አሁን ባለንበት ዘመን ከትውልዱ የሥልጣኔ ዕድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የተለያዩ የቴክኖሎጅ ውጤቶች አሉ። እነዚህ ፈጠራዎች የሠው ልጅ መረጃን ለማግኝትም ሆነ በዓለም ዙሪያ ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያደርገውን ሩጫ ቀላል እና ቀልጣፋ ያደርጋሉ። በዚህ ምክንያት ትውልዱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ጋር ያለው ትስስር እጅግ እየጨመረ መምጣቱ በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት ጉዳይ ነው።
‹ቲክቶክ› በዓለማችን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅ እና በአጭር ጊዜ ታዋቂነትን ያተረፈ የመዝናኛው ዓለም መተግበሪያ ሲሆን፣ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ እና መተግበሪያውም ተወዳጅነቱን እያስፋፋ የሚገኝ ነው። ባለቤትነቱ የቻይና የሆነው ይህ የተንቀሳቃሽ ምስል መጋሪያ ሚዲያ፣ በዓለማችን በጣም እየተወደደ እና ተደራሽነቱ እየተስፋፋ የሚገኝም ሆኗል ።
አሁን ላይ ዓለም ላይ ከአንድ ቢሊየን በላይ የሚሆኑ ሠዎች የቲክቶክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። በኢትዮጵያም ይሄን የማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ሠዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየተበራከተ መጥቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግለኝነትን የሚያንፀባርቁ የጥላቻ ንግግሮች ማስተላለፊያ እና ሰዎችን ለጥፋት የማደራጃ መድረክ፣ እንዲሁም ነውረኝነትንም ማስተዋወቂያ እየሆነ ነው ይባላል።
በተለይ ደግሞ በአገራችን ወጣቶች ዘንድ ሚዲያው በጣም እየተለመደ እና ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣ ሆኗል። ቁጥራቸው የማይናቅ ወጣቶች በቲክቶክ ሱስ የተያዙ ይመስላል። ይህ ደግሞ ወጣቱን ስለሌላ ነገር እንዳያስብ፣ ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና ጉልበቱን በአግባቡ እንዳይጠቀም ብሎም ብቁ ዜጋ እንዳይሆን እንደሚያደርገው መገመት አይከብድም። በተለይ አብዛኛው የቲክቶክ ተጠቃሚ ወጣት በአብዛኛው ከቁም ነገር ይልቅ ሹፈት፣ ቧልትና ውበትን ማሳየት፣ እንዲሁም ቅብጠት ላይ ያተኮሩ ተግባራትን ነው ለዕይታ ሲያቀርቡ የሚስተዋለው። ወጣቱ በዚህ ከቀጠለ ማኅበራዊ ሕይወቱ ይበልጥ መፈተኑ የማይቀር ነው።
ቲክቶክ በማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ ሰዎች ብቸኛ እንዲሆኑ እና የነበራቸውን ቅርርብ ችላ እንዲሉ፣ እንዲሁም የግለኝነት ስሜት እንዲያድርባቸው ከማድረግ ባሻገር፣ እራሳቸውን እንዳይገዙ ያደርጋል በሚል ይተቻል። ጊዜ ማሳለፊያ ነው ሲሉ ብዙዎች እንደጥቅም አድርገው ጎጂነቱን በኩራት ሲናገሩም ይደመጣሉ። ይህ ደግሞ በተለይ ከድህነት ጋር ለምንኖር ኢትዮጵያዊያን አቅም እንዳይኖረን፣ ሥራ እንዳንሠራ፣ ስኬታማ እንዳንሆን ያደርጋል ።
በአገራችን ያለውን የቲክቶክ አጠቃቀም፣ ያለውን ጥቅም እና ሊኖረው የሚችለውን ጉዳት በተመለከተ አዲስ ማለዳ በተለያዩ ቦታዎች ያገኘቻቸውን ወጣቶች አነጋግራለች። ሀዋርያው ጳውሎስ የሚባል የአዲስ አበባ ነዋሪ የቲክቶክን ጥቅምና ጉዳት እንዲህ ያብራራል።
ቲክቶክ በቀላሉ በየትኛውም ዓለም ወይም ቦታ ያሉ ሠዎች እራሳቸውን እና ሐሳባቸውን የሚገልፁበት እና የሚተዋወቁበት መንገድ ነው። የተለያየ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ ለኑሯችን ምንን እንዴት አድርገን መጠቀም እንዳለብን ያስረዱናል። እራሳቸውን አዝናንተው ሌሎችንም ለማዝናናት ይጠቀሙበታል ሲል የታዘበውን ይጠቅሳል።
በተለይ የማኅበረሠብ አንቂዎች መተግበሪያውን በብዛት በመጠቀም መልዕክታቸውን ብዙ ሰዎች ጋር ማድረስ ይችላሉ። ሐኪሞች፣ ሹፌሮች፣ አስተማሪዎች፣ ስፖርተኞች፣ ፖለቲከኞችና ኃይማነተኞች ኹላቸውም ለሠው ልጅ ይጠቅማል ያሉትን ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉበት መንገድ ነው። ሀብታሞች የሚነዱትን መኪና፣ የሚኖሩበትን ቤት እና ቁሳቁስ የሚያስጎበኙበትም ለታይታ የሚሆን መድረክም ነው። አንዳንዶች ደግሞ እንደ ቪዲዮ ኮንፈረንስ ቀጥታ በመግባት በመሰብሰብ የሚያወሩበት ነው። በአጠቃላይ የት ሔጀ ልተንፍስ ያለ ኹሉ መተንፈሻ ያገኘበት መድረክ ነው ይላል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ማኅበረሠቡ ዘንድ ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሷል ይላል። በተለይ በማኅበራዊ ግንኙነት ላይ የሚያሳደረው ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን በመግለጽ፣ ሠዎች ከቲክቶክ ጋር መጫወትን እንደ ብቸኛ አማራጭ ስለሚወስዱት ብቸኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ማኅበራዊነትን ሸርሽሮ ግላዊነትን ያስከትላል በማለት ስለ ቲክቶክ ያለውን ሐሳብ አጋርቶናል።
ሌላኛዋ ሐሳብ ሰጭ ደግሞ በዕምነት ፍቃዱ ትባላለች። እሷም ስለ ቲክቶክ ጥቅም እና ጉዳት አብራርታለች። ጥቅሙ አንድ ሠው ብልህ እና አስተዋይ ከሆነ የራሱን በጎ ነገር እና አስተማሪ ታሪክ ይዞ በመቅረብ የራሱን አሻራ የሚያሳርፍበት እና ተጽዕኖ የሚፈጥርበት መንገድ እንደሆነ ትገልፃለች። ለምሳሌ፣ ወቅታዊ ነገሮች ላይ ሊሠራበት ይችላል፤ የክህሎት ማስጨበጫ ሐሳቦችን ማስተላለፍም ያስችላል ብላለች። ጉዳቱን ስትገልፀው ደግሞ፣ አብዛኛው ወጣት ሚዲያውን የሚጠቀምበት መንገድ ችግር የሚስተዋልበት ነው። ሚዲያውን የመሰዳደቢያና የመተራረቢያ መንገድ ሲያደርገው አይበታለሁ ትላለች። ይህ ደግሞ ወጣቶችን ሥነ ምግባር እንዳይኖራቸው እና ልቅ እንዲሆኑ መንገድ ይከፍታል ስትል ትናገራለች።
ቲክቶክን እንዴት እንጠቀመው?
ቲክቶክን ከአገራችን ተጨባጭ ኹኔታ ጋር በማገናዘብ እና በመፈተሽ መጠቀም ይቻላል። ወጣቱ ከራሱ ዝንባሌ በመነሳት ወደ ፊት የማያሳፍረውንና የሚጠቅምን ነገር ቢያስተላልፍ መልካም ይሆናል። ከፍላጎት ጋር የተቀራረቡ በርካታ ዕውቀቶችን በመምረጥ የሚታመኑ የሚድያ አካላት ላይ በማተኮር ሐሳብንም ማካፈል ይቻላል። የቲክቶክን አደገኛነትን ለመቀነስ ኹነኛው መፍትሔ ደግሞ፣ የዜጎችን የሚድያ ግንዛቤ ማሳደግ ነው። ኹሉም ሠው በኃላፊነት የሚሠራውን ሥራ በማወቅ ለማኅበረሠቡ የሚሆን የጋራ ሐሳብ በማቅረብ፣ እያዝናና ቁም ነገር በሚያስጨብጥ ኹኔታ መተግበሪያውን መጠቀም ያስፈልጋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ወይም በጠቅላላ የኢንተርኔት ሱሰኝነት በአገራችን አሁን አሁን በተደጋጋሚ መስማቱ እየተለመደ ነው። ብዙ ጊዜ ገደብ የሌለው የበዛ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በቤተሰብ ደረጃ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ለልጆቻቸው የማስተማር የማሳወቅ ኃላፊነት ወላጆች አለባቸው። የልጆችን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በመገምገም የማኅበረሠቡን ክብር፣ ባህል እና ወግ ያልጣሰ እንዲሆን፣ እንዲሁም ከጊዜ አንጻር የተወሰነ የጊዜ ገደብ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል። ይህ በወጣቶ የሚዘወተረው ተግባር በቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመሥሪያ ቤትም የሚታይ ሱስ ነው። በፊት በፊት ሥራቸውን እየተዉ ኮምፒውተር ላይ ካርታ መጫዎትን ከሚያዘወትሩ ሠራተኞች የባሰ ችግር ለአገርም ለተጠቃሚውም ያስከትላል።
ወጣቶች ብዙ ጊዜያቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያሳልፉ እያዩ ዝም ከማለት ሕወታቸው ላይ የሚፈጥርላቸው ነገር ምን እንደሆነ በማሳሰብ፣ ከወጣቱ ሕይወት ጋር የሚሄድ ትምህርት በማስተማር ዕውቀት መፍጠር እና መቆጣጠር ይገባል። “ከእኩዮቹ እንዳይለይ” በሚል ገደብ የሌለው የሱስ አስያዥ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ነፃነት ለልጆች መስጠት መጥቀም ሳይሆን መጉዳት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ የሥነልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የበዛ ቲክቶክ አጠቃቀም በሥነ-ልቦና ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ምንድን ነው ስትል አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ቴወድሮስ ድልነሳው ሲመልሱ፣ አጫጭር፣ ኃይል ያላቸው እና በጣም የተመረጡ ቪዲዮች ስለሚሆኑ በቀላሉ የወጣቱን ትኩረት ይስባሉ። በማኅበራዊ ሥነ-ልቦና ላይ እያደረሰ ያለው ጫናን ስንመለከት፣ ቲክቶክ በባህሪው በቀላሉ ትኩረት የመሳብ አቅም ስላለው ሰዎችን ለአጭር ጊዜ ብቻ ትኩረት እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል። በተደጋጋሚ በምንጠቀምበት ጊዜ ለረጅም ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የማድረግ ብቃታችንን በማሳጣት ትዕግስት እንዳይኖረን ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።
ሰዎች ፈጣን እንዳይሆኑ እያደረገ ይገኛል የሚሉት ባለሙያው፣ ሙሉ የሆነ የአካልም ሆነ የአዕምሮ ዕድገት እንዳይኖር ያደርጋል ይላሉ። ውጤት ተኮር የሆነ እንቅስቃሴ እንዳኖርንና መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነታችን ላይ ጫና እያሳደረም ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቲክቶክ የራሱ የሆነ ጥቅም እና ጉዳት አለው ያሉ ሲሆን፣ ከጥቅሙ ስንጀምር እራስን ለማስተዋወቅ የሚያግዙ ሐሳብ እና ተሰጦ ማሳያ መንገድ ነው። በተለይ ደግሞ ጥበብ ዘርፍ ላይ ላሉና ራሳቸውን መለወጥ ለሚፈልጉ ሰዎች ትልቅ ዕድልን በመፍጠር ፈጣን የሆኑ መረጃዎችን የማስተላለፊያ ሚዲያ ነው ይላሉ ።
ቲክቶክ የምንፈልገውን ነገር ብቻ ማየት የምንችልበት መተግበሪያም ቢሆንም፣ በርካታ ጉዳቶችንም ያስከትላል። ሰዎችን በቀላሉ በመሳብ ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደርጋል። የምናነብበትን ጊዜ በቀላሉ ይሻማል። ኹሉም ሠው እራሱን እንደታዋቂ የማየት ችግር ያመጣል። “እኔ ልክ ነኝ፣ እኛ ልክ ነን” የሚል ሐሳብም ሊያስከትልብን ይችላል። የሚፈልጉትን የማያውቁ ሰዎች ደግሞ ልክ በወንዝ ላይ እንደሚንሳፈፍ ግንድ የሚጓዙበትን ዓላማ የማያውቁ ይሆናሉ የሚሉት ቴዎድሮስ፣ ጊዜያቸውን በከንቱ እንዲያጠፉ ያደርጋቸዋል ሲሉ ቲክቶክን ይገልፃሉ።
ከመንግሥትም ሆነ ከወላጅ የሚደረገው ቁጥጥርስ ምን ይመስላል?
መንግሥት የሚያገናዝብ ትውልድን የመፍጠር ኃላፊነት አለበት። ስለሆነም ለታዳጊ ሕጻናት የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ትምህርት መስጠት አለበት። መንግሥት አንዳንድ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሠራጩ ተቋማትን እያጠና፣ በፍርድ ቤት እያቀረበ አድራሻቸው የሚዘጋበት መንገድ ቢኖር ጥሩ ነው። ከዚህ የበለጠ ግን ወላጆች ለልጆች ጥቅሙን እና ጉዳቱን በግልጽ በመንገርና በማስረዳት አጠቃቀማቸውን ቢቆጣጠሩ ባይ ነኝ ሲሉ ባለሙያው ምክራቸውን ይለግሳሉ። ስለሆነም ልጆች ትኩረታቸውን በበጎ የሕይወት አቅጣጫ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ወላጆች ኃላፊነት መውሰድ ይገባቸዋል በማለት ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ወጣቱ ከእንደዚህ ዓይነት ሱስ አስያዥ ነገሮች እንዲታቀብና ለሚያጠፋው ጊዜ ትልቅ ዋጋ መስጠት እንዳለበት ይመከራል። ኹሉም ሠው ራሱን መገደብ እንዳለበት በማወቅ፣ ለሚሠራው ነገር ኃላፊነት በመውሰድና ጊዜ ወስዶ ራሱን የመፈተሽ ተግባር በየጊዜው ማከናወን እዳለበት ይነገራል። በአጠቃላይ ቲክቶክ ሰዎች በቀላሉ እንዲመሰጡ ለማድረግ ታስቦ የተሠራ ስለሆነ፣ ጉዳት እዳያመጣ ሊታሰብብት ይገባል። ከአገራችን ባህል አንፃር ለወጣቶችም ሆነ ለታዳጊዎች በቂ የሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ትምህርትም በቋሚነት መሠጠት ይኖርበታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014



