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ተፈናቃይ የሆኑ ዜጎች ባሚገኙባቸው ቦታዎች የኮቪድ 19 ምርመራ በነጻ እያደረገ እንደሚገኝ እና በቀጣይ ብዙ ኢንዱስትሪዎች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ የኮቪድ ምርመራ ለማድረግ ማቀዱን ሲስተር አጸደ ተናግረዋል።
ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪስ (ICL) ከ2004 ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ አገልግሎት መስጠትን አላማ አድርጎ እየሠራ የሚገኝ ተቋም ነው። በአገራችን ባሉ ከተሞች በጂማ፣ በባህርዳር ፣በአዲስአበባ ፣በደሴ፣ ድሬዳዋ እና ሐረር አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ላቦራቶሪ ነው።
የጤና ሚንስትር ዶክትር ሊያ ታደሰ በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ በመቐለ ጠቅላላ ሆስፒታል መጋቢት አራት ቀን ተገኝተው የኮቪድ 19ኝን ክትባት በመከተብ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው። መቐለ ከተማ በተደረገው የክትባት ማስጀመሪያ ስርኣት ወቅት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር ሙሉ ነጋ (ዶክተር) ፣ ያለንበትን ችግር እንድንቋቋምና የኮሮና ቫይረስ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ይህ የክትባት መርሃግብረ በክልላችን መጀመሩ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ ክትባቱን በወቅቱ መከተባቸውም የሚታወስ ነው።
በትግራይ ክልል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ጤና ተቋማት ወደ አገልግሎት መስጠት እየተመለሱ እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል። የመድሀኒትና ግብአት ስርጭት ተደርጎ ወደ ሥራ የገቡ ጤና ተቋማት 88 የደረሱ ሲሆን፣ በአምስቱም ዞኖች በአጠቃላይ ካሉት 40 ሆስፒታሎች ውስጥ 15 ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ እና አምስት ሆስፒታሎች በከፊል አገልግሎት እየሰጡ ነው። ካሉት 224 ጤና ጣቢያዎች 68 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አክሎ ያሳያል።



