“በድርቅ ለተጠቁ 57 ወረዳዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እየተሰራ ነው”:- የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር

0
892

ሐሙስ የካቲት 17 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በድርቁ ለተጠቁ 57 ወረዳዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒሰቴር የቆላማና አካባቢ ምርምርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እንድርያስ ጌታ ገለፁ፡፡

ድርቁ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቅረፍ በሦስት ፈርጆች የመፍትሔ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ዶ/ር እንድርያስ ተናግረዋል።

እነርሱም:- በ1ኛ ደረጃ በድርቁ ለተጠቁ ወገኖች አስቸኳይ የነፍስ አድን ሥራ ማለትም፤ ለተጎጂዎች የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የውሃና የእንስሳት መኖ አቅርቦት፤

በ2ተኛ ደረጃ የአጭር ጊዜ መልሶ ማቋቋም ማለትም አዳዲስ የውኃ ጉድጓድ መቆፈርና የተቆፈሩ ውሃ ጉድጓዶች ጥገና ማድረግ፣ መኖ ማምረትና የመኖ መጋዘን ማዘጋጀት፣ የውኃ ፓምፖችን በመጠቀም ውኃ ካለባቸው አካባቢዎች ስቦ ለተጎጂዎች ተደራሽ ማድረግ ሲሆን፤

በ3ተኛ ደረጃ ዘላቂ ልማት ማምጣት ማለትም እነዚህ አካባቢዎች የተፈጥሮ አደጋዎችን እንዲቋቋሙ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ማከናወን፣ አማራጭ የገቢ ምንጮችን ማሳደግና መሰል ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡

ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰፊ ርብርብ እያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም በሚኒስቴር መ/ቤቱ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በኩል ከዓለምባንክ፣ ከኢ.ፋ.ድ፣ ከጂ.አይ.ዜድ እና መሰል ተቋማት 1 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ተፈቅዶለት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከራሱ ወጪ በማድረግ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ምግብና ምግብ ነክ አቅርቦቶችን በመግዛት በኦሮሚያ ክልል በድርቁ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ መደረጉን መግለፃቸውን ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here