ሰኞ ጥር 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሸኔ አምስት ተማሪዎችንና አንድ በንግድ ሥራ የሚተዳደር ግለሰብን ጨምሮ በድምሩ ስድስት ሰዎችን በኦሮሚያ ክልል ማገቱን የፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ ላይ፤ ታጋቾቹ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ሲጓዙ ምስራቅ ወለጋ ጎቡ ሰዮ ወረዳ ልዩ ሥሙ ባፋኖ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ጥር 15 ቀን 2014 ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ በሽብር ቡድኑ ታፍነው መወሰዳቸውን አመልክቷል፡፡
በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የህወሓት ቡድን ጋር በመቀናጀት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሽብርና ትርምስ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱት የሸኔ ቡድን ታጣቂዎች በፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እና በኦሮሚያ ፀጥታ አካላት በቅንጅት እየተወሰደባቸው ባለዉ እርምጃ እየተደመሰሱ መሆናቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
ይሁንና የተበታተኑት የቡድኑ አንዳንድ ኃይሎች በየዋሻውና ጥሻው በመደበቅ በንፁሃን ላይ እንዲህ አይነት አስነዋሪ አፈናና እገታ መፈፀማቸውን ነው የጋራ ግብረ ሀይሉ በመግለጫው ያመለከተው፡፡
የፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ከኦሮሚያ ክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ታጋቾችን የማስለቀቁ እንቅስቃሴም እየተካሄደ በመሆኑ፤ እርምጃዎችን ተከትሎ የሚገኘውን ውጤት በቀጣይ ለህዝቡ እንደሚያሳወቅ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
_
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



