‹ወጣት የነብር ጣት› በአገራችን የተለመደ ብሂል ነው። ወጣትነት የብርታት፣ የትጋት፣ የያዙትን አጥብቆ ይዞ የመዝለቅና የጥንካሬ አምሳል ሆኖ ይሳላል። አንድ አገር እድገትን እንድታስመዘግብ ከሚያስፈልጓት መካከልም ይህ የወጣት ኃይል አንዱ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አዳጊና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥራቸው በአብዛኛው በወጣት የተውጣጣ አገራትም የወጣቶችን አዲስ ሐሳብ እንዲሁም ብርቱ ጉልበት ለእድገታቸው አብዝተው ይሻሉ።
የዛሬዋ እንግዳችን ወጣት ሰላማዊት ዓለሙ ወጣትነታቸውን በትጋት እያሳለፉ ከሚገኙት መካከል ትገኛለች። ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪክ ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። የ26 ዓመቷ ወጣት ሰላም፣ በሲፒዩ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የማርኬቲንግ ትምህርት በዲግሪ መርሃ ግብር የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ነች።
በአሁኑ ሰዓት በዓመት ኹለት ሚሊዮን ብር ካፒታል የደረሰ ‹ፊደል ቲቶሪያል› የተሰኘ ተማሪዎችንና አስጠኚዎችን የሚያገናኝ ድርጅት አላት። እንዲሁም ለወላጅ አባቷ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ‹ዓለም ማርኬቲንግ ኤንድ ፕሮሞሽን› በሚል የሰየመችው 50 ሺሕ ብር ዓመታዊ ገቢ የሚያስገኝ ድርጅት መሥርታለች። በሥራ ፈጠራዋም የኢፌዴሪ ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የሥራ ፈጠራ ክህሎት ውድድር ላይ ከነበሩ አሸናፊዎች መካከል ተገኝታለች።
ወጣቷ ሥራ ፈጣሪ ሰላማዊት ዓለሙ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ባደረገችው ቆይታ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም ወጣትነትና ሥራ ፈጠራን በተመለከተ ለተነሱላት ጥያቄዎች መልሶችን ሰጥታለች። መልካም ንባብ!
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ባለመረጋጋትና ሰላም ማጣት ውሰጥ መቆየቷ ይታወቃል። ይህን እውነት እያወቁ የራስን ሥራ አቋቁሞ መሥራት ምን ይመስላል? ስጋት ተሰምቶሽስ ያውቃል?
አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከባድ መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ይህ ያልፋል፤ አገር ግን ይቀጥላል። እኛም ትምህርት ላይ እንደሚሠራ ተቋም ነገ አገርን የሚረከብ ሰው እናፈራለን ብለን፣ ነገን ተስፋ በማድረግ ነው እየሠራን ያለነው።
ግን አዎን ስጋት ይኖራል። አገር አለመረጋጋት ውስጥ ስትሆን ሥራ ለመሥራትም ያስቸግራል፤ የሥራ እንቅስቃሴም ይቀንሳል። ትንሽ ረብሻ ሲነሳ ልጅ ያለው ቤተሰብ ላይ ጭንቀት ነው የሚፈጥረው። እኛም በዚህ የተነሳ በተለያየ አጋጣሚ ሥራችን ቀንሶ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ከእኛ ጋር ግንኙነት ያቋረጡና አገልግሎት ማግኘት ያቆሙ ወላጆች ነበሩ፣ ሁኔታው በሥራችን ላይ ብዙ ተጽእኖ ነበረው።
ምን ቀን ነው ይህን ሥራ የጀመርኩበት ብዬ ባልማረርም፣ አስጨናቂ ጊዜያት ግን ነበሩ። ምክንያቱም እኛ ሥራ እንድንሠራ ደንበኞቻችን ያስፈልጋሉ፣ ለዛ ደግሞ አገሪቱ ሰላም ያስፈልጋታል። እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲፈጠሩ፣ ደንበኛ ሲቀንስ እኛም ላይ እንደ ቢሮ የሚደርስብን አሉታዊ ተጽእኖ አለ። ከዚህ ውጪ ግን እንዳልኩት ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል በሚል ነው የተረካቢ ትውልድ ጉዳይ ላይ እየሠራን የምንገኘው።
በቅርቡ ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ አገራት ወደ አገራቸው መጥተዋል። የሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማራችሁ ወጣቶች ከዳያስፖራዎች ጋር የተገናኛችሁባቸው መድረኮች ነበሩ። ምን ውጤት ተገኘ? ቀድማችሁ የጠበቃችሁት ነገርስ ነበር?
አዎን! ከዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው መምጣት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ክዋኔዎች ተካሂደው ነበር። አንደኛው በአሁኑ ሰዓት ካሉ ችግሮች ጋር በተያያዘ ሂልተን ሆቴል የተደረገ ፕሮግራም ነበር። በዛም ከዳያስፖራው ጋር ክህሎትን ከማሳደግ አንጻር ወጣቶች ላይ የሚሠሩ ከውጪ የመጡ እንዲሁም በአገር ውስጥ ያሉ በዘርፉ ላይ ከሚሠሩት ጋር ያለውን የትምህርት ሁኔታ እንዴት እናሻሽል፣ ሥራ አጥነትን እንዴት እናስተካክል፣ ያለውን የትምህርት ሥርዓት እንዴት ማሻሻል ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ነበሩ። የተለያዩ ጥሩ ሐሳቦች ተነስተዋል፤ ልምዶችን ተለዋውጠናል። እነርሱ የነበሩበት አገር ያለውን ልምድም አካፍለዉናል።
ሌላው ፍሬንድሺፕ የተዘጋጀው ክዋኔ ነው። በዛም ክዋኔ ላይ ኢንቨስተሮች ተጠርተው የኢፌዴሪ ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን በተገኘበት፤ አገልግሎቱን እንድናስተዋውቅ የሚያስችል፣ ኢንቨስተሮች ከእኛ ጋር በጋራ ሊሠሩ እንዲችሉ እንዲሁም የሚያግዙበትን መልክ በተመለከተ መድረክ አዘጋጅቶልን ነበር።
እንደ ፊደል ቲቶሪያል በኦንላይን የኢትዮጵያን ቋንቋና ታሪክ ማስተማር የምንችልበት አውድ (ፕላትፎርም) ፈጥረን ነበር። ያንን ለማስተዋወቅ ትልቅ መድረክ ነው የሆነልን።
በዛው መድረክ የተለያየ የተሰጠን ምክረ ሐሳብ ነበር። በተለይ ከመጡበት አገር ላይ አገልግሎቱ በምን ዓይነት መንገድ እንደሚሰጥ እና የምናሻሽልበትን መንገድ አመላክተውናል፤ መዋዕለ ነዋያቸውን ፈሰስ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችም አናግረውናል።
በመድረኩ ላይ በብዛት የተገኘነው ጀማሪ ድርጅቶች ነበርን። በዛም የገንዘብ ድጋፍ የሚፈልግ፣ በሐሳብም መደገፍ የሚፈልግ ነበር አብዛኛው። እናም ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ፣ ድርጅቶቹ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት እንዲታወቁና የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽንም ድርጅቶቹን የሚያግዝበት መንገድ እንዲሁም ለቀጣት አዳዲስ ነገር እንድናይ የእውቀትና የኢንቨስትመንት እድል የነበረው ነው። ለእኛም አዲስ የወጪ ማርኬት ያገኘንበት ነበር።
ከዳያስፖራው መምጣት ጋር ከዚህ የተለየ የጠበቅነው ነገር ብዙም አልነበረም። ዳያስፖራው ሲመጣ አንድ ያገኘነውና ያሰብነውም የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል ውጪ ላለው ሰው እናስተምር ነው። ውጪ ያሉ ልጆቻቸው አማርኛ መናገር የማይችሉ ብዙ ሰዎች አሉ። እናም የእኛ ሐሳብ በቋንቋቸው እናስተምራቸው የሚል ነበር። ከወላጆቻቸው ጋር አብረው የመጡ ልጆች አገራቸውን፣ ቋንቋና ባህልን የማያውቁ ከሆነ ይወቁ የሚል ሐሳብ ነው የመጣልን፤ ምላሹም ጥሩ ነበር።
ወጣትነትና ሥራ ፈጠራን እናንሳ። አንዳንዶች ወጣቱ እድል አላገኘም ወይም አልተሰጠውም ሲሉ ሌሎች ደግሞ እድል አለ ግን ወጣቱ አልተጠቀመበትም ብለው ይሟገታሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለሽ?
እድል አሁን ነው እየተከፈተ ያለው የሚል ዕይታ ነው ያለኝ። አሁን ከሥራ ፈጠራ ጋር የተገናኙ ብዙ ማእከላት እየተከፈቱ ነው፣ ሥራና እድል ፈጠራ ኮሚሽንም ይህን በጣም እያበረታታ ነው። በየጊዜው ሥራ ፈጣሪዎችን እያወዳደሩና ለሥራ መነሻ ገንዘብም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን እየሰጡ ሥራ እንዲጀምሩ እያደረጉ ነው።
አሁን እድሉ አለ። እንደውም ወጣቱ በደንብ እየተጠቀመ ነው። በፈት እንዲህ ያለ እድል የነበረ አይመስለኝም። እኛም ከዚህ በፊት ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከማስተር ካርድ ጋር በጋራ ባዘጋጀው ውድድር ላይ ተዋዳድረን፣ አሸናፊ የሆንንበት ትልቅ እድል አግኝተን ነበር። እና በእኔ እምነት እድሉ አለ፤ ብዙዎችም እየተጠቀሙበት ነው።
ከሥራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ አሁንም የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ። አሁን ያለው እድል በቂ ነው ወይ? መንግሥትስ ምን ሊያግዝ ይገባል ትያለሽ?
እድሉ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ በመንግሥት በኩል መሠራት ያለበት ነገር አለ። አንደኛው ጀማሪዎችን የሚያበረታታ ሕግ የለም ነው። በቅርቡ በ100 ቀናት የሚጸድቅ ሕግ ተብሎ ነበር። በዚህም እንደ ሐሳብ እስከ 6 ወር ድረስ አንድ ጀማሪ ግብር እንዳይከፍል፤ ራሳቸውን ማቋቋም እንዲችሉ ማገዝ ነው። እንዲህ ያሉ ሕጎች በተለያዩ አገራት አሉ። ይህ እኛ ጋር አልተተገበረም። እኛም በዚህ የተቸገርንባቸው ቦታዎች ነበሩ።
ፈቃድ ከማውጣት አንጻር ወጣቶች አዳዲስ ሐሳቦችን ይዘው ሲነሱ ዘርፉ ራሱ የንግድ መመሪያ ላይ የማይኖርበት አጋጣሚ አለ። ይህ ሊሠራት ይገባል። ተበረታቶ በጊዜና በፍጥነት ሥራን የመጀመሩ ነገር ይኖራል። አዲስ ሐሳብ ነውና ማስለመዱ በጣም ከባድ ነው። እሱን ነው ለብዙ ሰው የሚከብደው፤ ሥራውን እስኪጀምሩ።
ቢሮ ተከራይቶ፣ ሠራተኛ ቀጥሮ ማስጀመሩ ብቻ ሳይሆን ቀጣይ እንዲሆን ነው። ብዙ ጀማሪ ድርጅቶች ለምሳሌ ከአንድ ዓመት በላይ አይቆይም። አንድ ዓመት ከስድስት ወር ካለፈ ግን በደንብ ሥራ ሠርቶ ትርፋማ ሆኖ ማኅበረሰቡን መጥቀሙ ከዛ በኋላ ነው የሚመጣው። ብዙ ድርጅት ከአንድ ዓመት በላይ አይዘልቅም። ይህ ደግሞ ከድጋፉ አንጻር ነው። መሥሪያ ቦታዎች ቢመቻቹ፣ ለጀማሪዎች እንደሌላው ንግድ ሳይሆን የተሻለ የግብርና ቀረጥ ገቢ ሕጎች ጋር በተገናኘ ይጸድቃል የተባሉ ቢስተካከሉ፣ ብዙዎች እንዲወጡና አዳዲስ ሐሳብ ይዘው ስኬታማ እንዲሆኑ ያስችላል።
ዋናው መጀመሩ ሳይሆን ምን ያህል ሄዷል፣ ምን ያህል ሰው ተጠቅሟል፣ ምን ያህል ሥራ ፈጥሯል፣ ማኅበረሰቡ ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ አምጥቷል የሚለው ስለሆነ መንግሥት ጀማሪ ድርጅቶችን የሚያበረታታበት ሕግ ወጥቶ ቶሎ ቢጸድቅ እላለሁ።
ኢትዮጵያ ብዙ ወጣት ኃይል አላት። ግን ብዙ የሰው ኃይል እንዳለው አገር ውጤታማ እንመስላለን?
እንደዛ አይደለንም። የሰው ኃይል እንዳለው ብንሆን ኖሮ ብዙ ችግሮችን ይፈቱ ነበር ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ወጣት መኖሩ ዋናው አዲስ ሐሳብ አምጥቶ የማኅበረሰቡን ችግር መፈታት መቻሉ ነው። እንደ አገር በጣም ብዙ ችግሮች አሉ፣ ግን አገሪቱ ወጣት ካላት ሐሳብ አምጥቶ ችግሩን መፍታት የሚችሉ መሆን አለባቸው። እሱ ላይ ምንም አልተሠራም።
በቅርቡ በአንድ ስብሰባ ላይ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ሲወጡ ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት ተደርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘ እኛ ለዩኒቨርሲቲዎች ያቀረብነው አንድ ፕሮፖዛል አለ። በዛም ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ እያሉ ማኅበረሰቡን ያገልግሉ የሚል ነው። በዛ መካከል የሚያዩት የማኅበረሰቡ ችግር በራሱ ዓይናቸውን ይከፍተዋል። ስለዚህ ትምህርት ጨርሰው ሲወጡ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግና ማኅበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ ሆነው ይወጣሉ።
በቅርቡ ቶታል ኢነርጂስ ያዘጋጀው ውድድር እንዳለና ፊደል ቲቶሪያል በዛ ተሳታፊ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ውድድሩ ምን መልክ አለው? ድርጅታችሁስ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
ውድድሩ በቶታል ኢነርጂስ የተዘጋጀ ነው። በሦስት ዘርፍ ነው ውድድሩ። አንደኛው ከሦስት ዓመት በታች ያሉ የንግድ ሐሳቦች ነው። ሁለተኛው ሴት የሥራ ፈጣሪዎች ሲሆን ሦስተኛ ደግሞ አዲስ ሐሳብ ወይም በደንብ የሥራ እድል እና ተጽእኖ መፍጠር የሚችል ፕሮጀክት ነው።
እንደ ፊደል ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት በንግድ ላይ የቆዩ ድርጅቶች እንዲሁም በሴት የሥራ ፈጠራ ባለሞያ ዘርፍ ላይ ተወዳድረናል። በዚህም ኹለት ዙር አልፈን አሁን የሕዝብ ድምጽ ነው እየሰበሰብን ያለነው። ሰዎች ድምጽ እንዲሰጡን ቅስቀሳ እያደረግን እንገኛለን። ይህም እስከ ጥር 24 ይቆያል። በዚህ አሸናፊ ከሆነን የተለያየ ሽልማት፣ ሥልጠና እንዲሁም የሚድያ ሽፋን የማግኘት እድላችን ይሰፋል። ደግሞም እናሸንፋለን ብለን እናምናለን።
ፊደል አሁን ያለበት ሁኔታ ስናነሳ፣ የጥናት አገልግሎት ቤት ለቤትም ኦንላይንም እየሰጠን ነወ። በመንግሥት ትምህርት ቤት ላሉና በትምህርት ውጤታቸው ዝቅ ያሉትን ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ጋር በመነጋገር፣ ለእነሱ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገርን ነው። ዓለማቀፍ ተቋማትም ፈንድ እንዲያደርጉና ልጆቹ ትምህርታቸውን የሚያሻሽሉበትን መንገድ ለመፍጠር እየሠራን ነው።
ዝም ብሎ ከክፍል ክፍል ከሚያልፉት በተጓዳኝ የማያልፉም አሉ። እነዚህ ልጆች እንዲያልፉ፣ ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው ከፍ ያለ ውጤት እንዲያመጡ ለማስቻል መንግሥታዊ ካልሆኑ ደርጅቶች ጋር እየሠራን ነው። በተያያዘ ደግሞ ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ ቋንቋና ታሪክ እያስተማርን ነው። ልጆች ማንነታቸውን፣ ቋንቋና ታሪካቸውን እንዳይረሱ አራቱንም ክህሎት ማዳበር የሚችሉበትን መንገድ አመቻችተናል።
ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያቀረብነው ፕሮፖዛል አለ። ይህም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በክልል ከተሞች ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፣ ከዛም ውጪ ያሉት ጋር በተመሳሳይ እየተነጋገርን እንገኛለን።
ይህ ተጽእኖ እንዲፈጥር ያሰብነው በሦስት መንገድ ነው። አንደኛ ተማሪዎችን ሲያስጠኑ ከማኅበረሰቡ ጋር እውቀቱን ያጋራል። ተማሪዎችም በነጻ የትምህርት ድጋፍ ያገኛል። ይህ እኛ በነጻ የምንሠራው ነው። እነርሱ ተማሪውን ያገናኙናል በዚህ በኩል በማስጠናት የሚሠሩ ወጣቶች አሉ ነው። ከዛ ውጪ ከክፍለ አገር የመጡ ተማሪዎች ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ይላመዳሉ። አዲስ አበባ ላይ ከተለያየ አካባቢ የመጣ ሰው አዲስ አበባ ላይ ማኅበረሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ፣ አዲስ አበባ ላይ ቤተሰበ ይኖረዋል ማለት ነው። በሁሉም አቅጣጫ ልክ እንደዛው ነው። ይህም ማኅበራዊ አገልግሎት መራራቅ የሚባለውን ነገር ይቀንሳል ብለን እናስባለን። ልጆቹም ሥራ ይለምዳሉ። ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ ማገልገልና የሥራን ባህል ቀድመው እንዲለምዱ ያስችላል። ከትምህርት ቤት ወደ ሥራው ዓለም ሲወጡ፣ ቢያንስ ልምድ አላቸው።
ስኬት ላንቺ ምን ማለት ነው?
ስኬት እንደ ሰው አረዳድ ይለያያል። በእኔ አመለካከት ስኬት የምንፈልገውን ሐሳብ ያለንን ሁሉ ተጠቅመን የምንደርስበት ግብ ነው። ስኬት አንድ ቦታ ብቻ መድረስ ነው ብዬ አላስብም። አንድን ነገር ለማሳካት ብዙ መሰናክሎች አሉ። እነዛ መሰናክሎች ሊያስቆሙን አይገባም፤ እንደውም ልንደሰትበት እና ወደ ስኬት እያመራን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ብዬ አስባለሁ።
እኔ የጀመርኳቸው ኹለቱ ድርጅቶች በመነሻ ካፒታል 10 ሺሕ ብር ከተጀመሩ ከአራት ወር በኋላ ነው የንግድ ፍቃድ በማውጣት ሥራው የቀጠለው። በአሁኑ ሰዓት ፊደል ቲቶሪያል ሁለት ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ ማግኘት የቻለ ሲሆን፣ ዓለም ማርኬቲንግ 50 ሺሕ ብር መድረስ ችሏል። ፊደል ቲቶሪያል ከአስጠኚዎች 20 በመቶ ኮሚሽን የሚወስድ ነው። ይህን ሳደርግ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፌ ነበር። ስለዚህ ወጣቶች ቶሎ ሀብታም መሆን ላይ ሳይሆን ሥራ ላይ ማተኮር አለባቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕይታን ለመቀየርና ለለውጥ የሚያነሳሱ አነቃቂ ንግግሮች ሲደረጉ እንሰማለን። በጉዳዩ ላይ የሚሠሩ አንቂዎች መኖራቸውና ለወጣቶችም ሆነ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ምን ያህል ያስፈልጋል ብለሽ ታስቢያለሽ?
አዎ! የሥነ ልቦና ውቅር ፕሮግራሞች በጣም ያስፈልጋሉ። ነገር ግን እነዚህ ሥልጠናዎችም ሆነ አጫጭር ንግግሮች የእድሜ ደረጃዎችን በመለየት መሰጠት አለባቸው። ሁላችንም ያደግንበት ማኅበረሰብ እና ቤተሰቦቻችን ሥሪቶች ነን። እናት፣ አባት እና አካባቢ ያስተማረንን እውቀት ብቻ ነው ይዘን የምናድገው።
ስለዚህ እነዚህ ንግግሮች ወጣቶች ሌላ የሕይወት ተሞክሮ እንዳለ እንዲገነዘቡ የማድረግ አስተዋጽኦ አላቸው። በእነዚህ የማኅበረሰብ አንቂዎች በኩል መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት መጣር ያስፈልጋል። በተለይ ሁሉንም ሳይሆን ለመለወጥ ዝግጁ ለሆኑ ሰዎች አስፈለጊ ነው። ይህም ከፍተኛ ጥቅም አለው ብዬ አምናለሁ።
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014


