ሠሞኑን መነጋገሪያ ከሆኑ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ለቀልድና ለቧልት ምቹ የነበሩት፣ የዘይት ዕጥረቱንና የዳቦ መጀመርን የተመለከቱ ወሬዎች ናቸው። ዘይት አንድ ሺሕ ብር ገባ ተብሎ ብዙዎች በኑሮ ውድነቱ ሲማረሩ ነበር። የሕዝብ መማረርን ከቁብ ያልቆጠሩት አስተያየት ሰጪዎች ሲሳለቁ የቆዩ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ ሹፈት አዘል ቀልድ በመሠንዘር ችግሩን ለመግለጽ ሞክረዋል።
ዘይት እንደስጦታ እየቀረበ፣ አብሮም እንዲተኛ እየተደረገ ፣ እንክብካቤም እየተደረገለት፣ የሃብት መገለጫ ተደርጎ እንደተወሰደ ለማሳየት የተጻፉና የተነገሩ ቀልዶችን በቁጥር መግለጽ ያስቸግራል። ባል ጠብ እያደረገ ሲሠጥ፣ ሥጦታ ይዞ ሲገባ እግሩ ሲሳምም ሆነ ሲታጠብ የሚያሳይ፣ በሲሪንጅ ወጥ ላይ ሲጨመር፤ ዘይት ስትቀዳ አብዝታ ፌንት የምትነቅል ሴት፣ በሳኒታይዘር መርጫ ዘይትን ወጥ ላይ ሲፈነጠቅ፣ እንዲሁም እንደልጅ ታቅፈውት ሲሔዱና ተመሳሳይ የመወደዱን ጉዳይ የሚያሳዩ መልዕክቶች እስኪሰለች ማለት ይቻላል ሲቀርቡ ቆይተዋል።
ከዋናው የዘይት ችግር ይልቅ የዋጋው መወደድ ተፈላጊ እንዳደረገው ማሳየት እንጂ፣ በባህላዊ መንገድ ሲጨመቅም ሆነ የቅባት እህልን ለመጠቀም ሲሞክር የታየ ነገር የለም። መፍትሔው ላይ ሐሳብ ሲሠነዝር የሚታይም ያን ያህል ባይኖርም፣ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ግን ከመንግሥት አንስቶ ምንም ማስረጃ የሌለው ኹሉ ሲወርድባቸው ይታይ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዘይቱ መወደድም ሆነ ሕብረተሰቡ የሠጠው ትኩረት ያሳሰባቸው ሹመኞች ብልሃት ያሉትን ይዘው ብቅ ብለው ነበር። 40 ሚሊዮን ሊትር ብለው ለግለሰብ በሊትር ያከፋፍሉ ይመስል ሕብረተሰቡ ባለበት ዕጥረት ላይ፣ “ላም አለኝ በሠማይ” ብሎ እንዲጋደል አድርገዋል። ይህ ዘገባ ግን ትንሽ ቆይቶ እውነት እንዳልሆነ ተነግሮ አነስተኛ መጠን ነው ተብሎ ከነብዛቱ ለሸማቾች መከፋፈሉ ተነግሮ ነበር።
ይህ ሲሆን ሕብረተሰቡና ነጋዴው ጋር የነበረው የዘይት ዕጥረት ጠኔ፣ በሠላም ተሠልፈው በትዕግስት እንዲወስዱ አላደረገም። በአንዳንድ ቦታዎች ሕብረተሰቡ ለማግኘት ሲጋደል ሥርዓት ስለፈረሰ ፖሊስ ቢጠራም መስመር ሊይዝ ስላልቻለ ማከፋፈያው ጭራሹኑ እንዲዘጋ የተደረገበት ክስተት ነበር። በዚህ ኹኔታ ብዙዎች ተሰልፈው ዘይቱን ያገኙ ሲሆን፣ አሁንም ልማድ ያለቀቃቸው አንዳንዶች በጊዜያዊ ችግሩ ለመክበር ሲሯሯጡ መታየታቸውንም የተናገሩ አሉ።
የዘይቱ ዕጥረትና ሥርጭት ብዙ እያባባለ ባለበት ወቅት፣ ሌላ የተረሳ ዕጥረት ደግሞ በመንግሥት ተወስቷል። የዳቦ ውድነትን ያስቀራል ተብሎ የነበረውና ተቋርጦ የቆየው ሸገር ዳቦ በአዲስ መልክ ለገበያ ቀረበ ተብሎ ዜና ተሠርቶለታል። ይህ አስደሳች ቢመስልም፣ ከዕጥፍ በላይ ዋጋው እንዲጨምር መደረጉ ብዙዎችን አስከፍቷል። መንግሥት የሚያደርግለት ድጎማ ለአንድ ዳቦና ለአጠቃላይ እየተባለ የተዘረዘረ ቢሆንም፣ ትኩረት ስቦ የነበረው የዋጋው መወደድና ከዘይቱ ጋር አብሮ እንዲቀርብ መደረጉ ነው። ዘይቱን በዳቦ እያሉ ጠብሰው እንዲበሉ በሹፈት የመከሩ ቢኖሩም፣ ድጎማ ከተደረገለት የመንግሥት ዳቦ የዕገሌ ይሻላል እያሉ አነጻጽረው ያጣጣሉትም ነበሩ።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014



