ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የደቡብ ሱዳን ሥደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ

0
775

ሥደተኞቹ ከ400 ሺሕ በላይ ደርሰዋል

ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል የሚገቡ የደቡብ ሱዳን ሥደተኞች ቁጥር ፣በተለይ በዚህ ወር ውስጥ፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የክልሉ መንግሥት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ከጥር 6/2014 ጀምሮ የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ባሉ ኹለት የደቡብ ሱዳን ግዛቶች መካከል በተቀሰቀሰ የእርስበርስ ግጭት ምክንያት፣ አገራቸውን ትተው ወደ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል የሚሠደዱ ደቡብ ሱዳናውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ኡጉቱ አዲንግ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሥደተኞቹ በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ የገልጹት ኃላፊው፣ ከቀናት በፊት ወደ አገራቸው የተመለሱ አሉ መባሉን አስተባብለዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በኢንታግሊ ወረዳ በሦስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች፣ በጋምቤላ ወረዳ ጀዊ በሚባል አንድ መጠለያ ጣቢያ፣ በጎግ ወረዳ በኹለት መጠለያ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም ዲማ ወረዳ ውስጥ ፊኒቶ ከተማ በሚገኝ አንድ መጠለያ ጣቢያ፣ በድምሩ በክልሉ በሚገኙ ስድስት በሚሆኑ የመጠለያ ጣቢያዎች ቁጥራቸው የበዛ ሥደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ ነው ያመላከቱት።

ሥደተኞቹ የሠፈሩት የሥደተኛ አሠፋፈር መርህን ባልጠበቀ መልኩ በአብዛኛው በከተሞች አካባቢ መሆኑ የገለጹት ኃላፋው፣ የሥደተኞች አሰፋፈር ለከተማ ቅርበት ካለው ለመቆጣጠር አስቸጋሪ የሚሆንበት ኹኔታ መኖሩን ተናግረዋል። ሥደተኞቹ ባሉባቸው አብዛኞቹ ከተሞች የሥደተኞች ቁጥር ከነዋሪ ማኅበረሰቡ የበለጠ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ይህም በክልሉ ትልቅ የደኅንነት ሥጋት መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በተለይ ኢንታግሊ ወረዳ የሚገኝ አኩላ የሚባለው ትልቅ መጠለያ ጣቢያ ወደ ድንበር የተጠጋ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የተጠለሉ ሥደተኞች እንደፈለጉ ስለሚወጡና ስለሚገቡ፣ ድንበር አቋርጠው ወደ መሀል ደቡብ ሱዳን እየገቡ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ይዘው በመመለስ ከፍተኛ የድኅንነት ሥጋት መፍጠራቸውን አብራርተዋል።

ይህ ድርጊት በክልሉ እየተበራከተ ላለው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር አንዱ ምንጩ ከመሆኑም በላይ፣ አዘዋዋሪዎቹም በአብዛኛው ደቡብ ሱዳናውያን ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። በተለይ ሥደተኞቹ የሚያደርጉት የጦር መሣሪያ ዝውውር በቀጠናው ትልቅ ሥጋት መፍጠሩን ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለፈው ጥር 9/2014 የሙርሌ ጎሳ አባላት የሆኑ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች፣ በክልሉ በሚገኘው አኮቦ ወረዳ ካንካን ቀበሌ ውስጥ ወደ ጤና ጣቢያ ሕመምተኞችን ለማድረስ በሚጓዝ አምቡላንስ ላይ ጥቃት ፈጽመው የሰው ሕይዎት ጠፍቷል ነው ያሉት።

እነዚህ ታጣቂዎች በሠነዘሩት ጥቃትም አምቡላንሷ ውስጥ የነበሩ ሦስት ሰዎችን እና ሌሎች በአካባቢው የነበሩ አምስት ሰዎችን ከገደሉ በኋላ መኪናዋን ማቃጠላቸውን አሳውቀዋል። በድምሩ ስምንት ሰዎችን የገደሉት ታጣቂዎቹ፣ በዕለቱ በሌሎች አምስት ንጹኃን ላይም ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ነው ኃላፊው ጨምረው ያስገነዘቡት።

የሙርሌ ታጣቂዎች በየዓመቱ ድንበር በማቋረጥ ወደ ክልሉ ዘልቀው በመግባት ሕጻናትን አፍነው የሚወስዱ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ከብቶች የሚዘርፉ ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን አካሄዳቸውን ቀይረው በንጹኃን ላይ ጥቃት ሠንዝረዋል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት ከተጠቀሰው ሌላ በክልሉ የተከሰተ ግጭት አለመኖሩን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ታጣቂዎቹም ጥቃት የሚያድርሱት ከጫካ እየወጡ በመሆኑ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እየታደኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ባለው መረጃ የሥደተኞች ቁጥር ከ400 ሺሕ በላይ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፣ አሁን ላይ ቁጥራቸው ከዚህ እንደሚልቅ እና ወደፊትም ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሠላም እስካልሠፈነ ድረስ ቁጥራቸው ይቀንሳል ተብሎ እንደማይታመን አመላክተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here