በሚቀጥለው ዓመት ኹሉን ዐቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ይጀመራል ተባለ

አገልግሎቱ ከኹለት ዓመት በላይ ዘግይቷል

በሚቀጥለው ዓመት ኹሉንም የሕብረተሠብ ክፍል ተሳታፊ የሚያደርግ ጤና መድኅን አገልግሎት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት በሚቀጥለው ዓመት በአገሪቱ ኹሉም አካባቢዎች የሚገኙ የሕብረተሠብ ክፍሎችን ተሳታፊ የሚያደርግ የማኅበራዊ ጤና መድኅን አገልግሎት እንደሚጀምር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዘመድኩን አበበ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ገቢ ለሚያስገቡ ሠዎች የማኅበረሠብ ጤና መድኅን አገልግሎት መሥጠት ከተጀመረ ከዐሥር ዓመት ወዲህ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ቢሆንም፣ ከዚህ ባሻገር ለመሥራት እና ኹሉንም የሕብረተሠብ ክፍል ተሳታፊ የሚያደርግ የማኅበረሠብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎትን ለማስጀመር ሠፋፊ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

መሥሪያ ቤቱ በሚቀጥለው ዓመት በመጀመሪዎቹ ኹለት እና ሦስት ወራት ውስጥ አገልግሎቱን የሚሠጥ ሲሆን፣ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ አሥራ አንዱንም ክልሎች እና ኹለቱን ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም፣ ምንም እንኳን አገልግሎቱን ለማስጀመር ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ሠፊ ሥራዎች ተሠርተው የነበረ ቢሆንም፣ ማሻሻያ ዐዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ ባለመቻሉ እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በኩል ዕውቅና ባለማግኘቱ አገልግሎቱን ማስጀመር አልተቻለም ነበር ተብሏል። የተጠቀሱትን እነዚህን ችግሮች ከጤና ሚኒስቴር እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር መፍታት በመቻሉ ከመሰከረም 1/2015 ጀምሮ ኤጀንሲው የመድኅን አገልግሎቱን ሥራ የሚያስጀምርበት ዕድል ሠፊ ነው ብለዋል።

ተቋሙ አገልግሎቱን ወደ ሥራ በሚያስገባበት ወቅት፣ በመንግሥትም ሆነ በግል ድርጅቶች ውስጥ በቋሚነት እና በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችን፣ ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ከሥራ ገበታ በጡረታ የተገለሉትን እና በዓመት አንድ ጊዜ እና ከዚያ በላይ ገቢ የሚያስገቡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ተሳታፊ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

የሕዝብ ግንገኙነት ኃላፊው ዘመድኩን በተጨማሪ እንደተናገሩት፣ የማኅበረሠብ መድኅን አገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድርጅታቸው በየወሩ ከሚከፈላቸው ደሞዝ ላይ ተቆራጭ የሚያደርግ ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ደምበኞች የቤተሰብ አባላቸውንም የሚያካትቱበት መመሪያ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ መሠረት፣ የቤተሰብ አባልን የሚያካትት የሕክምና ማዕቀፍ የሚባል መመሪያ እና ደንብ እንደተዘጋጀ የገለፁት ዘመድኩን፣ ደምበኛው ከአገልግሎቱ አቅም በላይ የሆነ እና በአገር ውስጥ ደረጃ ሕክምና ሊሰጥ የማይችል ሕመም ካጋጠመው ተቋሙ አያስተናግድም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አግልግሎት በአሁን ወቅት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ማጠናቀቁን የጠቆሙት ኃላፊው፣ እስካሁን ባለው ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የማኅበረሠብ ጤና መድኅን አገልግሎት እየሠጠ እንደሚገኝ እና በዚህም ከስምንት መቶ ያላነሱ ወረዳዎችን ማዳረስ መቻሉን ነው ያመለከቱት።

ከዚህ ባለፈ፣ መሥሪያ ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ870 በላይ የሚሆኑ ወረዳዎችን የማኅበረሠብ ጤና መድኅን አገልግሎት ተሳታፊ ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here