ሐሙስ የካቲት 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በህክምና መገልገያዎች እና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሁም የጤና ክብካቤ አገልግሎት ቴክኖሎጂ እና ግብአቶች ላይ ትኩረት የሚያደርገው 6ተኛው ኢትዮ ኸልዝ ዓለም ዓቀፍ ዓውደ ርዕይና ጉባኤ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል በይፋ ተከፍቷል።
በዓለም ዓቀፍ ዓውደ ርዕዩና ጉባኤው ላይ ከባንግላዴሽ፣ ህንድ፣ ጆርዳን፤ ሱዳን፤ ደቡብአፍሪካ፤ ታይላንድ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ እና አሜሪካ መሰረታቸውን ያደረጉ ስምንት ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ ከ3 ሺሕ በላይ ሰዎችም እንደሚጎበኙት ይጠበቃል፡፡
የዘንድሮው ኹነት ለመጀምሪያ ጊዜ የህንድና የባንግላዲሽ ብሄራዊ ተሳትፎን በማረጋገጥ እድገቱን ማሳየት መቻሉን የኹነቱ አዘጋጅ የሆነው የፕራና ኤቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነብዩ ለማ በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል።
ዓውደ ርዕይ እና ጉባኤው የጤናውን ዘርፍ ልማት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በዘርፉ ተዋናዮች መካከል የንግድ ልውውጥን በማሳደግ፣ የገበያ ትስስርን በመፍጠር እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና የዕውቀት ሽግግርን በማምጣት ደረጃ ትልቅ እድልን የሚፈጥር ኹነት ነው ተብሏል።
በተጨማሪም 6ኛው ኢትዮ ኸልዝ የጤና ጉባኤ በኢትጵያ ትልቁ የህክምና ሙያ ዘርፎች ተከታታይ የሙያ መጎልበቻ መድረክ ነው ያሉት ነብዩ፤ የዘርፉ ተዋናዮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት እና ምክክር የሚያደርጉበት መሆኑንም ገልፀዋል።
በዘንድሮው ጉባኤም በአምስት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም፤ የህክምና አገልግሎት ልሕቀት፣ የታካሚ ደህንነት፣ የጨረር እና የላብራቶሪ ምርመራዎች፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ እና መድሃኒት ላይ ተከታታይ የህክምና ትምህርቶች የሚሰጡበት መሆኑም ተገልጿል።
በ6ኛው ኢትዮ ኸልዝ የጤና ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሃኪሞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ የፅንስና የማህፀን ሃኪሞች ማህበር የኢትዮጵያ የውስጥ ደዌ ሀኪሞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ራዲዮሎጂ ሶሳይቲ፣ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር የኢትዮጵያ ህዝብ ጤና ላብራቶሪዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ነርሶች ማህበር፣ የኢትዮጵያ የራዲዎ ቴክኖሎጂስቶች ማህበር እንዲሁም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ማህበር የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና እንደሚሰጡም ታውቋል።
የኹነቱ የሚዲያ አጋሮች አዲስ ማለዳ እና ሜዲካስፔስ ሲሆኑ ዓለም ዓቀፍ ዓውደ ርዕዩና ጉባኤው ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቀጥልም ለማወቅ ተችሏል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n










