በዓለም አቀፍ የቱሪስት ፍሰቱ ላይ የኮሮና ወረርሽኝ ያደረሰው ተጽእኖ እየተጠና መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አለማየሁ ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከወረረሽኑ ጋር በተያያዘ ያጣችውን የምጣኔ ሀብት ገቢን በሚመለከት የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ጥናት እያደረገበት በመሆኑ ውጤቱ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ ከጎዳቸው የሥራ መስኮች መካከል ቱሪዝም መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ለጥናቱ የሚያግዙ የተለያዩ መረጃዎችን ለኮሚሽኑ መላካቸውንም አስታውቀዋል።
በወረርሽኙ ምክንያት የዓለም አቀፍ ጎብኚዎች አሉ የምንልበት ደረጃ ላይ አይደለም ሲሉ ዳሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ያጣችውን የገቢ መጠን ለማወቅ ጥናቱ ሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በወረርሽኙ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የጉዞ እገዳ የጣሉ አገሮች በመኖራቸው እንቅስቃሴው እንዲስተጓጎል ምክንያት መሆኑ ታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ወደ ተለያዩ አገሮች ብዙ ተጓዦች እንዳይገቡና እንዳይወጡ በመደረጉ የቱሪዝም ፍሰቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ መጎዳቱ ተነግሯል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ጎብኚዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ የመጡበት ዓላማ ለስራ እና ለንግድ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ገቢው እንዳልቆመ ቢታወቅም ዋነኛው የገቢ ማግኛ መንገድ ግን የማስጎብኘት ስራ ነው ብለዋል።
ለጉብኝት ብለው በመሰረታዊነት የሚመጡ ጎብኚዎች አለመኖራቸውን የነገሩን አለማየሁ፣ ይህ ቢሆንም ግን የቱሪዝም ዘርፉ ሙሉ በሙሉ አልተጎዳም ብለዋል። ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ደንበኛ ቢቀንስባቸውም በከተሞች አካባቢ የሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎች አገልግሎት በመስጠት ገቢ እያገኙ ነው። ይህ ማለት ግን በወረርሽኙ የተጎዱ ሆቴሎች የሉም ማለት እንዳልሆነ ተነግሯል። የሆቴልና የቱሪዝም መስኩን ለመደገፍ መንግሥት በአነስተኛ ወለድ(5%) ብድር መፍቀዱን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ የብድሩ ዓላማ በዘርፉ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ታስቦ ነው ብለውናል።
በተለይ በቱሪዝም ዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ሠራተኞቻቸው እና አገልግሎቶቻቸው ከወረርሽኑ በኋላ ባሉበት እንዲቀጥሉ ለማድረግ መሆኑም ተነግራል። በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማትም ወረርሽኙ የፈጠረውን የሥራ ክፍት ጊዜ በመጠቀም ለማኅበር አባላቶቻቸውና ለሌሎችም በዘርፉ ለተሰማሩ የሙያ በቃት ደረጃን ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ መሆናቸውንም ሰምተናል። የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንዲጨምር ያደርጋል ከተባለው ስልጠና በተጨማሪ፣ ተቋማቱ የኢንተርኔት መረብን በመጠቀም ከወርርሽኙ በኋላ ወደፊት የተሻሉ አሰራሮችን ለመከተል የሚያሥችሏቸውን ሥራዎችን በመቅረጽ ላይ ናቸው ተብሏል።
ከዚህ በፊት ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲያዩና እንዲያሻሽሉም እድል መፈጠሩንም ዳሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን፣ በዚህ ወረርሽኝ ወቅት በርካታ ሆቴሎችና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችም እድሳት ላይ መሆናቸው ታውቋል። ለአብነትም በጥያ ትክል ድንጋይ የወዳደቁ ትክል ንጋዮችን የማንሳት፣ የሳር ተከላ፣ የፈሳሽ ማስወገጃ ፣የአጥር እና ለጎብኚዎች ማረፊያ የሚሆኑ መቀመጫዎች መስራት ከእድሳቶቹ መካከል እንደሚጠቀስ ተገልጻል። ወረርሽኙ የዓለም አቀፉ የቱሪዝም ፍሰት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩ እንዳለ ሆኖ፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴው የተሻለ ነው ተብሏል። መንግሥት ከወረርሽኙ ጋር ተያያይዞ የተለያዩ ክልከላዎችን ቢያደርግም ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን ተከትሎ ሕብረተሰቡ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ይገኛል። በእነዚህ የአገር ውስጥ እንቅስቃሴዎችም ያልተጠበቀ የአገር ውስጥ የቱሪዝም ገቢ መገኘቱን አለማየው ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከወረርሽኑ ጋርም በተያያዘ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሰው ሀይል በሚበዛባቸው ክፍሎች ሰራተኞች በፈረቃ እና በቤታቸው እንዲሰሩም እያደረገ መሆኑንም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል። የዓለም አቀፍ ቱሪዝሙ እስከ 2012 ድረስ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ እንደነበረ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሜኒኬሽን ዳሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013



