የስፖርታዊ ዉርርድ ማቋመሪያ ፍቃድ መሰጠት ቆመ

0
1047

የስፖርታዊ ዉርርድ(ቤቲንግ) ፍቃድ ለጊዜዉ መስጠት ማቆሙን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ቴዎድሮስ ነዋይ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የእግር ኳስ ቤቲንግ(ቁማር) ከ2012 ግንቦት ጀምሮ መስፋፋቱን እና በርካታ ሰዎች ወደ ውርርዱ እንዳዘነበሉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የተለያዩ ስፖርታዊ ዉድድሮች ላይ በተለይም የእግር ኳስ ላይ በዉርርድ ገንዘብ በማስያዝ የሚካሄድ ቁማር መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሕብረተሰቡ ቅሬታዎች እና ትችቶች በሰፊው እየቀረቡ መምጣታቸዉን ቴዎድሮስ ነዋይ ተናግረዋል።

አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥናቶች አካሂዶ የስፖርታዊ ዉርርድ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ አስኪያደርግ ድረስ ለጊዜዉ የቤቲንግ ፈቃድ እንደማይሰጥ ገልጿል። ከስፖርታዊ ዉርርዱ ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ ለአስተዳደሩ እንደ ችግር ካቀረባቸዉ ዉስጥ፣ ወጣቱ ወደ ጨዋታዉ በስፋት መሰማራቱ፣ተማሪዎች ጊዜያቸዉን በቤቲንግ ማጥፋታቸው፣ የገንዘብ አያያዝ ስርአቱ ትክክል አለመሆን እና በአንዳንድ ቦታዎችም የሕገ-ወጥ የቤቲንግ መጫወቻ ቤቶች መከፈትን ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ሕብረተሰቡ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቁጥጥር ማነሱን ጨምሮ የተለያዩ በርካታ ቅሬታዎችን አንስቷል።

በ2012 የቤቲንግ ፍቃድ የተሰጣቸዉ 42 ደርጅቶች መሆናቸውን አስታዉሰዉ፣ ዘንድሮም ፈቃድ የጠየቁ በርካታ እንደነበሩ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የቁማር ጨዋታዉ ጥንቃቄ እና ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ መጀመሪያ ብሔራዊ ሎተሪ ማሻሻያዎችንና ችግሮችን መቅረፍ እንዳለበት አመላክቷል። ከብሔራዊ ሎተሪ ፍቃድ ወስደዉ በሥራዉ ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙ የቤቲንግ አቋማሪ ድርጅቶች በበኩላቸዉ ቁጥጥር እንዳለና እድሜያቸዉ ከ18 አመት በታች የሆኑ ልጆች እንዳይገቡ ማስታወቂያ መለጠፋቸውን አታውቀዋል። ወደ ስፖርታዊ ዉርርዱ ለመጫዎት የሚመጡ ራሳቸዉን የሚያዉቁና አስበዉበት የሚያደርጉት ነገር በመሆኑ ለችግር እንዴት ሊጋለጡ ይችላሉ ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውርርድ ቁማሩ በተለይም የወጣቱን ህይወት በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል ብለዋል። የአንዳንዶችን የትዳር ህይወት ጭምር እየጎዳ እንደሚገኝ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። ወጣቱ ሥራና ትምህርቱ ላይ ጊዜዉን ማሳለፍ ሲኖርበት በቁማር ጨዋታ ጊዜዉንና ገንዘቡን ማባከን እንደሌለበትም ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል። ይህ ቤቲንግ የተባለው የዉርርድ ቁማር ወጣቶችን ለስርቆትም ሊዳርጋቸዉ እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፣ የእግር ኳስ ዉድድር እና ትንበያዎች ላይ ወጣቱ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀሱ የሥራ ባህላችንን ያበላሻል እንዲሁም የግለሰቡን ኢኮኖሚ ይጎዳል ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጠቁመዋል።

የዚህን የስፖርታዊ ዉርርድ(ቤቲንግ) ሁኔታ ብሔራዊ ሎተሪ ፍቃድ ከመስጠቱ በፊት ሊያስብበት ይገባ ነበር መባሉንም አዲስ ማለዳ ከአስተያየት ሰጪዎች ሰምታለች። የሕብረተሰቡን ስጋትና ቅሬታ ተረድቻለሁ ያለው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር፣ በስፖርታዊ ዉርርዱ(ቤቲን) ዙሪያ የተለያዩ ማሻሻዮችን በማድረግ እና ችግሮችን በመቅረፍ በድጋሜ ፍቃድ መስጠት እንደሚጀምር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ቴዎድሮስ ነዋይ ገልጸዋል። በሌላ በኩል አስተዳደሩ የ10 ወር ሪፖርት ማቅረቡን ለአዲስ ማለዳ ያሳወቀ ሲሆን፣ በሪፖርቱም የተለያዩ ችግሮች ገጥመዉት እንደነበር አስታዉቋል። በዚህም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ተጽእኖ፣ የጸጥታ ችግር በነበረባቸዉ አካባቢዎች የሎተሪዎች አለመሸጥ፣ የአንዳንድ ሎተሪ ትኬቶች ቶሎ ታትሞ አለመድረስና ገበያ ላይ አለመገኘት እንደችግር ተጠቅሰዋል። ከነዚህ በተጨማሪም በየቦታዉ የሕገወጥ የእድል ጨዋታ(ቁማር) መስፋፋቱ ችግር ሆኖ እንደነበር አስተዳደሩ በሪፖርቱ አሳዉቋል።

ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በ2013 የበጀት አመት 10 ወራት ውስጥ ከሎተሪ ሽያጭና ፈቃድ ከሚሰጣቸው የእድል ጨዋታዎች 801.9 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ዳይሬክተሩ አስታዉቀዋል። አምና ከነበረዉ ገቢ ሲነጻጸር በ147 ሚሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ በበጀት አመቱም 193.2 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘት መቻሉ ተገልጻል።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here