ቃጠሎው በሰው ህይወት ላይ ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለማድረሱ ተገልጿል
አርብ የካቲት 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ 62 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ አንድ አገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ የእሳት ቃጠሎ አደጋ እንዳጋጠመው በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
የእሳት ቃጠሎው የንብረት ውድመት ቢያደርስም በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል።
በጽህፈት ቤቱ የመንገድ ደህንነትና ትራፊክ ክፍል ባለሙያ ዋና ሳጅን ወንድ ወሰን ጌታሁን እንደገለጹት የሰሌዳ ቁጥሩ ኢት ኮድ3-99319 አውቶቡስ አደጋው ዛሬ ረፋድ ላይ ያጋጠመው በዞኑ ጅሌ ጥምጋ ወረዳ ጎዳ ቀበሌ ሲደርስ ነው።
በደረሰው አደጋ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለመመዝገብ ተሳፍረው ይጓዙ የነበሩ ተማሪዎችን ሻንጣና ዶክመንት ጨምሮ የሌሎችን ተሳፋሪዎች ንብረትም ሙሉ በሙሉ ከአውቶቡሱ ጋር መውደሙንም ገልጸዋል።
አውቶብሱ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ያጋጠመው በሞተሩ ላይ በተከሰተ የቴክኒክ ችግር እንደሚሆን ጠቅሰው፤ የቃጠለውን መንስኤ ለማጣራት ሙሉ የምርመራ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ተሽከርካሪው ከሽዋ ሮቢት ጀምሮ የጭስ ምልክት ያሳይ እንደነበርና አሽከርካሪው ፍሬን ሸራ ነው በሚል ሲያሽከረክር እንደነበር ከተሳፋሪዎች መረጃ መገኘቱንም አመልክተዋል።
በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች በሌላ መኪና ወደ ደሴ መላካቸውን አመልክተው፤ አሽከርካሪውና ረዳቱ በቁጥጥር ሥር ውለው የማጣራት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
አሽከርካሪዎች የተሽከርካሪውን አካል በመፈተሽ የተሳፋሪውን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




