የሜካኒካል ምኅንድስና ምሩቅ የሆኑት የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አማኑኤል ባልቻ ድሮን በመሥራት የተሳካ የሙከራ በረራ ማድረጋቸው ተገለጸ።
መምህሩ የሠሩት ድሮን 250 ሜትር በተሳካ ሁኔታ በበረራ መሸፈን እንደቻለም ተነግሯል።
ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ በሜካኒካል ምኅንድስና ተመርቀው በደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት እያገለገሉ ያሉት አማኑኤል ባልቻ፣ በአሁኑ ወቅትም ኹለት ድሮን እና አንድ አውሮፕላን እየሠሩ እንደሚገኝ ነው የተጠቆመው።
ዩኒቨርስቲው “የፈጠራ ቀን” በዓሉን በፓናል ውይይትና የተማሪዎቹን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች በአውደ-ርዕይ በማሳየት ባከበረበት ወቅትም፣ ተማሪዎች እየሠሯቸው ላሉ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ድጋፍ እየተደረገ እንዳለ እና በፈጠራ ሥራዎቻቸው አርዓያ የሆኑ ተማሪዎች ሽልማትና እውቅና እንደተበረከተላቸው ተመላክቷል።
ዩኒቨርስቲው እንደ ድሮን፣ የቡና መፈልፈያ ማሽን፣ የእንጨት መላጊያ፣ የጨርቃ ጨርቅ መሥሪያ ማሽኖች፣ የተለያዩ መሣሪያዎች መለዋወጫ፣ የዶሮ ማስፈልፈያ ማሽን፣ የተለያዩ ዓይነት ተሽከርካሪዎች፣ የውኃ መሳቢያ ሞተር፣ የሕፃናት ንጽህና መጠበቂያ ዳይፐር እና የመሳሰሉት ላይ በመርሃ-ግብሩ አካቶ እየሠራ እና እያበለጸገ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014


