ኢትዮጵያ በ2014 ግማሽ ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበችው የሥጋ ምርት 58.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ፡፡
የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ጥቅል አፈጻጸም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲንጻጸር የ167 በመቶ ዕድግት በማሳየት ለገበያ ከቀረበ 233 ቶን የዳልጋ ከብት ሥጋ ከ860 ሺሕ ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ የዕርድ ተረፈ ምርት፣ ማለትም ጉብት፣ ኩላሊት እና መሰል ምርቶች እንደ ቬትናምና ማሌዥያ ባሉ የሩቅ ምሥራቅ አገራት ተፈላጊነት ያላቸው በመሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ ከተላከ 2671 ቶን ተረፈ ምርት 7.3 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። በአጠቃላይ ከበግና ፍይል እንዲሁም፣ የዳልጋ ከብት እና የአህያ ሥጋ ሽያጪ 58 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኝት ተችሏል።
በግማሽ በጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ የቀረበ የሥጋ ምርት ከባለፍው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲንጻጸር 102 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ከሥጋ እና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል። ለዚሀም ጭማሪ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የበግና ፍየል ሥጋ ሲሆን፣ በ 2013 ከተላከው 5631 ቶን፣ 57 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ከ 8800 በላይ ቶን ለውጪ ገበያ ማቅረብ መቻሉንና በዚህም ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ የሥጋ ክፍል ባልደረባ፣ እንደ ፓኪስታን፣ ሕንድ እና ኔዘርላንድ ካሉ አገራት ጋር ለመወዳደርና ከእነሱ ብቃት ደረጃ ለመድረስ ከአንድ ከብት የሚገኝውን የሥጋ ምርት ማሳደግ የሚቻልባችውን አቅጣጫ መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዓለም ላይ ካሉ ከፍተኛ የሥጋ ምርት ከሚሰጡ ዝርያዎች ዘር በማስመጣት በሰው ሠራሽ (አርቴፊሻል) መንገድ የማስረገዣ ዘዴ ወይንም ኢንሲሚኔሽን የሥጋ ምርቱን የተሻለ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ለውጪ ገበያ ከቀረበ የወተት ምርት 170 ሺሕ ዶላር ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ለውጪ ገበያ ከቀረበው 451 ሺሕ ሊትር ወተት አንጻር የ2014 ግማሸ በጀት ዓመት በ9 በመቶ ቀንሷል፡፡ በተመሳሳይ የሰም ምርት በ75 በመቶ እና የአሳ ምርት 97 በመቶ ቅናሽ ማሳየታቸው የታወቀ ሲሆን፣ ለውጪ ገበያ ከቀረበ የዶሮ ምርት 115 በመቶ መሻሻል በማሳየት 300 ሺሕ ዶላር ማስገባቱ ታውቋል።
እንዲሁም፣ በግማሽ ዓመቱ በኦሮሚያ ከልል አርሲ ዞን በሚገኘው የአህያ ቄራ አማካይነት ወደ ሩቅ ምሥራቅ ገበያ ከተላከ 168 ቶን የአህያ ሥጋ ከ190 ሺሕ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ለማወቅ ተችሏል። “ሮህንግ ቻንግ” የተሠኝ መቀመጫውን በቻይና ያደረገው ቄራው፣ በ2007 በ60 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የተቋቋመ ነው፡፡ በቀን ከ300 በላይ አህያ ማረድ የሚችል መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ በጊዜው በኦሮሚያ ክልል በነበርው ተቃውሞ ለ7 ዓመታት ያለሥራ ቆሞ እንደንበረ ይታወቃል።
ከአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ የነበረውን የባህል እና የአመለካከት ተቃርኖ መፍታት በሚቻልበት ቅድመ ኔታ ላይ ተነጋግሮ ቄራው ሥራውን እንደጀመረ የሥጋ እና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቱዩቱ የሥጋ ምርት ክፍል ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ባለሙያው፣ ቄራው ካረጀ እና ከታመመ አህያ ውጪ ማረድ እንደማይችል እንዲሁም፣ በ200 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ አህያ መግዛት እንደማይችል አስረድተዋል።በተጨማሪም የማኅበረስቡ አባላት በየወሩ በሚባል ደረጃ ወደ ቄራው እየገቡ ከባህል እና እሴት ጋር ተፃራሪ ተግባራት ቄራው ውስጥ እንደማይፈጸም እንደሚመለከቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቁም በእንሰሳት ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን፣ ከ60 ሚሊዮን በላይ የዳልጋ ከብት፣ከ52 ሚሊዮን በላይ የበግ እና ፍየል፣ ከኹለት ሚሊዮን በላይ ግመል እንዲሁም፣ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጋ ዶሮ እና ከ ስምንት ሚሊዮን በላይ አህያ እንዳላት ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ከ20 በላይ ቄራዎች የሥጋ ምርታቸውን ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርቡ ለማወቅ ተቸሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014



