የሕብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ያቀረበውን የኩባንያውን ካፒታል ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የማሳደግ ዕቅድ ባለ አክሲዮኖች ውድቅ ማድረጋቸውን እና አጀንዳው ለቀጣይ ዓመት እንዲዘዋወር መወሰኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት ሙሉአለም ብርሃኔ እንደገለጹት፣ ካፒታሉን ማሳደግ ከተፈለገባቸው ዋናዋና ምክንያቶች አንዱ የሆነው በብሔራዊ ባንክ የውጪ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚፈቅድ መመሪያ ቢወጣ፣ በአሁኑ ሰዓት ኢንሹራንሱ ካለው አቅም አንጻር የውጪ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ የተሻለ ካፒታል ይዘው እንደሚገቡ ከግምት ውስጥ በማስገበት፣ ካፒታሉን ከፍ ለማደረግ ታቅዶ እንደ ነበር ጠቁመዋል።
“ኢንሹራንሱ በሕንጻ እና በንብረት በተለይም በቦሌ እና ቃሊቲ አካባቢ ባሉት ሕንጻዎች እና በሌሎችም ሀብት ያካበተ ቢሆንም፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ንበረቶች ማከማቻ ቦታ ያስፈልገናል” ሲሉ ሙሉአለም ብርሃኔ ገልጸዋል። ለዚህም ኢንሽራንሱ የተጎዱ ንብረቶች ለማከማችት የሚያገለግል የራሱ ይዞታ ስለሚያስፈልገው ካፒታሉን ማሳደግ አስፈልጎታል ተብሏል።
የሕብረት ኢንሹራንስ ሰኔ 30/2013 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያገኘው ትርፍ ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 169.9 (15 በመቶ) ሚሊዮን ብር ዕድገት ማስመዝገቡ ተገልጿል።
ከሦስት ዓመታት በፊት በተካሄደው የአክስዮን ባለደርሻዎች ስብሰባ ላይ፣ የኩባንያውን የተከፈለ ካፒታል ግማሽ ቢሊዮን ብር ለማድረስ የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ባሳለፍነው የበጀት ዓመት የኢንሹራንሱ ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል ብር 473.4 ሚሊዮን ከ 501 ባለአክሲዮኖች ማደረስ መቻሉ ታውቋል። በአሁኑ ሰዓት የኩባንያው ሀብት 1.8 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።
ስማቸው አንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢንሹራንሱ ባለ ድርሻም በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ ኹኔታ መዋዕለ ነዋይን ለማፍሰስ የሚጋበዝ አይደለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። “ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣው መመሪያ ኢንዱስትሪውን የሚገነዘብ ባለሙያ እንደሌለው የሚያመለክት ነው” ሲሉም ባለድርሻው አክለዋል።
በተጨማሪም፣ ከሰሞኑ ያስተላለፈው መመሪያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከገቢያቸው ላይ እስከ 15 በመቶ በሚደርስ ወጪ የልማት ባንክን ቦንድ እንዲገዙ የሚያዝ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ በሙስና እና በተበላሸ ብድር ስሙ የተበላሸውን ልማት ባንክ ያቀረበውን ቦንድ እንዲገዙ ትዕዛዝ መስጠት ተገቢ አለመሆኑን ለአዲስ ማለደ ገልጸዋል።
ከስድሳ ዓመት በላይ በኢንሹራነስ ሙያ ላይ ያገለገሉት እና የሕብረት ኢንሹራንስ መሥራች እየሱስወርቅ ዛፉ ከባለ አክሲዮኑ ሐሳብ ጋር ከሞላ ጎደል እንደሚስማሙ ገልጸው፣ “ነገር ግን ዋናው ችግር በማዕከላዊ ባንክ ውስጥ የተሰገሰጉት ነገር ግን፣ እውቀት የጎደላቸው ባለሙያዎች ውሳኔ ኢንዱስትሪውን እየጎዳው ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አክለውም፣ ካፒታል ለማሳደግ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የብር ምንዛሬ እየቀነሰ መምጣት የኩባንያው የአረቦን ገቢ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፣ ለጠለፋ መድን ዋስትና የሚሰጠው ወይንም በኩባንያው አቅም የሚያስቀረው የሽፋን መጠን ዕድገት ጋር የተመጣጠነ ካፒታል አቅም እንዲኖረው ለማስቻል ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል።
የሕብረት ኢንሹራንስ የተመሰረው በ1994 በ87 ባለድርሻዎች፣ በስምንት ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እና በ25 ሚሊዮን ብር ካፒታል ነበር። በ2002 ከቀድሞው አንበሳ ኢንሹራንሽ ጋር በፈጠረው ጥምረት የባለ አክሲዮኖችን ብዛት ወደ 318 አሳድጎ፣ ካፒታሉንም ወደ 250 ሚሊዮን ብር ከፍ ማድረግ መቻሉ ይታወሳል።
ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014



