የዲጂታል መታወቂያ በአምስት ክፍለ ከተሞች መሠጠት ተጀመረ

0
1217

በመዲናዋ ሕገ ወጥ የመታወቂያ ሥርጭትን ይከላከላል ተብሎ የታመነበት የዲጂታል መታወቂያ፣ በአምስት ክፍለ ከተሞች መሠጠት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ በአራዳ፣ በቦሌ፣ በየካ፣ በጉለሌ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሕገ ወጥ የመታወቂያ ሥርጭትን እና አሠራርን ይቀርፋል ተብሎ ዕምነት የተጣለበት የዲጂታል መታወቂያ ማተሚያ ማሽን እና መታወቂያ የመሥጠት ሥራ በቅርንጫፎቹ በኩል ሙሉ ለሙሉ መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ከፍተኛ አማካሪ መላክ መኮንን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ይህ ዲጂታል መታወቂያ በክፍለ ከተሞቹ ታትሞ ለነዋሪዎች መሰጠቱ ሕገ ወጥነትን ከመከላከል ጎን ለጎን፣ ደንበኞችን በፍጥነት ለማስተናገድ እንደሚረዳ እና በከተማዋ ነዋሪዎች መስተንግዶ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል።

ከፍተኛ አማካሪው አክለውም፣ ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት የዲጂታል መታወቂያ ማተሚያ ማሽን ለጊዜው ምን ያህል ወጭ እንደወጣበት መግለጽ አስፈላጊ እንዳልሆነ እና ኤጀንሲው በአዲስ አበባ ከተማ ኹሉም ክፍለ ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ፣ ከ11 ያላነሱ የማተሚያ ማሽኖች ከአንድ ሳምንት በፊት ግዥ ፈጽሞ ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ችሏል ብለዋል።

ከሚቀጥለው ሳምንት በኋላ ቂርቆስ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ለሚ ኩራ፣ አስኮ እና በሌሎች ክፍለ ከተሞች የዲጂታል መታወቂያ ማተሚያ ማሽን ተሠራጭቶ፣ በክፍለ ከተማ በኩል የመታወቂያ ኅትመቱን በማከናወን ለነዋሪዎች ፍጥነት የታከለበት አገልግሎት መሥጠት እንደሚጀመር ተገልጿል።

ከዚህ ባሻገር፣ ሕገ ወጥ አሠራርን ለመቆጣጠር የወሳኝ ኩነት ሠርትፍኬት መረጃ የሚያትሙ 250 ዘመናዊ ፕሪንተሮች በከተማዋ ለሚገኙ 125 ወረዳዎች እንደተሰጡ እና ብልሹ አሠራርን ከመከላከል ባለፈ መረጃውን የሚያትመው አካል ማንነትንም በመረጃ አስደግፎ ያሳያል ተብሏል።

ኤጀንሲው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ልምድ በመውሰድ፣ ሕገ ወጥነትን የሚከላከል ዘመናዊ መኃተሞችን በውጭ አገር ድርጅቶች በኩል አሠርቶ፣ በውጭ ጉዳይ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው ከኹሉም ክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎች የሚመጡ የሠርትፍኬት መረጃዎች፣ የፕሮግራም ስቲከሮች ሥራ መሥራቱንም መላክ ጠቅሰዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ተቋርጦ የነበረው የነዋሪነትና የመታወቂያ አገልግሎትን ከኹለት ሳምንት በፊት መጀመር የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ‹የኔት-ወርክ› መጨናነቅና አንዳንድ የመቆራረጥ ችግሮች በሚያጋጥሙባቸው አካባቢዎች የመኖሪያ አገልግሎት ብቻ እየተሰጠ ነው ተብሏል።

ኤጀንሲው፣ አሁን ላይ የተጠቀሱት ችግሮች እስከሚቀረፉ ጊዜ የተጠናከረ ክትትል እንደሚያደርግ እና የከተማዋም ነዋሪዎች ሕገ ወጥ አሠራርን በተመለከቱበት ወቅት ለሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ወይም ለፀጥታ ኃይሎች ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

ከዘህ በፊት ማለትም የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት መሠጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የመታወቂያው ኅትመት በኤጀንሲው በኩል ብቻ እንደሚከናወን እና ደንበኞችም መታወቂያውን ለማግኘት በትንሹ ከአምስት ቀናት በላይ እንደሚወስድባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሲያነሱ ይደመጥ ነበር።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ፣ ከኹለት ሳምንት በፊት ተቋርጦ የነበረውን የመታወቂያ ምትክ እና ዕድሳት አገልግሎት የካቲት 17 ቀን 2014 በኹሉም ወረዳዎች ማስጀመሩን ገልጿል።
ከዚሁ በተጨማሪ፣ ተቋርጦ የቆየው ከወረዳ ወረዳ በመሸኛ አማካይነት ሲሠጥ የነበረው አዲስ የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎትም መጀመሩ አይዘነጋም።

ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚመጡ መሸኛዎችን በመቀበል የሚሰጠው አዲስ የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት እንዳልጀመረ እና አገልግሎቱን ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here