ብዙዎችን የሚነጥቀው የመኪና አደጋ መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

0
1521

በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሠተው የመኪና አደጋ በጦርነቱ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም ሌሎች መሠል የሰውን ልጅ ላይመለስ እስከወዲያኛው ከሚሸኙ መንስኤዎች ድርብ ችግር እየሆነ ከመጣ ሰንበትበት ቢልም መፍትሔ የተገኘለት አይመስልም።

የትኛውም አንቱ የተባለ ፈላስፋ፣ ተመራማሪ፣ መምህር እንዲሁም መሰል የዕውቀት ማደሪያ የሆነ ሰው፣ ጥበብን ተላብሶ ብዙ ትዓምራትን ማድረጉ ባይካድም፣ ሞትን ማስቀረት የቻለ የለም። ገና ዕጣ ፋንታው ያልደረሰው ካልሆነ በስተቀር ከሞት ያመለጠ አንድም አካል የለም።

በርግጥ የሠው ልጅ ከሞት ሊያመልጥ እንደማይችል ዕሙን ነው። ሆኖም ግን “አስተውሎ የተራመደ ብዙ ርቀትን ይጓዛል” እንዲሉ በማስተዋል ሕይወትን ያለጊዜው ከመቅጠፍ ማስመለጥ እየተቻለ በአሽከርካሪዎችም ሆነ በመንገደኞች እንዝህላልነት፣ ለጉዞ በማይመቸው ድልድይም ይሁን፣ በተሸከርካሪዎች የቴክኒክ ችግር የበርካታ ሠዎች ሕይወት እየተቀጠፈ ይገኛል።

በኢትዮያ ውስጥ ያሉ አሁናዊ ኹኔታዎችን ስንመለከት፣ ዜጎችን ለሞት እየዳረጉ ያሉት ከተፈጥሮ አደጋዎች ይልቅ ሠው ሠራሽ ስህተቶች መሆናቸው ሲወሳ ይሰማል። የጉዳዩን ትክክለኛነት ለመረዳት ከኮረና ቫይረስ እስከ ጦርነቱ፣ከዚያም ባለፈ በየ ወቅቱ ተጓዦችንም ሆነ እግረኞችን ለሞት የሚዳርገው የመኪና አደጋ በሠዎች ምክንያት የሚከሠቱ ችግሮች ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥም ሕዝብን ለመጨረሽ በየወቅቱ የሚፈጠሩ ክስተቶች እንዳሉ ብዙዎች ሲያወሱ ይደመጣሉ። እንደ አስተያየታቸው ከሆነ፣ “በተሽከርካሪ በኩል እንኳ ከመጠን በላይ ያገለገሉ መኪናዎችን ለሕዝብ ማመላለሻ ማድረግ፣ ሆን ብሎ ለበሰበሰ መኪና ቦሎ መግጠም” ለአደጋው መከሰትና ለዜጎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት እየሆኑ ነው።

ይህን በተመለከተም ከዓመታት በፊት የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ያረጁ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ሁኔታ ስለመኖሩ አምኖበት ይህ ዓይነቱን ጉዳይ ለመቅረፍ የሚያስችል መመሪያ ለማፅደቅ ዝግጅት ላይ መሆኑን ሲገልፅ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ለዜጎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት የሆነውና መፍትሔ ያልተዘየደለት ሰው ሰራሽ ክስተት በመኪና አደጋ እየደረሰ ያለው ችግር ነው። በመኪና አደጋ ሰዎች ሞቱ፣ ቆሰሉ የሚሉ ዜናዎች በየቀኑ እየተሠሙ መሆናቸውን ተከትሎ፣ አሁን አሁን ይህን መሰል አደጋ መስማት ለጆሮ ቅርብ እየሆነና እተለመደ የመጣ ይመስላል።

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጣው በተሽከርካሪዎች የሚደርስ አደጋ በየዓመቱ አምስት ሺሕ የሚሆኑ ሠዎችን ለሕልፈተ ሕይወት፣ 15 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎችን ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ከመዳረጉም ባሻገር፣ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ላይ ውድመትን እንደሚያስከትል የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስተር በተለያዩ ወቅቶች ለሚዲያ ተቋማት ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል።

ከጊዜ በኋላም ኢትዮጵያ በመኪና ቁጥር ከዓለም ዝቅተኛዎቹ ደረጃዎች የምትመደብ እንደሆነችና በየዓመቱ ከ5200 በላይ ሰዎችን በመኪና አደጋ በመግደል ከዓለም አገራት ቀዳሚ እንደሆነች ሲነገር ይሠማል። በኢትዮጵያ በቀን እስከ ዐሥር ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ይነገራል።

የመኪና አደጋ በየቀኑ የሚከሠት መፍትሔ ያልተገኘለት ችግር እየሆነ ስለመምጣቱ በ2014 ያጋጠሙ ችግሮች ማንሳት በቂ ነው። ባሳለፍነው የካቲት 20/2014 በአዲስ አበባ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የአዲስ አበባ ፌደሬሽን የብስክሌት ውድድር ላይ ባጋጠመ ድንገተኛ የመኪና አደጋ የአንድ ሠልጣኝ ሕይወት ማለፉ ሲነገር መቆየቱ የሚታወስ ነው።

እንዲሁም፣ ባሳለፍነው የካቲት 10/2014፣ 65 ሠው ጭኖ ከሞያሌ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ ተሸከርካሪ በጌድዮ ዞን በይርጋ ጨፌ ወረዳ በቆንቃ ቀበሌ በመገልበጡ ስድስት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈና፣ 13 ሰዎች ደግሞ ከባድ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ እንዲሁም የንብረት ኪሳራ መድረሱ የሚታወስ ነው።

በተሽከርካሪዎች የሰው ሕይወት የሚጠፋው በግጭት አደጋ ብቻ ሳይሆን፣ ቴክኒክን በተመለከተ ከሚመጡ የመቃጠል፣ የመገልበጥ፣ እንዲሁም የፍሬን መበጠስ እና በሌሎች ሠው ሠራሽ ክስተቶችም ጭምር ነው።

በ2014 ከተከሰቱት የመኪና አደጋዎች መካከል በየካቲት ወር በቃጠሎ ምክንያት የሠዎች ሕይወት ማለፉ አይዘነጋም። ባሳለፍነው የካቲት 11/2014 መነሻውን አዲስ አበባ በማድረግ 62 ሰዎችን ጭኖ ወደ ደሴ ሲጓዝ የነበረ አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ የቃጠሎ አደጋ እንደደረሰበትና በዚህም ተሳፍረው የነበሩ ተማሪዎችን ንብረት ጨምሮ ተሸከርካሪው መውደሙ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ታዲያ ተሽከርካሪው የቃጠሎ አደጋ የገጠመው ከሞተሩ ጋር በተያያዘ ቴክኒክ ችግር እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።
ከ100 ሺሕ ሰዎች መካከል 26 ነጥብ ስድስት የሚሆኑት ሰዎች በትራፊክ አደጋ ለሞት እንደሚዳረጉና በአፍሪካ የሚያጋጥሙ የመኪና አደጋዎች ከአውሮፓ ጋር ሲነጻጸር በሦሥት ዕጥፍ ከፍ እንደሚሉ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል።

መፍትሔው ምንድን ነው?
በዘርፉ የተሠማሩ ባለድርሻ አካላት እንደሚሉት ከሆነ፣ ምንም እንኳ በተሽከርካሪዎች የሚደርሰው አደጋ ከእስካሁኑ ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ ቢመጣም፣ አሁንም ቢሆን ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ ከ2010 ጀምሮ በትራፊክ የሚደርሰው አደጋ ስድስት በመቶ እየቀነሰ እንደመጣ ያመላከቱ ሲሆን፣ ይህ ግን በቂ እንዳልሆነና አደጋ ከመከሰቱ አሁንም ቢሆን ስላልቀመ ከዚህ የበለጠ መሠራት እንዳለበት ነው የገለፁት።

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የትራፊክ አደጋ 10 ገዳይ ከሚባሉ የሞት አደጋዎች በዘጠነኛ ደረጃ ይገኛል የሚሉት አረጋዊ በ2023 ወደ ሦስተኛ ደረጃ ለመቀነስ የሚያሥችል ዕቅድ እንደያዙ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
እስካሁን የሚነሱት አስተያየቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፣ የመኪና አደጋ የሚከሠተው በፍጥነት ብቻ ሳይሆን የአገልግሎት ዘመን ያለፈባቸው ተሸከርካሪዎች በሥራ ከመሠማራት ባለመታገዳቸው መሆኑን ነው።
አረጋዊ ማሩም በከተማ ውስጥ አገልግሎት ዘመናቸው ያበቃ አሮጌ መኪናዎች በሥራ ተሠማርተው እንደሚታዩ የገለፁ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቅረፍም ይበልጥ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የመኪና አደጋ ከሚደርስባቸው ሰዎች መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት እግረኞች ናቸው ያሉት አረጋዊ፣ አሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ እግረኞችን ጨምሮ ጥንቃቄ በማድረግ ራሳቸውን ከአደጋ መከላከሉ ግንባር ቀደሙ መፍትሄ ሊሆን እንደሚገባ ነው ያብራሩት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 1.3 ሚሊዮን ሠዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የጠቆሙት አረጋዊ፣ በአገራችን ከሚከሠቱት አደጋዎች መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት ከባህሪ ጋር የተያያዡ ችግሮች እንደሆኑና አደጋውን ለመቀነስ ባህሪ ላይ ይበልጥ መሠራት እንዳለበት ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

በተሽከርካሪዎች ለሚደርሱ አደጋዎች የተለያዩ ምክንቶች እንዳሉ የሚነገር ሲሆን፣ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩም የሚከተሉትን ነጥቦች እንደ ዋነኛ ችግር አንስተዋል።

አረጋዊ ለአደጋው መከሠት ምክንያት በመጀመሪያ ደረጃ ያነሱት ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ሲሆን፣ ይህንም አሠራር ለማስተካከል የሚመለከተው አካል ሁሉ ይበልጥ መሥራት እንዳለበት ነው የገለጹት።
ከዚህም በተጨማሪ ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት፣ ስልጠና ሳይወስዱ በሕገ ወጥ መንገድ መንጃ ፈቃድ በመያዝ ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር እና ሌሎችም ችግሮች ለመኪና አደጋ መከሰት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

አክለውም፣ 19 በመቶ የሚሆነው አደጋ የሚከሰተው ከተፈቀደው የፍጥነት ገደብ በላይ በማሽርከር፣ 11 በመቶ የሚሆነው የእግረኞች የቀኝ ረድፍን መያዝ መሆኑን ገልጸዋል። አረጋዊ በተያያዘ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፣ የመኪና አደጋን ይበልጥ ለመቀነስ ባህሪ ላይ በደንብ መሠራት እንዳለበት ሲሆን፣ ይህ ሲሆንም 43 በመቶ አደጋውን መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here