ከጅምሩ ትችት የበረታበት አገራዊ ምክክር እና ቀጣይ ፈተናዎቹ

0
1194

የኢትዮጵያ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱና እየተወሳሰቡ መምጣታቸውን ተከትሎ፣ ለችግሮቹ የጋራ መፍትሔ ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አገራዊ ምክክር ተወጥኗል፡፡ አገራዊ ምክክሩን የሚመራ ኮሚሽን ማቋቋምና ኮሚሽኑን የሚመሩ 11 ኮሚሽነሮች መረጣ ሒደት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ እስካሁን በነበረው ሒደት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያዩ አካላት ትችት ሠንዝረውበታል፡፡

ምክክሩን የሚመራውን ተቋም ማቋቋምና ኮሚሽነሮችን የመሠየም ሥራ የምክክሩ የዝግጅት ምዕራፍ ነው፡፡ አገራዊ ምክክር ያካሄዱ የዓለም አገራት ተሞክሮና በዘርፉ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚሳዩት፣ ተግባሩ ሦስት ዋና ዋና ሒደቶችን ያልፋል፡፡ የመጀመሪያው የዝግጅት ሒደት ሲሆን፣ በዚህ ሒደት ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ወደ ስኬታማ ምክክር የሚመራ መሠረት እየጣለ ስለመሆኑ ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡

የዝግጅት ሒደቱ ላይ መግባባትና መተማመን ካልተፈጠረ፣ በኹለተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘውን የምክክር ሒደትና ሦስተኛ ደረጃ በሆነው የትግበራ ሒደት ላይ ችግር እንደሚፈጠር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ አገራዊ ምክክር አድርገው በትግበራ ምዕራፍ የከሸፈባቸው አገሮች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ በአገራዊ ምክክር ላይ የተሠሩ ጥናቶችንና መጻሕፍትን በማጣቀስ፣ እንዲሁም የዘርፉን ባለሙያ በማነጋገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ማጠንጠኛ አደርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ በየዘመኑ በሚፈጠሩ ውስብስብ ችግሮች እና የዴሞክራሲ ባህል ያልዳበረበት ፖለቲካ በሚፈጥረው ተግዳሮቶች ተወጥራለች። ችግሮቹ ውስብስብና የተደራረቡ መሆናቸውን ተከትሎ የመፍትሔ በር ይከፍታል ተብሎ የታሠበው አገራዊ የምክክር ውጥን ተጀምሯል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን አገራዊ ችግር መስመር ለማስያዝ የጋራ ምክክር ያስፈልጋል የሚሉ ድምጾች ባለፉት ዓመታት ተሠምተዋል።

የአገራዊ ምክክሩን ውጥን ‹ማይንድ ሴት› ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና የተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ባለፉት ኹለት ዓመታት ሲሠሩ ቆይተዋል። በግብረ ሠናይ ድርጅቶች ቀድሞ የተጀመረው የአገራዊ ምክክር አጀንዳ ቀስ በቀስ ወደ መንግሥት ተጠግቷል። በኢትዮጵያ የሚታዩትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ምክክርና መግባባት አስፈላጊ መሆኑን እያመነ የመጣው መንግሥት፣ ሒደቱ የሚመራበት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዐዋጅ አቋቁሟል። ኮሚሽኑ ጎልተው የሚታዩ አገራዊ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙና የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ለሚሠራቸው ሥራዎች 11 ኮሚሽነሮች ተመርጠውለታል።

አገራዊ ችሮችን ለመፍታት “የብሔራዊ ውይይት” በሚል መነሻ ሐሳብ “ማይንድ ሴት ኢትዮጵያ” የተሠኘው ግብረ ሠናይ ደርጅት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲሠራ ነበር። ማይንድ ሴት ኢትዮጵያ ቅድመ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ማካሔዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፈው ኅዳር ወር እንደሚጀመር ተገልጾ ነበር። በማይንድ ሴት ኢትዮጵያ የተጀመረው ብሔራዊ ውይይት በመንግሥት ተቋም ደረጃ እንዲመራ ኮሚሽን መቋቋሙን ተከትሎ፣ ተግባሩን የማካሄድ ኃላፊነቱን አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተረክቧል።

አገራዊ ምክክር ምንድን ነው?
አገራዊ ምክክር በአንድ አገር ውስጥ ለሚፈጠሩ ቀውሶች ምላሽ የሚሠጥ፣ የጋራ ችግር መፍቻ መፍትሔ እንደሆነ በአገራዊ ምክክር ላይ የተሠሩ ጥናቶችና ጽሑፍች ያስረዳሉ።
‹ቤርግሆፍ ፋውንዴሽን› የተሠኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በ2009 ያሳተመው `National Dialogue Handbook፡ A Guide for Practitioners` የተሰኘ ጽሑፍ ስለ ብሔራዊ ውይይት ዝርዝር መረጃዎችን ያትታል። በዚህ ጽሑፍ አገራዊ ምክክሮች “…በብሔራዊ ደረጃ የሚካሄዱ የፖለቲካ ሒደቶች ሲሆኑ፣ በከባድ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት፣ ከጦርነቱ በኋላ በተከሠቱት ሑኔታዎች ወይም ሠፊ የፖለቲካ ሽግግሮች ወቅት በብዙ የአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት መካከል ስምምነት የሚፈጥር ነው” ተብሎለታል።

በጽሑፉ ላይ ለአገራዊ(ብሔራዊ) ምክክር የተሠጠው ትርጓሜ መነሻ የሆኑት በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ የተካሔዱ ብሔራዊ ውይይቶች ሲሆኑ፣ በዚህም ለትርጓሜው የሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ፣ ሱዳን፣ የሊባኖስ፣ ጆርዳን፣ የመንና ባህሬን ብሔራዊ ምክክሮችን ተጠቅሟል። ጽሑፉ እንደሚያሳየው ምክክሮቹን በቅድሚያ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመቆጣጠር እንደተጠቀሙበት የአገራቱ ተሞክሮ ያስረዳል። በኹለተኛነት በብሔራዊ ደረጃ ባለድርሻ አካላትን ያካተት እና ችግሮቻቸውን ለይተው የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ተጠቅመውበታል።

ሌላኛው ትኩረቱን ሠላምና የፖለቲካ ሽግግር ላይ አድርጎ የሚሠራ “ኢንክሉሲቭ ፒስ” የተሠኘ ዓለም ዓቀፍ ደርጅት፣ አካታች ሠላምና ሽግግር ላይ ያተኮረ `What Makes or Breaks National Dialogues?` በሚል ርዕስ አገራዊ ምክክር ያካሄዱ 17 አገራትን ተሞክሮ አካቶ ባወጣው የጥናት ሪፖርት፣ “ብሔራዊ ውይይቶች የፖለቲካ ቀውስን ለመፍታት እንደ መፍትሔ ይጠቅማሉ። ለቀውሶች፣ ለፖለቲካ ሽግግር እና ለዘላቂ ሠላም መንገድ ይከፍታሉ” ይላል።

ሱሳና ስቲጋንት እና ኤልዛቤት ሙራይ የተባሉ ጸሐፊዎች በ2007 `National Dialogues: A Tool for Conflict Transformation?` በሚል ርዕስ በተባበሩት መንግሥታት የሠላም ተቋም ድረ-ገጽ ባስነበቡት ጽሑፍ “ብሔራዊ ውይይት ለግጭት አፈታት እና ለፖለቲካዊ ለውጦች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተመራጭ መፍትሔ እየሆነ መጥቷል። ከተለመደው የልኂቃን ውሳኔ ሠጪዎች ባለፈ የአንድን አገር አካሄድ በተመለከተ ክርክርን ሊያሠፋ ይችላል። ነገር ግን፣ ሥልጣናቸውን ለማጠናከር መሪዎች አላግባብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ” ብለዋል።

ትችት የበረታበት የምክክሩ መሠረት
በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ችግሮችን በጋራ መግባባት ለመፍታት ያስችላል ተብሎ የተወጠነው አገራዊ ምክክር፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ መንግሥት የታመነበት ጉዳይ ሆኗል። ይህንኑ መሠረት አድርጎ ምክከሩን ለማካሄድ የሚያስችል የአገራዊ ኮሚሽን በዐዋጅ ተቋቁሟል።
የአገራዊ ምክክሩ ውጥን፣ በዐዋጅ የተደገፈ ኮሚሽን ከማቋቋም አንስቶ ኮሚሽኑን የሚመሩ ኮሚሽነሮች እስከ መምረጥ የደረሰ ሒደት ላይ ደርሷል። በዚህ የምክክር ውጥን አጠቃላይ ሒደቱን የሚመራና የሚያመቻች ተቋም መቋቋሙ በብዙዎች ዘንድ ድጋፍ አግኝቷል። ይሁን እንጂ፣ በዐዋጁ ማቋቋሚያው፣ በኮሚሽኖቹ አመራረጥ ሒደቶችና በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አንስቶ፣ በዘርፉ ላይ ልምድ ባካባቱ ባለሙያዎች ትችት በርትቶበታል።

እስካሁን በተከናወኑት ሒደቶች ላይ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተነሱት ጥያቄዎች የግልጸኝነት እና የገለልተኝነት ችግር ጥያቄዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በምክክር ሒደቱ ላይ የግልጸኝነት፣ ነጻነት እና ገለልተኝነት ጥያቄ እንዳለው የካቲት 19/2014 የዝግጅት ሒደቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የካቲት 3/2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የምክክር ኮሚሽኑን ማቋቋሚያ ዐዋጅ፣ የዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ እና ምልመላ፣ እንዲሁም ከሒደቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ተያያዥ ጉዳዮችን በስፋት ተመልክቻለሁ ብሏል። ከኮሚሽን ማቋቋሚያ ዐዋጅ እስከ ዕጩ ኮሚሽነሮች ምልመላ መንግሥት እየሄደበት ያለው መንገድ ከፍተኛ የገለልተኝነት እና ተአማኒነት ችግር ያለበት ነው ብሏል።

ከምክር ቤቱ በተጨማሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በየግላቸው ቅሬታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አንዳንድ ፓርቲዎች እራሳቸውን ወደ ፊት ከሚካሄደው ምክክር ማግለላቸውን ከወዲሁ እየተናገሩ ነው። ይሁን እንጂ ቅሬታ የቀረበበት እስካሁን የነበረው ሒደት እና የተነሳው የግልጸኝነት ጥያቄ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሠረተ ቢስ መሆኑን የሚገልጽ ግብረ መልስ ከማግኘቱ ባለፈ በተግባር የተቀየረ ነገር የለም።

ሒደቱን ከተቃወሙት ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ)፣ በሒደቱ የታዩ ግድፈቶች ዕርምት ተወስዶባቸው በሚቀጥሉት ሥራዎች እና ምዕራፎች ላይ የማይሻሻሉ ከሆነ፣ ምክክሩ እንዲያሳካልን የፈለግነውን ዓላማ እንደማያሳካ ሥጋቱን ገልጿል። ዐዋጁን ከማስጽደቅ ጀምሮ እስከ ኮሚሽን የማቋቋም ሒደቱ በተለያዩ ወገኖች የግልጽነት ችግር የተነሳበት “የአደባባይ ምስጢር ነው” ያለው ኢዜማ፣ ከፍተኛ የሆነ የግልጸኝነት ችግር ተመልክቻለሁ ብሏል።

ሌላኛው እስካሁን ባለው ሒደት ቅሬታውን የገለጸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) ሲሆን፣ የአገራዊ ምክክር አካሔዱ የገለልተኝነት ጥያቄ ያለበት ነው ብሏል። ኦፌኮ በምክክሩ ላይ ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች ተሳታፊ ካልሆኑ የምክክሩ አካል እንደማይሆን መግለጹ የሚታወስ ነው። የፓሪቲው መሪ መረራ ጉዲና(ፕ/ር) ከኹለት ሳምንት በፊት ለአዲስ ማለዳ በሠጡት ቃለ መጠይቅ አገራዊ ምክክሩ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ አካላትን ካላካተተ የሚታሠበውን ውጤት እንደማያመጣ ጠቁመዋል።

የአገራዊ ምክክሩ ውጤት የሚለካው በሒደቶቹ ነው የሚሉት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ በዓለም ዐቀፍ የደኅንነት ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ተመራማሪ፣ ከምክክር ዝግጅቱ እስከ መግባባት የሚደርሱ ሒደቶች ውጤታማነት፣ የምክክሩን አዎንታዊነት ማሳያዎች ናቸው ይላሉ። ተመራማሪው በኢትዮጵያ የተጀመረው አገራዊ ምክክር በተቋም እንዲመራ መደረጉ መልካም ጅሟሮ ቢሆንም፣ ሒደቱ የምክክሩ መሠረት እንደመሆኑ መጠን በአግባቡ የተካሔደ አይደለም ይላሉ።

በዓለም ላይ እስካሁን ውጤታማ አገራዊ ምክክር ያካሔዱ አገራት ትክክለኛውን ሒደት ተከትለው ምክክር በማድረጋቸው ተሳክቶላቸዋል የሚሉት ተመራማሪው፣ በሒደቱ መግባባትና መተማመን ካልተፈጠረ በመጨረሻ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ጠቁመዋል። “እስካሁን እንደተመለከትነው ብዙ አካላት ቅሬታ ያነሱት በተቋቋመው ኮሚሽንና በኮሚሽነሮች ምርጫ ግልጸኝነትና ገለልተኝነት ላይ ነው። እኔ እንደሚታየኝ የሒደቱ ትልቁ ክፍተት ከግልጸኝነት ባለፈ የዝግጅት ጊዜ የሚባለው ሒደት በአግባቡ አለመተግበሩ ነው” ይላሉ።

ተመራማሪው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት ከተፈለገ በአገራዊ ምክክሩ ላይ፣ ከኹሉም ቀዳሚ በሆነው በዝግጅት ሒደቱ ላይ ሠፊ ሥራዎች መሠራት ነበረባቸው ብለዋል። በዝግጅት ጊዜ ከሚሠሩ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል፣ እንደ ችግሩ ሥፋት በሒደቱ ላይ መተማመን እንዲኖር ምክክሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ በማኅበረሠቡ ዘንድ ሠፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ካሉ ውስብስብ ችግሮች አንጻር፣ በእጅጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ላይ መተማመንና በቂ ግንዛቤ በየደረጃው መፈጠር አለበት የሚሉት ተመራማሪው፣ ይህ ባለመሆኑ አሁንም ድረስ በተለያዩ ወገኖች ምክክሩ ችግሮቻችንን ይፈታል የሚል ዕምነት አለመፈጠሩን መረዳት ይቻላል ብለዋል።

የአገራዊ ምክክር ሒደቶች
አገራዊ ምክክር፣ የፖለቲካ ችግር በገጠማቸው አገራት ተጨማሪ ቀውሶችን ለማስቀረት ወይም ለማርገብ ተመራጭ የፖለቲካ ለውጥ ሥልት እየሆነ መምጣቱን ጥናቶች ያመላክታሉ። ስኬታማ አገራዊ ምክክር አድርገው መግባባት ላይ የደረሱ አገራት ተሞክሮ ላይ የተሠሩ ጥናቶች እና በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጽሑፎች እንደሚያስረዱት፣ አገራዊ ምክክር ሦስት መሠረታዊ ሒደቶች አሉት።

በዋናነት እስካሁን የሚታወቁት የአገራዊ ምክክር ሒደቶች፣ የዝግጅት ደረጃ(Preparation phases)፣ የምክክር ሂደት ደረጃ(process phases) እና የትግበራ ደረጃ(implementation phases) ናቸው። ቤርግሆፍ ፋውንደሽን በ2009 ያሳተመው `National Dialogue Handbook A Guide for Practitioners` “ብሔራዊ ውይይቶች በሦስት ተከታታይ ደረጃዎች ያልፋሉ። ዝግጅት፣ ሒደት እና ትግበራ። በእያንዳንዱ ደረጃ የተለያዩ ተግባራትን ማዘጋጀት ያስፈልጋል” ይላል።

የአገራዊ ምክክር የመጀመሪያ መነሻ የሆነው የዝግጅት ሒደት፣ የምክክሩን ቅርጽ መሠረት የሚያሲዝ እና የዕቅድ ጊዜ መሆኑን የሚገልጸው ጽሑፉ፣ “በዝግጅት ደረጃ ላይ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ያስፈልጋል” ይላል። ከእነዚህም ውስጥ እንደ ምሳሌ የተጠቀሱት ግጭትን መከላከል ወይም ማቆም፣ የማኅበረሰብ ግንኙነቶችን እንደገና መገንባት እና ከጦርነት በኋላ የፖለቲካውን ሥርዓትና መሠረት ልማትን እንደገና ለመገንባት መፈለግ ይገኙበታል።

ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ በታሠበው አገራዊ ምክክር የመጀመሪያ ምዕራፍ ወይም የዝግጅት ሒደት ላይ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮና ከጥናቶች ምክረ ሐሳብ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸው ተመራማሪው ጠቁመዋል።
ኹለተኛው ደረጃ ራሱ የምክክሩ የሚካሄድበት ሒደት ሲሆን፣ በአብዛኛው የሕዝብና የባለድርሻ አካላት ምክክር የሚያካሂዱበት ሲሆን፣ በዋናነት የውይይት አጀንዳዎች ወደ መድረክ የሚቀርቡበት መንገድ መሆኑን ጽሑፉ ያትታል። በዚህ ወቅት ላይ የአገሪቱ ችግሮች ተለይተው መግባባት ላይ የሚደረስበት ኹኔታ ለመፍጠር የሚመከርበት ነው።

ሦስተኛው የአገራዊ ምክክር ደረጃ የትግበራ ሒደት ሲሆን፣ የምክክሩ ቀዳሚ ሒደቶች ውጤት የሚለካበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ከብሔራዊ ውይይት የሒደት ደረጃ ውጤት ሊገኝ ይችላል።

ስለ ትግበራ ደረጃው የሚያብራራው ጽሑፉ “ሒደቱ ስምምነት በመፈረም አያልቅም፤ የራሱ ውስብስብ ፈተናዎች እና ዕድሎች ይኖሩታል” ይላል። በትግበራ ሒደት የፖለቲካ ድርድር እንደሚቀጥል የሚያብራራው ጽሑፉ፣ በጣም አስፈላጊው ነገር ሥምምነት የተደረሰባቸው ነገሮች ተግባራዊ መደረጋቸው መሆኑን ያብራራል። የአገራዊ ምክክር ሒደት አፋጣኝ የውጤት አዝማሚያዎች ሊኖሩት እንደሚችል በጽሑፉ ተመላክቷል። የአገራዊ ምክክር ውጤቱ በተኩስ አቁም ድርድር ወይም በሽምግልና ከተደረጉ ሥምምነቶች ጋር ተመሳሳይ የመሆን ዕድል እንዳለውም ያክላል።

“ኢንክሉሲቭ ፒስ” የአገራትን የምክክር ተሞክሮ በጥናት መልክ ባወጣው ጽሑፍ እንደተገለጸው፣ በጥናቱ ከተካተቱ 17 አገራት ስኬታማ ምክክር አካሒደው ውጤቱን ተግባራዊ ያደረጉት ሰባት አገራት ብቻ ናቸው ይላል። ስኬታማ ምክክር አካሒው ውጤቱን በከፊል ተግባራዊ ያደረጉት ኹለት አገራት ሲሆኑ፣ የምክክሩን ውጤት ተግባራዊ ያላደረጉ አምስት አገራት ናቸው። ሦስት አገሮች ደግሞ በብሔራዊ ምክክር መግባበት መድረስ እንዳልቻሉ ጽሑፉ ይጠቁማል።

የምክክሩ ቀጣይ ፈተናዎች
አገራዊ ምክክር የጋራ ስምምነት የሚሻ፣ የፖለቲካ ቀውስ ለገጠማቸው አገራት ለችግራቸው መውጫ በር የሚከፍት ቢሆንም፣ በሒደቱ ላይ መተማመንና የጋራ ሥምምነት ካልተፈጠረ ከችግሩ ይልቅ መዘዙ ሊያመዝን እንደሚችል ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሠላምና ድኅንነት ተመራማሪው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የተወጠነው አገራዊ ምክክር ገና ከጅምሩ የመተማመን ችግር የታየበት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በሰሜኑ ክፍል ያለው ጦርነት እና በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ተባብሶ የቀጠለው የታጣቂ ኃይሎች ጥቃት ዋናኛ እንቅፋት እንዳይሆኑ ተመራማሪው ሥጋት አላቸው።
መንግሥት በአገራዊ ምክክሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብረተኝነት የተፈረጁት ሕወሓት እና “ሽኔ” እንደማይሳተፉ መግለጹ ትልቅ ሥጋት መሆኑ እየተገለጸ ነው። የዚህ ሳምንት አዲስ ማለዳ አንደበት እንግዳ አለማየሁ አረዳ(ዶ/ር) ስለ አገራዊ ምክክሩ ተጠይቀው፣ ጦርነት ባልቆመበት ኹኔታ የምክክሩ ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን ጠቁመዋል።

“ኢንክሉሲቭ ፒስ” በአገራዊ ምክክር እነማን እንደሚካተቱ በገለጸበት የጥናቱ ምዕራፍ፣ ዋና ዋና አገራዊ የፖለቲካ ተዋንያን እንደሚካተቱ ያስቀምጣል። በዚህም መንግሥት፣ የታጠቁ ወይም ያልታጠቁ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማኅበረሠብ ድርጅቶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የኃይማኖትና የባህል ተዋናዮች መካተት እንዳለባቸው ጽሑፉ ያብራራል።

አሁን ላይ የተወጠነው አገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ላለው ችግር መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል ብዙዎች ይገልጻሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለው ወቅታዊ ኹኔታ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማካሄድ የሚያስችል አይደለም የሚሉ አሉ።
ምክክሩን እንዲመራ የተቋቋመው ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ መስፍን አርአያ(ፕ/ር) መንግሥት በኮሚሽኑ ሥራ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው እንደሚለቁ መግለጻቸው የሚታውስ ነው። ምናልባት ምክክሩን የሚመራው ኮሚሽን ወደ ፊት የሚያቀርባቸው ሐሳቦች የምክክሩን ዕንቅፋቶች ያስቀራሉ ወይስ በፈተናዎች ታጅቦ ምክክሩ እንዲካሄድ ያስችላሉ የሚለው ጉዳይ ወደፊት ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here