የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቃሊቲ ላይ በ250 ሚሊዮን ብር ኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ መሆኑን የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10፣ አራት መቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚኖሩት ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሊገነባ መሆኑን ነው የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ያስታወቀው። የቢሮው የክላስተርና የመሥሪያ ቦታዎች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ግርማ አበራ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ በ 93.9 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኩ በኹለት ዙር የሚገነባ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው 40 ሔክታር መሬት ላይ እንደሚያርፍና ግንባታውም በኹለት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ነው የተናገሩት። ኢንዱስትሪ ፓርኩን ለመገንባት የዲዛይን ሥራው በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተጠናቆ፣ ኘሮጀክቱን የመገንባት አቅም ላላቸውና መሥፈርቱን ለሚያሟሉ ድርጅቶች የጨረታ ሒደት ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ነው ቢሮው ያስታወቀው። በመጀመሪያው ዙር ዕቅድ በፓርኩ ከ14 ያላነሱ ትላልቅ የሕንፃ ግንባታዎችን እንደሚሠሩ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
የፓርኩ ግንባታ በኹለት ዙር ተከፍሎ እንደሚከናወን የገለጹት ግርማ፣ ከኹለት ዓመት በኋላ የኹለተኛው ዙር ግንባታ በስንት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚወሠን ይሆናል ብለዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለ 19 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና በርካታ ግብዓቶችን የማምረት አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ፓርኩን ለማስገንባት አቅዶ የነበረው 2010 ላይ ቢሆንም፣ በበጀት ዕጥረትና ተገቢው ትኩረት ባለማግኘቱ ምክንያት ግንባታውን ለማስጀመር ለሦስት ዓመት መስተጓጎል ገጥሞት እንደነበር ተጠቁሟል።
ግርማ አያይዘውም፣ ኘሮጀክቱ መጀመሩ ከተማዋ ያላትን ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ኹለት የሚያሳድግ ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ከከፍተኛ እና ከመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ተርታ እንዲሰለፍ፣ መንግሥትም ሆነ ፕሮጀክቱን የሚረከቡ ድርጅቶች ትኩረት ሠጥተው መሥራት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።
በሌላ በኩል፣ ከተማ አስተዳደሩ በኢንተርፕራይዝና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ በከተማዋ ኢንተርፕራይዞችንና አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመለየትና ለመቆጣጠር በኹሉም ክፍለ ከተሞች በተሠራ የማጣራት ሥራ ከአምስት ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች መክሰማቸው ተነግሯል።
በከተማዋ ይኖራሉ ተብሎ ከተገመተው 43 ሺሕ 324 ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪዎችውስጥ 36 ሺሕ 670 ሲገኙ፣ ከአምስት ሺሕ በላይ ደግሞ እንደከሠሙ ተገልጿል። በዚህም ለኢንተርፕራይዞቹ መክሠም ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለመለየት በቀጣይ በትኩረት ይሠራል ተብሏል።
በበጀት ዓመቱ ከተማ አስተዳደሩ የአሠሪና ሠራተኛን ዘርፍ ሕጎች መፈፀማቸውን ክትትል ያደረገ ሲሆን፣ 8ሺሕ የሚደርሱ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ለመሥራት ታቅዶ፣ 6072 የሚደርስ የቁጥጥር ተግባራት ተከናውናል ነው የተባለው።
በዚህ የቁጥጥር ሒደት የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሠረተ፣ የሥራ ላይ ደኅንነት ያረጋገጠ እና መሰል ተግባራትን የሚያጠቃልል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እንደተሠሩ ተጠቁማል። በዚህም፣ የሠራተኞችን መብት የሚያስከብርና የሚያስጠብቅ ሥራ በዘርፉ የተከናወነ ሲሆን፣ በክትትል ተግባሩ ከ193 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን ተጠቃሚ ኹነዋል ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014



