የመኪና ኪራይ ለከፍተኛ ወጪ እንዳደረገዉ ኤጀንሲዉ አስታወቀ

የመስክ መኪና እጥረትን ለመፈታት  የኪራይ መኪኖችን መጠቀሙ ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረገዉ የከፍተኛ ትምህርት  ጥራትና አግባባነት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡  የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና  አግባብነት ኤጀንሲ ከገጠሙት የተለያዩ ችግሮች መካከል  የመስክ መኪና ጉዳይ አንዱ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ በላከዉ የዘጠኝ ወር ሪፖርቱ ገለጸ፡፡ ኤጀንሲዉ  ከተመሰረተ ከ1995 ጀምሮ የመስክ መኪኖች ችግር እንደረበት እና እስካሁንም እንዳልተቀረፈለት ይናገራል፡፡   ችግሩንም ለመፍታት ተቋሙ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን የኤጀንሲዉ የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተሩ ታረቀኝ ገረሱ ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ማህበራት ስር  ያሉትን መኪኖች በጨረታ በማወዳደር ለከተማ ውስጥ በትንሹ በቀን ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ብር(2200) በማዉጣት  እንደሚከራይ ተቋሙ ገልጻል፡፡ በአዲስ አበባና ቅርብ ከተሞች በቀን 5 እና 6 የሚሆኑ የኪራይ መኪኖችን ለመስክ ስራ እንደሚልክ ተገልጻል፡፡ ከ2008 ጀምሮ ተቋሙ  ለመስክና ለቢሮ አገልግሎት  የሚዉሉ መኪኖች እጥረት  መኖሩን  በመገንዘብ ሰራተኞች ለመስክ ምልከታ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሲሄዱ መኪኖችን በኪራይ መልክ እንዲጠቀሙ  ማድረጉን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ከ2011 በፊት ከ10 በማይበልጡ እዉቅና ሰጪ ተቋም የሰዉ ሀይል ይንቀሳቀስ እንደነበረና አሁን ላይ የሰዉ ሃይሉን 42 ማድረሱን ከተቋሙ የተገኘዉ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ የሰዉ ሀይል መጨመር የእዉቅና ፍቃድ በሚጠይቁ ተቋማት ላይ የጊዜ መጓተትን የሚቀንስ ቢሆንም፣ የመኪና እጥረቱን ግን እንዲባባስ ማድረጉ ተገልጻል፡፡ አሁን ላይ ኤጀንሲዉ 15 መኪኖች ሲኖሩት፣ ከእነዚህ ዉስጥም ለመስክ ስራ የሚሰማሩት አስራ አንዱ ብቻ ናቸዉ፡፡ የተቀሩት 4ቱ የሃላፊዎችና የዳሬክተሮች መሆናቸዉ ታዉቋል፡፡ ኤጀንሲዉ ያለዉ የመስክ መኪና እና የመስክ ሰራተኞች አለመመጣጠኑ ደግሞ ተቋሙን ለተጨማሪ ችግርና ወጪ እየዳረገዉ ነዉ፡፡

ኤጀንሲዉ በአለም አቀፍና አገር አቀፍ ደረጃ  የተከሰተዉ የኮሮና ቫይረስ ወርሽኝ ምክንያት የመስክ ስራዎቹን  በሚፈለገዉ ደረጃ ለማወከናወን አለመቻሉን አሳዉቋል፡፡ በዚህም  የኤጀንሲዉ ስራዎች እንዳይቋረጡ በሚል  ባለሙያዎች  ከቤታቸዉ ሆንዉ የሚሰሩበትን መንገድ ሲያመቻች መቆየቱንም  ተናግሯል፡፡  የግድ  ቢሮ መግባት  ለሚኖርባቸዉ ሰራተኞችም ኤጀንሲዉ ተገቢዉን ድጋፍ እና ጥንቃቄ  አድርጎላቸዉ ስራቸዉን  በጥንቃቄ  መሥራታቸዉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡   ኤጀንሲዉ ካለበት የመኪና እጥረት በተጨማሪ የገጠሙትን የተለያዩ ተግዳሮቶችን  ይፋ አድርጓል፡፡  ተቋሙ ሲቋቋም ከነበረበት  አደረጃጀት አለመሻሻሉ፣ በኤጀንሲዉ  የአደረጃጀት  ክፍተት ምክንያት በተቋማት ላይ የተደራጀና ቀጣይነት ያለዉ  ክትትልና ግምገማ  በሚፈለገዉ ደረጃ አለማከናወኑንም በዘጠኝ ወር ሪፖርቱ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ያሉበትን የመኪና እና የተለያዩ ችግሮች ለመቅረፍም የተለያዩ መፍትሄዎችንም  ለመዉሰድ ሞክራል፡፡ ሆኖም ግን ተቋሙ ያለበትን የመኪና እጥረት ለመፍታት የሄደበት ርቀት ለሌላ ኪሳራ እየዳረገዉ መሆኑም ተገልጻል፡፡ የኤጀንሲዉንም አደረጃጀት ለመቀየር  አዲስ የመዋቅር ጥናት በማጥናት  በኤጀንሲዉ ቦርድ ጸድቆ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በኤጀንሲዉ ብዙ ትኩረትን የሚሹ ስራዎችም መሰራት እንዳለባቸውም ተመላክቷል፡፡ በቀጣይም ተቋሙ ስር ነቀል ለዉጥ  ለማምጣት የኤጀንሲዉ አደረጃጀት ጥናትን አጸድቆ  ስራ ላይ እንዲዉል እንደሚሰራ አስታዉቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኤጀንሲዉ  በህገ- ወጥ ተቋማት ላይ የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገዉ አገራዊ እርብርብም ላይ  ኤጀንሲዉ የበኩሉን ለመወጣት እንደሚሰራ ነዉ ያሳወቀው፡፡ ሌላዉ ተቋሙ ሊሰራ ካቀዳቸዉ ነገሮች መካከል የሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ  እንዲጣራላቸዉ በቀጣሪ መስሪያቤች የሚቀርብ ጥያቄን  በክፍያ  የሚሰራበትን አሰራርም ለመዘርጋት ተዘጋጅቷል፡፡  ኤጀንሲዉ ከዚህ በፊት የነበሩበትን ድክመቶችና ተግዳሮቶች በቀጣይ ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ማቀዱን አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲዉ ባገኘችዉ መረጃ ለማወቅ ተችላል፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here