በ5.1 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የባቱ ሐዋሳ ፈጣን መንገድ በኹለት ዓመት መጓተቱ ተገለጸ

0
1079

በ5.1 ቢሊዮን ብር በጀት የሚገነባው የባቱ(ዝዋይ)-አርሲ ነገሌ-ሐዋሳ የፈጣን መንገድ ግንባታ በፀጥታ ችግር ምክንያት ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜ በኹለት ዓመት መጓተቱን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ከ110 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የባቱ-አርሲ ነገሌ-ሐዋሳ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ከአንድ ዓመት በፊት በአካባቢው በተደጋጋሚ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ለኹለት ዓመት መጓተቱን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ማለትም 67 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቱ አርሲ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በላይ ግንባታው እንዲቆይ እንደተገደደ እና ለዚህ ደግሞ ባለፈው ዓመት በአካባቢው ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩት የፀጥታ ችግሮች በምክንያትነት ተጠቅሠዋል።

አሁን ላይ 35 በመቶ የግንባታው ሒደት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ግንባታውን ሰኔ 30/2014 አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ከዓለም ባንክ በተገኘ 33 ቢሊዮን ብር በላይ የውጪ ብድር፣ የግንባታ ሥራው በእስራኤል አገር ኩባንያ እየተሠራ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ኹለተኛው ምዕራፍ ማለትም 52 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአርሲ ነገሌ-ሐዋሳ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ለኹለት ዓመት ግንባታው እንዲዘገይ የተገደደ ሲሆን፣ ለዚህም ግንባታው በተጀመረባቸው የመጀመሪያዎች ወራት በአካባቢው የነበሩ ተደጋጋሚ የፀጥታ ችግሮች ለሥራው እንቅፋት በመሆናቸው ነው ተብሏል።

ይህ መንገድ ከ30 በመቶ በላይ በሚባል ደረጃ ግንባታው እንደተጠናቀቀ እና ጥር 2015 ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሎ የታሠበ ሲሆን፣ ከቻይናው ‹ኤግዚም› ባንክ በተገኘ ከ 5.1 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር፣ በቻይናው ‹ሲኦ ሲሲ› ሥራ ተቋራጭ ድርጅት አማካይነት የግንባታ ሒደቱ እየተከናወነ ይገኛል ተብሏል።

የባቱ-አርሲ ነገሌ-ሐዋሳ የፈጣን መንገድ ግንባታን ከላይ በተጠቀሱት ቀነ ገደቦች አጠናቀው፣ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ የፕሮጀክቱ ተቋራጮች ሥራውን በፍጥነት እንደሚሠሩ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በየጊዜው የግንባታውን ሒደት እንደሚከታተል ተጠቁሟል።

አሁን ላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች በመንገድ ግንባታ ክልል ውስጥ ያሉ ቤቶች አስፈላጊው ግምት ወይም ክፍያ ተከፍሏቸው በተያዘላቸው ቀነ ገደብ መሠረት መፍረስ አለመቻላቸው፣ ለተለያዩ የመንገድ ግንባታዎች መዘግየት ተጠቃሽ ምክንያት እየሆኑ ነው።

በኹለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተካሄደ ያለውን የመንገድ ግንባታ፣ በ2013 በመጨረሻዎቹ ወራት ለማጠናቀቅ ታስቦ በ 2010 በየካቲት ወር ወደ ሥራ ተገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ባለው ጊዜ ግንባታው ከ 50 በመቶ በታች ነው ተብሏል።
ሞጆ-መቂ-ባቱ የሚደርሰው የመንገድ ግንባታ ግን በተያዘው ዓመት ከሦስት ወራት በፊት ተጠናቆ አገልግሎት እየሠጠ እንዳለ እና በኢትዮጵያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ እየተዳደረ መሆኑ ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here