ለዓመታት ሥራ ያቆመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከ370 ሚሊዮን ብር በላይ ለሠራተኞች ከፍሏል

0
1280

በአፋር ክልል አሳኢታ ወረዳ የሚገኘው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከኹለት ዓመታት በላይ ምንም አይነት ምርት እየሰጠ ባይሆንም ከ7 ሺሕ ለሚበልጡ ጊዜያዊ ሠራተኞቹ በየወሩ ክፍያ እንደሚፈጽም እና ለዚህም 378 ሚሊየን ብር ወጭ ማድረጉን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያሳያል። ስኳር ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ምርት መስጠት ካቆመ ከኹለት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም በፋብሪካው ሲሠሩ ለነበሩ ጊዜያዊ ሠራተኞች ግን አሁንም በየቀኑ የሚታሰብ ከ40 እስከ 45 ብር ክፍያ እየፈጸመ እንደሚገኝ በፋብሪካው ቋሚ ያልሆኑ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይህ ክፍያ በወር እና በዓመት ሲሰላ 378 ሚሊየን የሚጠጋ ብር ወጭ መደጉን ያመላክታል።

ፋብሪካው 2 ሺሕ ያክል የድርጅቱን ቋሚ ሠራተኞች ወደተለያዩ የስኳር ፋብሪካዎች ማዘዋወሩንም ሠራተኞቹ ገልጸዋል። የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት ውስጥ በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት የሚሠሩ ሠራተኞች የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች እንዲሁም የሸንኮራ አገዳ ተመርቶ ፋብሪካው ሳይገነባ በፊት በስፍራው በነበረው የጥጥ እርሻ ይሠሩ የነበሩ ጭምር መሆናቸውን ገልጸዋል። ሀብት ንብረት አፍርተው የሚኖሩ ቋሚ ሠራተኞች ራቅ ባሉ ቦታዎች ወዳሉ የስኳር ፋብሪካዎች መዘዋወራቸው ሌላ ቅሬታ ማስነሳቱንም ሠራተኞቹ ገልጸዋል። የስኳር ፋብሪካው ሲገነባ ለሠራተኞች መኖሪያ ተብለው በተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ዛሬም ድረስ የሚኖሩ የድርጅቱ ሠራተኞች እንዳሉም አስተያታቸውን የሰጡ ሠራተኞች ገልጸዋል።

አሁን በተንዳሆ የስኳር ፋብሪካ የአገዳ እርሻ በነበረበት ስፍራ ላይ ስንዴ እየተዘራበት እንዳለም የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ስንዴው የሚዘራው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በግለሰቦች እንጂ የእርሻው ባለቤት በሆነው መንግሥት እንዳልሆነም አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በፋብሪካው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ደሞዝ በወቅቱ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ እና ችግር ውስጥ እንደወደቁ በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር ማሳሰባቸውን በአስተያየት ሰጭዎቹ ተገልጿል። ለስኳር ፋብሪካው አገዳ እርሻ የተገነባው የመስኖ ግድብ ከልክ ሲያልፍ ለአካባቢው ነዋሪዎች የጎርፍ ስጋት እንደሆነም ነዋሪዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሥር ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚውል 21 ሺሕ ሔክታር ይዞታ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ይዞታ ላይ ለምቶ የነበረ የሸንኮራ አገዳ ተክል በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በቤት እንስሳት ተበልቷል። የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ1998 ሥራው ለህንዱ ‹ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አላየንስ› በይፋ ተሰጥቶ ግንባታው ቢጀመርም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በታሰበው መንገድ መሄድ ሳይችል ቀርቶ ግንባታው መጓተቱ የሚታወስ ነው። በኹለት ምዕራፎች የተከፈለው ይህ ፕሮጀክት የመጀመርያው ምዕራፍ 13 ሺሕ ኩንታል፣ ኹለተኛው ምዕራፍም 13 ሺሕ ኩንታል፣ በድምሩ 26 ሺሕ ኩንታል ስኳር በቀን የማምረት አቅም እንደሚኖረው በወቅቱ ተነግሮ ነበር።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ፕሮጀክት በ1998 ተጀምሮ በጥቅምት 2007 ቢጠናቀቅም፣ ፋብሪካው የቴክኒክ ችግር ስላጋጠመው፣ ከዚሁ ጋርም ፕሮጀክቱ ረዥም ጊዜ የወሰደ በመሆኑ በ2007 ባጋጠመው ድርቅ ምክንያት የሸንኮራ አገዳው ለከብቶች መኖ እንዲውል ተደርጓል። በወቅቱ በድጋሚ ልማት በ2010 ወደ ምርት እንደሚገባ ቢገለጽም ፋብሪካው እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ምርት የማምረት ሙከራ እንዳላደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በሐምሌ 2011 የሰራችው ዘገባ ላይ የተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ለግድብ፣ ለቤት ፕሮጀክቶችና ለእርሻ ልማቱ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት እንደነበርና 232 ሚሊዮን ዶላር የውጭ እዳ እንዳለበት ተዘግቦ ነበር፡፡ ካለ ሥራ በየወሩ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለደሞዝ ክፍያ ወጪ ማውጣቱ አገራዊ ኪሳራ እንደሆነም በዜናው ተካቷል።
ከላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ወደ ስኳር ኮርፖሬሽን ስልክ የደወልን ቢሆንም፣ ኮርፖሬሽኑ ለሁሉም የመገናኛ ብዙኃን በቅርቡ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here