በዋግ ኽምራ ዞን በሚገኙ አራት ወረዳዎች ርሃብ ተከሠተ

0
1631

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን በሚገኙ አራት ወረዳዎች፣ በክረምት ወቅት በቂ ዝናብ ባለመዝነቡና በጦርነቱ ምክንያት በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች ሠብላቸውን መሰብሰብ ባለመቻላቸው ርሃብ መከሠቱን ከዞኑ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
በዞኑ የሚገኙ አራት ወረዳዎች በድርቅ መጎዳታቸውንና ማኅበረሰቡ ርሃብ ላይ መሆኑን የዋግ ኽምራ ዞን ብሔረሰብ አስተዳደር የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ከፍያለው ደባሽ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዝቋላ፣ ሳህላ፣ ፃግብጅ እና አበርገሌ የተሠኙ በዞኑ የሚገኙ ወረዳዎች ድርቅ የነበረባቸው ናቸው የሚሉት ከፍያለው፣ በወረዳዎቹ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለተፈናቃይ መርዳት ይቅርና ለራሳቸውም የመሠረታዊ ፍላጎት ችግር ተጋርጦባቸዋል ብለዋል።

አራቱ ወረዳዎች በክረምት ወቅት በቂ ዝናብ አለማግኘታቸው፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በሠነዘረው ጥቃት የአካባቢው አርሶ አደሮች ሠብላቸውን መሰብስብ አለመቻላቸው ለርሃቡ መከሠት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አብራርተዋል።

በአካባቢው የዝናብ ዕጥረት ነበር ያሉት ከፍያለው፣ ከዚህም በተጨማሪ ሕወሓት በሚሠነዝረው ጥቃት አርሶ አደሩ ምሽግ ውስጥ ስለነበር አንድም ጣሳ እህል ቤታቸው አልገባም” ሲሉ ነው አክለው የገለጹት።

ከፍያለው አክለውም፣ የድርቁ መከሠት እንደ አንድ ችግር ሆኖ ሳለ በአካባቢው ሠፍኖ የነበረው ሠላም በመደፍረሱ አርሶ አደሩ ከድርቅ ያመለጠውን ሠብል እንኳ መሰብሰብ አለመቻሉ እና አሁንም ድረስ ጦርነቱ አለመቋጨቱን ተከትሎ የተፈናቃዮች መበራከት ለርሃቡ መከሠት ድርብርብ ምክንያት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

አያይዘውም፣ በአካባቢው የተከሠተው ርሃብ እንኳን ከዞኑ ከክልሉም አቅም በላይ ስለሆነ፣ የፌደራል መንግሥትን ጣልቃ ገብነትን ይሻል ብለዋል። አስከትለውም መንግሥት “ጣልቃ መግባት ብቻ አይደለም፣ ሒዶ አካባቢውን መጎብኘት አለበት። አካባቢውን እስካላየ ድረስ ችግሩን አያቀውም” ነው ያሉት።

ኃላፊው በሌላ በኩል፣ የሕወሓት ታጣቂዎች ሠሞኑን በዝቋላ በኩል ጥቃት ማድረስ በመጀመራቸው ሚሊሻው እየተከላከለ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪ “በአንድ በኩል እየተጋደለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በርሃብ እየተጎዳ ነው። ችግሩ ከክልሉ አቅም በላይ ስለሆነ የፌራል መንግሥት በዚህ ዙሪያ በዋነኝነት ቀርቦ ማየት ግድ ይለዋል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ድርቅ ተከስቶባቸው ነበር የተባሉት ወረዳዎች ማለትም፣ ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች ጤፍ፣ ማሽላ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ እንዲሁም ፃግብጅ ወረዳ ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ እና ሌሎች ጥራጥሬዎችን በማምረት እንደሚታወቁ ከፍያለው አብራርተዋል።

በሌላ በኩል፣ የሕወሓት ታጣቂዎች በዝቋላ ሠሞኑን ጥቃት መሠንዘራቸውን ተከትሎ የኹለት ሠዎች ሕይወት ማለፉን፣ በወረዳው ሥር በሚገኙ ደብረ ፀሐይ፤ በድረ አባይ፣ አገረ ሠላምና ሰሜን በር በተባሉ ቀበሌዎች የነበሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውና በቂ ድጋፍ አለማግኘታቸው የወረዳው አደጋ መከላከል ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኃላፊ ንገስ አዱኛው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አክለውም፣ ሰሞኑን ደብረ ፀሐይ ቀበሌ ላይ ሕወሓት ትንኮሳ ጀምሮ እንደነበር የገለፁ ሲሆን፣ በወረዳው ስድስት ቀበሌዎች ብቻ የነበሩ 18 ሺሕ 304 ተፈናቆዮች በዝቋላ ወረዳ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እንደሚገኙና ከዘጠኝ ሺሕ 617 ሠዎች ውጭ ድጋፍ ማዳረስ እንዳልተቻለ ገልፀዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ወደ ዋግ ኽምራ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ ደስታዬ ጌታሁን ስልክ ብትደውልም፣ ለማንሳት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማወቅ አልተቻለም።

ከፍያለው፣ የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 70 ሺሕ ደርሷል ያሉ ሲሆን፣ ሕወሓት የሚሠነዝረውን ጥቃት ተከትሎ የዝቋላ ወረዳ ስድስት ቀበሌ ነዋሪዎ፣ የአበርገሌ፣ የፃግብጅ፣ የወፍላ (ኮረም) ነዋሪዎች መሉ ለሙሉ፣ እንዲሁም በሰቆጣ ወረዳ የሚገኙ የኹለት ቀበሌ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አብራርተዋል።

ኃላፊው በመጨረሻም፣ “በመጀመሪያ መሠራት ያለበት ሠው ማዳን ነው፤ መንግሥት አለ ተብሎ ከታሰበ ደግሞ ወደ ሠው ማዳን መሔድ ግዴታ ነው። የፌደራል መንግሥት እዛ አካባቢ ልማት እየሠራ ሊሆን ይችላል። ልማት የሚሠራው ለሠው ልጅ ነው። አሁን ግን ሠዎች የመኖር ሕልውናቸው እየጠፋ ስለሆነ ሔዶ አካባቢውን ማየት እንዳለበት መልዕክቴን አስተላልፋለሁ” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በሰቆጣ የሚገኙ 30 ሺሕ ተፈናቃዮች የመጠለያ ችግር እንደገጠማቸውና ዝቋላ ወረዳ የመድኃኒት ዕጥረት ስለመከሠቱ ስትዘግብ መቆየቷ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here