በሱማሌ ክልል በ170 ሚሊዮን ብር ወጪ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ሊገነባ ነው

በሱማሌ ክልል 170 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ሊገነባ መሆኑን የመገናኛ ብዙኃኑ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ አሊ በደል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም የነበሩት የክልሉ መገናኛ ብዙኃን በርካታ የሚጎድሏቸው ነገሮች እንዳሉ የጠቀሱት የቦርዱ ሰብሳቢ፣ በዋናነት መገናኛ ብዙኃኑ በቂ የሠራተኛ መሥሪያ ክፍሎች (production room) እና የአመራር ቢሮዎች የሌላቸው ሲሆን፣ የኮምፒውተር እጥረት እና መሰል አስፈላጊ ነገሮች የሚጎድሏቸው በመሆኑ አዲስ ለመገንባት ዋነኛ ምክንያት እንደሆናቸው አስረድተውናል።

ባለፉት በርካታ የድርጅቱ የጉዞ ዓመታት ከውጭና ከውስጥ፣ ከጊዜና ከአቅም ጋር ተያይዘው የገጠሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ የሕዝብ ድምፅ በመሆን ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። የክልሉ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ሙሐመድ በክልሉ የመገናኛ ብዙሃኃን ድርጅት ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደነበሩ ባደረጉት ጉብኝት መመልከታቸውን ዋና ሰብሳቢው ገልጸዋል። አያይዘውም የቴሌቭዥን ጣቢያው ጥራት ያለው ዜናና ዜና-ነክ ፕሮግራሞችን ለአድማጭ ተመልካቹ እንዲደርስ ለማድረግ የማስፋፊያ ግንባታው ፕሮጀክት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህንንም ዓላማ ከግብ ለማድረስ በ170 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲስ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ክልሉ እንደሚገነባ ነው ያስረዱት። ፕሬዝዳንቱ ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ሦስት ዓመታት የመገናኛ ብዙኃን ለክልሉ ብሎም ለአገሪቱ ምን ያህል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው በመታወቁ፣ አቅጣጫ በማስቀመጥ እና ውይይት በማድረግ እንዲሁም በክልሉ ቴሌቭዥን ጣቢያ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ማስፋፊያ ማድረግ ማስፈለጉን ጠቅሰዋል። ለዚህም የመገናኛ ብዙኃኑ የቦርድ አባላት እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ብዙ ውይይትና ምክክር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ ወይም የህንጻ ግንባታው ባለ አንድ ፎቅ መሆኑን ያነሱት የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ፣ ይህም ከዚህ ቀድሞ የነበረውን የመሥሪያ ቢሮዎች እጥረት የሚቀርፍ ሲሆን፣ ከዚህም ባለፈ ህንጻው ሰፊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የሥርጭት መቆጣጠሪያ ክፍል (control room) የተለያዩ ዘመናዊ ስቱዲዮች፣ ካፍቴሪያዎች እና መናፈሻ ቦታዎች ይኖሩታል ብለዋል። አሁን ላይ የህንጻ ግንባታው መጀመሩን አንስተው፣ በሚቀጥሉት ኹለት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ህንጻው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስረድተዋል።

ይህንን ፕሮጀክት ለማስጀመር በጄት ትልቅ ማነቆ እንደነበር ሰብሳቢው ገልጸው፣ አሁን ላይ ከብዙ ዓመታት በፊት ታቅዶ የነበረውን ግንባታ እውን ለመሆን መቃረቡ እንዳስደሰታቸው አመልክተዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታ በአገር በቀል ኮንትራክተሮች ይከናወናል ያሉት አሊ፣ በተያዘው ጊዜ በፍጥነት አጠናቀው እንደሚያስረክቡ ኮንትራክተሮቹ መስማማታቸውን አንስተዋል። የሱማሌ ክልል መገናኛ ብዙኃን የቦርድ ሰብሳቢው አሊ በደል የቴሌቪዥን ጣቢያው እያከናወነ የሚገኘው የለውጥ ሥራ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፣ የክልሉ መንግስት የጎላ ድጋፍ እንዳይለየው አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here