ቢንቢ በሚል በምናውቃት ትንኝ የሚተላለፈው የወባ በሽታ የዓለማችንን ሕዝብ ከሚገድሉ በሽታዎች በግንባር ቀደም ከሚሰለፉት መካከል ይገኛል። በተለይ ከሰሀራ በታች ባሉ ሞቃታማ የአፍሪካ አገራት በከፍተኛ ቁጥር ነዋሪዎችን የምታጠቃው ትንኝን ለማጥፋት ምርምርና ጥናት መካሄድ ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ቢንቢዋ እንዳትነክስ አጎበር አድርጎ ከመተኛት ጀምሮ፣ ሽታ አትወድም እየተባለ ነጭ ሽንኩርትን የመሳሰለ ጠንካራ ጠረን ያለውን ነገር ራስጌ ጋር በማንጠልጠል ከንክሻ ለመዳን ይሞከራል።
በዘመናዊ መንገድ የተመረቱ ክትባቶችንም ሆነ የሚቀቡ ነገሮችን፣ በተለይ ወባ አለባቸው ወደሚባሉ አካባቢዎች ለሥራም ሆነ ለመዝናናት የሚጓዙ እንዲጠቀሙ ሲደረግ ቆይቷል። ቢንቢዋ የምትራባበትን የተጠራቀመ ውኃ ለማስወገድ የዝናብ ወቅት ካበቃ በኋላ ከሚጀመር የዘመቻ ፅዳት አንስቶ፣ ትንኞቹ ሊደበቁ የሚችሉባቸው ቦታዎችን በማጥፊያ ኬሚካል በመርጨት የበርካቶችን ሞት ለመታደግ ይሠራል።
በዘመናዊ ዘዴም ይሁን በተለምዶ የሚደረጉ የወባ በሽታ መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ማድረጉ የተጎጂውን ቁጥር ይቀንሳል እንጂ፣ በሽታውንም ሆነ አስተላላፊ ቢንቢዋን ማጥፋት ሳያስችል በርካታ ዐሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁንም ቢሆን አንዳንድ ቆላማ ቦታዎች ለኑሮ ምቹ እንዳይሆኑ በማድረግ የሠው ልጅን ነፃ እንቅስቃሴ ቢንቢዎቹ እንደገደቡ ይገኛል።
የወባ ትንኝ በመባል የምትታወቀውና በሽታውን በማስተላለፍ ተጠያቂ የምትደረገው ሴቷ ትንኝ እንደሆነችና፣ ለመራባት በምታደርገው ጥረት ደም ስለሚያስፈልጋት እሱን ለማግኘት ስትል በሽታውን ከሠው ሠው እንደምታስተላልፈው ከተማሪነታችን አንስቶ ሲነገር እየሰማነው ያደግነው ነው። ጨለማን ተገን አድርጋ በተለይ የመተኛ ጊዜን መርጣ በመናከሷ የተለከፈው ሠው ሕመሙ ሲመጣበት እንጂ ቀድሞ እንዳያውቀው ታደርጋለች። ችግሩ አንድ ሠው ከመታመሙ በፊት ቀድሞ ማወቅ አለማወቁ ሳይሆን፣ በአንድ ምቹ ጊዜ ተራብተው በወረርሽኝ መልክ ሊያጠቁ መቻላቸውና የሕክምና ተቋማትን አቅም መፈታተናቸው ነው።
በወባ ትንኝ አማካኝነት የሚመጣውንና “ማሌሪያ” እየተባለ በመላው ዓለም የሚታወቀው በሽታ እንደአደገኛነቱ ስለትንኟም ሆነ ስለበሽታው አብዛኛው ማኅበረሠብ የሚያውቀው ትንሽ ነው። ኬሚካል ተነክሮ ለስድስት ወር ገደማ እንዲያገለግል የሚሠራው አጎበር እንኳን፣ ከአጠቃቀም ጉድለት እስኪበተን ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል። በአንዳንድ ቦታዎች ለዓሳ ማስገሪያም እያገለገለ በቀላሉ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ሲደረግ ይስተዋላል። በዚህ ረገድ የሕብረተሠቡን ግንዛቤ ለማሳደግና አመለካከትን ለመቀየር ግብረ-ሠናይ ተቋማትም ሆኑ መንግሥት ብዙ ሠርተናል ቢሉም ከችግሩ ግዙፍነት አኳያ ብዙ እንደሚቀር አጠያያቂ አይደለም።
በሌላ በኩል፣ ስለበሽታውም ሆነ ስለትንኙ የሚደረጉ የምርምር ሥራዎች እስካሁን አልተቋረጡም። ከሠሞኑም የአሜሪካ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ስለቢንቢዋ አጥንተው ግኝታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ተሠምቷል። በ‹ሳይንስ ዴይሊ› ላይ እንደወጣው የምርምር ሥራቸው ውጤት ከሆነ፣ የወባ ትንኞቹ ቀለም የመምረጥ ዝንባሌ እንዳላቸው ነው። ግኝቱን ለየት የሚያደርገው በትንኞቹ ምርጫ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ሲሆን፣ አንዲት ቢንቢ ዕይታዋን እንድትመርጥ የሚያደርጋት ቀለም እንዳለ ነው። ንቦች የተወሠኑ ቀለሞችን መርጠው የተወሠኑትን እንደማይጠጉ ሁሉ፣ የወባ ትንኞችም በተመሳሳይ ቀይ ነገር ይስባቸዋል ተብሏል።
የወባ ትንኝ ቀለምን ለይታ ታጠቃለች የሚለው ግኝት፣ በምንተኛበትም ወቅት ሆነ ባለችበት አካባቢ ስንሆን የምንለብሰውንም ሆነ የምንሸፈንበትን ቀለም እንድንመርጥ በማድረግ የበለጠ ከንክሻዋ መዳን ያስችላል ተብሏል። የማትፈልገውን በመልበስም ሆነ የምትቀርበውን ለይቶ በማሳሳት ሠውነታችን እንዳይነከስ ማድረግ እንደሚቻል ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።
ከሠውነት የሚወጣን ትንፋሽ ተከትለው ወደሚነክሱት ሠው የሚያመሩት ቢንቢዎች፣ የሚመጡት ደም ያለበትን የሚለዩት በቀለም መሆኑን ማረጋገጥ የቻሉት ተመራማሪዎች፣ ቀይ ቀለም ምርጫቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ከቀይ በተጨማሪ ብርቱካናማ፣ ጥቁርና ወደውኃ ሠማያዊ የሚያደላ ከአረንጓዴ ጋር የተቀላቀለ ቀለም ይማርካቸዋል። የማይስባቸውና የሚርቁት ቀለም ደግሞ ወይነጠጅ፣ ነጭ፣ አረንጓዴና ሠማያዊ ነው ሲሉ፣ በምርምር አረጋግጠናል ያሉትን የትንኞቹን የቀለም ምርጫ አሳውቀዋል።
የቀለም ምርጫቸውን ማወቁ የሚጠቅመው እንዳንታያቸው ለመሸፈን ብቻ ሳይሆን፣ ዕይታቸውን አውቆ ሠውነታችን ጋር እንዳይደርሱ ለማድረግ ነው ያሉት ሳይንቲስቶች፣ የትኛውንም ዓይነት የቆዳ ቀለም ሲያዩ ቀይ ቡርትካናማ ኾኖ እንደሚታያቸው ለማወቅ ችለናል ብለዋል። ከትንፋሻችን የሚወጣ ካርቦን ዳይ ኦክሳድን የመሳሰለ ንጥረ ነገርን ተከትለው የሚነከስ ሰው ያለበትን የሚለዩት የወባ ትንኞች፣ አካባቢውን ከለዩ በኋላ ከየትኛው አካል እንደሚወጣ የሚያውቁት በቀለሙ እንደሆነ ተነግሯል።
ቢንቢዎቹን የሚስባቸው ነገር በዋነኝነት በሦስት የሚከፈል ሲሆን፣ ትንፋሽ፣ ላብና የቆዳችን የሙቀት መጠን መሆኑን ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም ይታወቁ ከነበሩት ከሦስቱ ነገሮች በተጨማሪ ቀለምም አንዱ ሳቢያቸው መሆኑ በተካሄደው ጥናት ታውቋል የተባለ ሲሆን፣ ቀይ ልብስና ጨርቅ ብቻ ሳይሆን ቆዳችን ኾኖ የሚታያቸው ብርቱካናማ ቀይ ቀለም መንገድ ጠቋሚያቸው መሆኑ ታውቋል። ጥቁር፣ ቀይም ሆነ ነጭ የቆዳ ቀለም አለው የምንለው ሠው ላይ በተመሳሳይ የሚታያቸው አመልካች ቀለምን መለወጥ የሚያስችልን የሚቀባ ዘዴን በመጠቀምም ሆነ፣ የማይፈልጉት ቀለም ያለውን ልባስ በማድረግ ከዕይታቸው በመሠወር እንዳይነክሱን ማድረግ ይቻላል ተብሏል።
ሳይንቲስቶቹ ለምርምራቸው የተጠቀሙት የተለመደ የሴቷን የቢጫ ወባ በሽታ አምጪ ትንኝ (Aedes aegypti) ዝርያ ሲሆን፣ የተለያየ ሽታና ቀለም ያለውን እንደአማራጭ በማቅረብ የቱን እንደሚመርጡ ለማወቅ ችለዋል። ሴቷ ትንኝ ብቻ ስትሆን የሠውን ደም የምትመጠው፣ ይህን የምታደርገው ለመራባት በምትፈልግበት ጊዜ ነው። ለዚህ ዓላማዋ ስትል ሠውን የምትነክሰው በጥናቱ የተመረጠችው የቢንቢ ዝርያ ደንግ፣ ቢጫ ትኩሳት፣ ቺኩንጉንያና ዚካ በሽታንም ልታስተላልፍ ትችላለች።
ቢንቢዋን ቤተ-ሙከራ ውስጥ ለይተው፣ ቀለም አንድ ቦታ አድርገው ቢጠብቋት ምንም እንደማታደርግ ያስተዋሉት ተመራማሪዎች፣ ቀለሙ ላይ የተለያየ ጠረን እየረጩ ሲሞክሩ ፍላጎቷን ለማወቅ አስችሏቸዋል። በዚህም፣ የምትበላውን የምትመርጠው በአንድ ጠቋሚ ነገር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የስሜት ሕዋሳቶቿን በአንድነት በመጠቀም ነው ብለዋል። አንደኛውን በማዛባት እንዳትደርስ ማድረግ የሚቻል ሲሆን፣ ልዩ የሚያደርጋት ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን አሽትታ መለየት መቻሏ ነው ተብሏል።
ልክ በመንገድ ላይ ሲጓዝ የምግብ ጥሩ መዓዛ ሸቶት በዐይን ቃኝቶ ከየት እንደመጣ ለማጣራት እንደሚማትር ሠው፣ ቢንቢዎችም ከሠውና እንስሳት ትንፋሽ የሚወጣው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን ሲያሸቱ እንደሚያቅበዘብዛቸው ከዚህ ቀደም በምርምር ተረጋግጧል። ሽታው የመጣበትን ለማወቅ እንደውሾች አፍንጫቸውን ተጠቅመው በማነፍነፍ ፈንታ፣ ዐይናቸውን ተጠቅመው በማማተር ቀለምን መሠረት አድርገው ተነካሽ ኢላማቸውን ይመርጣሉ። ወደቀለሙ በማቅናትም ሞቃቱንና ለስላሳውን ቦታ በመምረጥ ደም መጠጣቸውን ይጀምራሉ።
በአንድ የቢንቢ ዝርያ ላይ የተካሄደው ይህ ጥናት በኹሉም ላይ አንድ ዓይነት ውጤት ይኖራል እንደማያስብል የተናገሩት ተመራማሪዎች፣ ቢያንስ ተመሳሳይ ስለሚሆን የአሁኑ ግኝት እንደግብዓት በመጠቀም የዘርፉን ምርምር ያግዛል ብለዋል። ላብና የተለያየ የሠውነት ኹኔታ በምርጫቸው ላይ ምን ልዩነት እንደሚያመጣ ገና ስላልታወቀ የአሁኑ ምርምር አመላካች ይሆናል ተብሏል። በአጠቃላይ፣ የተመራማሪዎቹ ግኝት በወባ የሚያዙ ሠዎችን ቁጥር ለመቀነስ የሚደረግ ጥናት ላይ አዲስ ያልታወቀን መንገድ ለመጠቆም፣ የበሽታውን መከላከያ ለማምረትና ሕብረተሠቡን ለማስተማር ያግዛል መባሉ ተጠቁሟል።
እንደዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በፈረንጆቹ 2020፣ በዓለም ዙሪያ በወባ በሽታ የተጠቁ ሠዎች ቁጥር 241 ሚሊዮን ነበር። ከእነዚህም ውስጥ 627 ሺሕ ሠዎች ለሞት ተዳርገዋል። በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ የጤና ተቋማት የወባ ታማሚዎችን ትኩረት ይነፍጋሉ በሚል፣ በተለይ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የተጠቂና ሟቾች ቁጥር በዕጥፍ ሊያድግ ይችላል ተብሎ በዓለም ጤና ድርጅት ተተንብዮ የነበረው ባይከሰትም፣ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር መጨመሩ ግን ታውቋል። ከቀደመው 2019 ዓመት በ14 ሚሊየን የተጠቂዎች ቁጥር ሲጨምር፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ በ47 ሺሕ ጨምሯል። ይህ የሆነው በሽታውን ለመከላከልና ሕመምተኞችን ለማከም ይደረግ የነበረን ጥረት የኮሮና ወረርሽኝ በማናጋቱ ነው ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014



