20 የውኃ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ ዕጥረት እና የዋጋ ንረት መዘጋታቸው ተገለጸ

0
888

የታሸገ ውኃ በማምረት ሥራ ላይ የተሠማሩ 20 ፋብሪካዎች በማሸጊያ ጥሬ ዕቃ ዋጋ ግሽበት እና በግብዓት ዕጥረት ምክንያት ሥራ እያቆሙ መሆኑን የታሸገ ውኃ እና ለስላሳ መጠጥ አምራቾች ማኅበር አስታወቀ፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ከተከሠተ ጀምሮ በቫይረሱ ከፍተኛ ጉዳት ከደርሰባችው መስኮች መካከል አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪው መሆኑ የሚታወቅ ነው። በቫይረሱ ምክንያት ትልልቅ የሚባሉ የቻይና ወደብ ከተሞች መዘጋታቸው እና ለወራት ከሥራ ውጪ በመቆየታቸው ምክንያት የጥሬ ዕቃ ዕጥረት፣ የዋጋ መናር፣ የኮንቴነር እና ማጓጓዣ ዕጥረት፣ በኢትዮጵያ ያሉ የታሸገ ውኃ አምራቾችንም ሆነ ሌሎች ድርጅቶችን አጣብቂኝ ውስጥ መክተቱ ታውቋል፡፡ ከዚህ ችግርና በአገሪቱ ውስጥ ካለው የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ጋር ተዳምሮ ኢንዱስትሪዎቹ ሠራተኞቻቸውን በትነው ሥራ ለማቆም እየተገደዱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከ20 በላይ ፋብሪካዎች መዘጋታቸውን ያረጋገጡት የታሸገ ውኃ እና ለስላሳ መጠጥ አምራቾች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አሽናፊ መርዕድ፣ የትኞቹ ፋብሪካዎች እንደተዘጉ ሥማቸውን መናገር ከኃላፊነታቸው እና የድርጅቶችን ሚስጥር ከመጠበቅ አንጻር እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ጉዳዩ ለሚመለከተው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መረጃዎችን አቅርበው ድጋፍ በሚደረግበት ኹኔታ ላይ ለመነጋገር እየተጠባበቁ እንደሆነ ተናግረዋል።

የዋጋ ንረቱ ከዓመት በፊት ከነበረው ከ120 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰው፣ በኮቪድ ምክንያት የነበሩ ዕገዳዎች እንኳን ከተነሱ በኋላ 53 ብር የነበረው የጥሬ ዕቃ ዋጋ በአሁኑ ሠዓት ከ 120 ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አንድ የውኃ ፋብሪካን ለማቋቋም በትንሹ ከ60 እስከ 80 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የምግብ፣ መጠጥ እና መድኃኒት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የመጠጥ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አዲስ ሰውነት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ የታሸገ ውኃ አምራች ፋብሪካዎች ከኮቪድ 19 መከሰት ጅምሮ በተለያየ መልኩ ሲፈተኑ የነበር ቢሆንም፣ እስከ አሁን በኃይል አቅርቦት ዕጥረት ወደ ኢንስቲትዩቱ የመጡ እንጂ፣ ተዘጉ ከተባሉት 20 ፋብሪካዎች ወሰጥ እስካሁን ያሳወቀ እንደሌለ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የኤክሳይስ ታክስ ዐዋጅ ከፍተኛ ተጸዕኖ ፈጥሮባቸው የነበር ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆን ኤክሳይስ ታክስ ተጥሎባቸው የነበረው ወደ 10 በመቶ ተቀንሶላቸዋል። ዘርፉ በፋብሪካ ውሰጥ ተቀጥረው ከሚሠሩ ሠራተኞች ጅምሮ እስከ አከፋፋይ እና ጫኝ አውራጆች ድርስ በመቶ ሺሕ ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ አዲስ ተናግረው፣ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ዜጎች ሥራ አልባ የመሆናቸው ዕድል እየጨመረ ይመጣል ብለዋል።

ለጥሬ ዋጋ ግሽበቱ ሌላው ምክንያት፣ ምንም እንኳን መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ዕድል ቅድሚያ እንዲያገኙ ከፈቀደላቸው መስኮች አንዱ አምራች ዘርፉ ቢሆንም፣ ካለው የዶላር ዕጥረት አንጻር በአግባቡ እየተዳረሰ አለመሆኑ ይነገራል፡፡ ስለሆነም አስመጪዎች የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ካለው ችግር አንጻር የጥቁር ገበያውን ወይንም ከ ‹‹ኤክስፖርተሮች›› በዶላር እስክ 17 ብር ጭማሪ እየገዙ መሆኑ የታሸገ ውኃ አምራቾችን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል።

‹‹የፋብሪካ ባለቤቶች ጥሬ ዕቃ የማምጣት ፍቃድ እንዲሰጣችው ጥናት ቢያቀርቡም፣ እስካሁን ምላሽ አልተሰጣቸውም›› ሲሉ አሸናፊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በአገር ውስጥ አምራቾች ቢኖሩም፣ ምርታቸው የታሸገ ውኃ አምራች ፋብሪካዎች ያላቸውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ማርካት አይችልም ሲሉ የሚገልጹት የዘርፉ ባለሙያ ቅባቱ ረታ ናቸው፡፡ መንግሥት ለመስኩ የሚገባውን ትኩረት ቢሠጠው አዲስ የሥራ መስክ በመፍጠር ረገድ የሚኖረው ሚና ቀላል የሚባል አይሆንም ሲሉ ሐሳባቸውን ሠጥተዋል፡፡

የታሸገ ውኃ ኢንዱስትሪ ከ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ካፒታል ኢንቨስት የተደርገባቸው እና ከ150 በላይ ፋብሪካዎች ያሉበት ዘርፍ እንደሆነ የሚናገሩት አሸናፊ፣ ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል እና ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ አንጻር መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መስክ መሆኑን ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here