200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የመርካቶ የብዙኀን ትራንስፖርት ተርሚናል ግንባታው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተጠናቆ በሚቀጥለው ሳምንት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አረጋዊ ማሩ ገልጸዋል።
በ2010 ግንባታው የተጀመረው የመርካቶ የብዙኀን ትራንስፖርት ተርሚናል አሁን 99 ነጥብ 4 በመቶ ተጠናቋል ሲሉ አረጋዊ አሳውቀዋል። የብዙኀን ትራንስፖርት ተርሚናሉ በአንድ ጊዜ 20 አውቶቡሶችን ለማቆም እና ለማስተናገድ የሚያስችል የራሳቸው መግቢያ እና መውጫ ያላቸው ኹለት ወለሎች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል።
በቀን 50 ሺሕ ለሚደርሱ ተሳፋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ እና በውስጡ የትኬት መቁረጫ እና የተሳፋሪዎች ማረፊያ እንዳለው ገልጸዋል። አክለውም በዋናነት የአውቶቡስ መጠበቂያ ቦታ፣ የተሳፋሪ መጫኛና የማራገፊያ ቦታ ያሉት ሲሆን፣ ዘመናዊ ስምሪት አገልግሎትን ጨምሮ የአውቶብስ መርሃ-ግብርና የአስተዳደር ቢሮዎችንም አካቷል ብለዋል።
በ4,125 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ይህ ተርሚናል በአንድ ሰዓት 6 ሺሕ ለሚጠጉ የብዙኀን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ታውቋል። የግንባታው ወጭ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደተሸፈነም ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እና በስሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት ባቀረቡት የዘጠኝ ወር ሪፖርት ላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስራ የጀመሩት የሸጎሌ እና የቃሊቲ የከተማ አውቶቡስ ዲፖዎች ከ99 በመቶ በላይ መጠናቀቁ እና ከግንባታው ተቋራጭ ርክክብ መደረጉ ተነግሯል።
ዲፖዎቹ የቀራቸው የጋራዥ እና ሌሎች የመለዋወጫ እቃዎች መግጠም እንደነ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል። ዲፖዎቹ ለከተማ አውቶቡሶች መቆሚያ፣ ነዳጂ መቅጃ እና ማደሪያ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ ከ250 እስከ 300 ድረስ አውቶቡሶችን ለማቆም የሚችሉ ስፍራዎች እንደያዙም ተገልጿል።
በዲፖዎቹ አውቶብሶችን በኹለት ደቂቃ ውስጥ ማጠብ እና ማድረቅ የሚችል ማሽን እንደተገጠመ፣ እንዲሁም በአንድ ጊዜ 19 ለሚሆኑ አውቶብሶች ቀላል የሆነ ጥገና የሚያደርጉ ጋራጆች መኖራቸውንም ከአዲስአበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በቢሮው ሪፖርት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የትራፊክ ቅጣትን ለመሰብሰብ የተዘረጋውን አሰራር በመጠቀም 652 ሺሕ 913 የትራፊክ ድንብ ጥሰቶች በሲስተም ማስተናገድ የተቻለ ሲሆን፣ 1 ሺሕ 378 አሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ የተለያዩ ጥፋቶችን በማጥፋት የተመዘገበው ነጥብ ከ 17 እስከ 21 በመሆኑ ለሶስት ወር መንጃ ፍቃዳቸው እንደታገደባቸው ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ብርሃኑ ግርማ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በመተግበሩ የትራፊክ ስርአትን የማክበር ተግባሩ መሻሻሉን ጠቁመው፣ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚከሰተው ሞት ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ቀንሷል ብለዋል።
በተለይ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 ተግባራዊ በመሆኑ፣ በከተማዋ በትራፊክ ግጭት የሚደርሰውን ሞት እና ጉዳት ለመቀነስ አስተዋፅኦ አበርክቷል ሲሉ ምክትል ዳሬክተሩ ገልጸዋል።
በሪፖርቱ ከቀረቡት ሌሎች ተግባራት ውስጥ ለከተማዋ ትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ መንስኤ የሆነውን የተሽከርካሪ ማቆሚያ እጥረትን ችግር ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ጋር በተያያዘ፣ በተለይ የህንፃ ስር ፓርኪንግ ቦታዎች አጠቃቃም ላይ ተገቢውን ፍተሻ እና ቁጥጥር ማድረግ የተጀመረ ሲሆን፣ በከተማዋ ለፓርኪንግ የተለዩ ቦታዎች እና ክፍት ቦታዎችን በአግባቡ ለፓርኪንግ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዘጠኝ ወራት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን፣ የበጀት እጥረት፣ የግብዓት እንዲሁም የአንዳንድ አገልግሎቶች አሰጣጥ መመሪያዎች እና ስታንዳርድ የሌላቸው መሆኑ የገጠሙ ችግሮች ተብለው ተጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013



