በስድስት ክልሎች እና በኹለቱ ከተማ አስተዳደሮች ባለፉት አምስት ዓመታት በ 2 ሚሊየን 710 ሺሕ 130 ሰዎች ላይ በተደረገ የደም ግፊት ምርመራ በ 306 ሺሕ 331 ሰዎች ላይ ከፍ ያሉ የደም ግፊት ንባቦች ተመዝግበዋል ሲሉ ነብዩ ኃይለማርያም የ‹ኸልዚ ኸርት አፍሪካ› የኢትዮጵያ ኃላፊ ተናግረዋል።
ኸልዚ ኸርት አፍሪካ(HHA) ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በሐረሬ፣ በደቡብ እና በሲዳማ ክልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ባደረገው ጥናት፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ንባቦች ከተመዘገቡባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ አብዛኛዎቹ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ እንደሆነ ታውቋል።
ኸልዚ ኸርት አፍሪካ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በየዓመቱ ግንቦት 17 ቀን የሚከበረውን የዓለም የደም ግፊት ቀን ምክንያት በማድረግ ከጤና ሚኒስቴር እና ፖፑሌሽን ሰርቪስስ ኢንተርናሽናል (PSI) ጋር በጋራ በሰጠው መግለጫ ላይ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመዘገቡ ሞቶች 39 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ ተብሎ እንደሚገመት የዓለም የጤና ድርጅትን ሪፖርትን ዋቢ አድርጎ ገልጿል።
ከነዚህ መካከል 16 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በልብ እና የደም ቧንቧ ህመም ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ መሆኑ ተነግሯል። በአገራዊ “STEPwise” የዳሰሳ ጥናት የኢትዮጵያ የበሽታ ሸክም ላይ ትንበያ የሰጠ ሲሆን፣ 95 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች ላይ አንድ ወይም ኹለቱ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የመያዝ እድል እንደነበራቸው ተገልጿል። ለበሽታው ባህሪያዊ መንስኤዎች የተባሉት የፍራፍሬዎች እና አትክልቶች ዝቅተኛ አወሳሰድን ጨምሮ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ አለመኖር፣ ከመጠን በላይ አልኮል መጠቀም፣ ትምባሆ መጠቀም እና ከመጠን በላይ ውፍረትን እንደሚያካትት በጥናቱ ተጠቁሟል።
የዚህ ዓመት የዓለም የደም ግፊት ቀን መሪ ቃል ‘የደም ግፊትዎን በትክክል ይለኩ፣ ይቆጣጠሩ፣ ረዥም ዓመት ይኑሩ’ የሚል ሲሆን፣ በእድሜ የገፉ እና የልብ እና የደም ቧንቧ ህመም የመሳሰሉ ስር የሰደዱ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች፣ በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) መሰረት፣ በከፋ የኮቪድ-19 ህመም የመታመም እድል እንዳላቸው ተገልጿል።
የደም ግፊት ወይም ከፍ ያለ የደም ግፊት ሳይታወቅ የሚገድል ነው። ምክንያቱም ምንም ምልክት አያሳይም። ስለዚህ፣ በጊዜ መመርመር እና ባህሪያዊ መንስኤዎችን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም መንግሥት ትምባሆ እና አልኮል የመሳሰሉ ጤናማ ያልሆኑ ምርቶች ላይ ግብር የመጨመር ፖሊሲዎችን እየተገበረ ነው። ስለ ደም ግፊት እና መንስኤዎቹ እውቀት ለመፍጠር ሚኒስቴሩ ሄልዚ ኸርት አፍሪካን ከመሳሰሉ የፈጠራ ፕሮግራሞች ጋር በመተባበር ይሰራል በማለት ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ገልጸዋል።
የአስትራዜኒካ ኸልዚ ኸርት አፍሪካ ፕሮግራም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 የተጀመረ ሲሆን፣ ዓላማውም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተጀመረውን የደም ግፊት ስርጭትን የመግታት እና በኢትዮጵያ መንግሥት የሚካሄደውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ብሄራዊ የትግበራ ዕቅድ ስልት መደገፍ ነው።
ኼልዚ ኸርት አፍሪካ የአስትራዜኒካ የፈጠራ ፕሮግራም ሲሆን፣ የደም ግፊትን ማለትም ከፍ ያለ የደም ግፊት ንባብ እና በአፍሪካ እየጨመረ የመጣውን የልብ እና የደም ቧንቧ በሽታ ለመከላከል እየሠራ ይገኛል። ይህን ለማሳካት የደም ግፊት ምልክቶች እና መንስዔዎች ላይ እውቀትን በመጨመር፣ እንዲሁም ትምህርት እና ምርመራ፣ ተገቢ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ህክምናና ቁጥጥርን በማከናወን የአካባቢ የጤና ሥርዓቶችን ይደግፋል። ፕሮግራሙ በምስራቅ እና በምዕራብ አፍሪካ እየተሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013



