“126ኛው የአድዋ በዓል በካርኒቫል መልክ ይከበራል” :-ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን

0
1434

ሰኞ የካቲት 21 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) 126ኛው የአድዋ ድል በዓል አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በካርኒቫል መልክ በየአውራ ጎዳናዎች እንደሚከበር የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን አስታወቁ። በዓሉን በአግባቡ ያላከበረ ክልልም ሆነ የከተማ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥቱ እንደሚጠየቅም አሳስበዋል።

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለ126ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአድዋ ድል በዓልን በድምቀት ለማሳለፍ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። በዕለቱ የካቲት 23 ቀን 2014 በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች አውራጎዳናዎች ላይ በዓሉ በካርኒቫል መልክ እንደሚከበርም ነው የተናገሩት።

በዕለቱ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞችን የሚወክሉ አልባሳትንና ጌጣጌጦችን ያደረጉ ወጣቶች የተለያዩ ትርኢቶችን እንደሚያሳዩ ይጠበቃል፤ አጫጭር ተውኔትና፣ የመድረክ ላይ ትዕይንቶችም በበዓሉ ወቅት ለዕይታ ይቀርባሉ። የአገር ፍቅር ስሜት የሚያሰርጹ ሙዚቃዎችና ቀረርቶዎችም እንዲሁ በተመረጡ አደባባዮች ይቀርባሉ ብለዋል።

ነጋሪት የሚጎስሙና ዕምቢልታ የሚነፉ እንዲሁም በአገር ባህል ልብስ አጊጠው ከበሮ በመምታት ለበዓሉ ድምቀት የሚሰጡ ወጣቶች እንደሚሳተፉ በመግለጽ፤ በዓሉም በአገራዊ የአንድነት ስሜትና ባህላችንን በሚያስተዋውቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት 125ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ሲከበር፤ በተለየ አኳኋን ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በምኒልክ አደባባይ መደረጉን ያስታወሱት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ በወቅቱ የከተማ አስተዳደሩ ያደረገው ዝግጅት የሚያስደንቅ ቢሆንም ዘንድሮም ከዓምናው የበለጠ እንጂ ያነሰ ዝግጅት እንደማይኖር ዕምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የአድዋ በዓል በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በጋምቤላም፣ በባህርዳር፣ ድሬዳዋና የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ እንደሚከበር ጠቁመው፤ በዓሉም በአግባቡ ያላከበረ ክልልም ሆነ የከተማ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥት እንደሚጠየቅም አሳስበዋል።

የትኛው ክልል ወይም ከተማ በዓሉን በሰላም ለማጠናቀቅ ችሏል? የትኛው አካባቢስ በዓሉን በአግባቡ አክብሯል? የሚል ምልከታ እንደሚደረግ የገለጹት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ጥሩ የሰሩት የሚወደሱበት በአግባቡ ግዴታቸውን ያልተወጡት ደግሞ ሥርዓቱን ጠብቆ የሚጠየቁበት አሰራር እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

ለበዓሉ ዝግጅት በፌዴራል ባህልና ስፖርት ሚኒስትር በኩል ዐቢይ ኮሚቴ መዋቀሩን በመግለጽ፤ እርሳቸውም የኮሚቴው አባል ሆነው እየሰሩ መሆኑን ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተናግረዋል።

በኮሚቴው ውስጥ የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። ለ126ኛው የአድዋ ድል በዓል የሚሆን ሎጎም ተዘጋጅቶ በመጽደቁ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል። ቲሸርቶችና በዓሉን እንዲሁም የአገራዊ አንድነትን የሚፈጥሩ መልዕክቶች ያዘሉ አልባሳትም ለህብረተሰቡ ይቀርባሉ ማለታቸውን የኢፕድ ዘገባ አመላክቷል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ 126ኛው የአድዋ ድል በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያውያን ሕብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ!” በሚል መሪ መልዕክት ይከበራል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here